Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየእናቶችና ሕፃናትን ጤና የሚደግፍ የ50 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

የእናቶችና ሕፃናትን ጤና የሚደግፍ የ50 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ቀን:

በስድስት ክልሎች በሚገኙ 67 ወረዳዎች የሥነ ተዋልዶ፣ የእናቶችና ሕፃናት የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚያስችል የ50 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡

በአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅትና በጤና ሚኒስቴር አማካይነት፣ ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ፕሮጀክት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ስድስት ሚሊዮን የሚደርሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

የዚሁ ፕሮጀክት የትኩረት አቅጣጫም ታካሚን ያማከለ ጥራቱን የጠበቀና ፍትሐዊ የሆነ የሕክምና አገልግሎትን ያዳርሳል፡፡ ከዚህም ሌላ በየወረዳዎቹ ለሚገኙ የጤና ተቋማት ተፈላጊ የሆኑ ልዩ፣ ልዩ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ማሟላትና ለሕክምና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠትም ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የተፈላጊ መሣሪያዎች መሟላት ደግሞ የሥነ ተዋልዶ፣ የጨቅላ ሕፃናትን የሕፃናትንና የአፍላ ወጣቶች ጤንነት በመታደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

በግንቦት 2015 የተጀመረውና እስከ ሚያዝያ 2020 ዓ.ም. ለሚቆየው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተመደበውን ገንዘብ የሸፈነው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ነው፡፡

የፕሮጀክቱን አፈጻጸም የሚከታተለውም በኅብረተሰብ ኑሮ መሻሻል፣ በጤና፣ በትምህርትና በፍትሐዊነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው ጂኤስአይ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ይፋ በሆነበት ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀው መድረክ የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ሁሉን አቀፍና ጥራቱ የተጠበቀ የጤና ሽፋን ዕቅድን ለማሳካት ያለመ ሌላ የሦስት ዓመት አዲስ ዕቅድ ሚኒስቴሩ አውጥቷል፡፡ የአሁኑ ፕሮጀክት ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጠሟት ቢሆንም ይህ ፕሮጀክት የተወሰኑ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በተለይም በግጭት የፈረሱ የጤና ተቋማትን ለማቋቋምና ሥራ ለማስጀመር እንዲሁም በገጠር የሚኖሩ እናቶችን ሞት ለመቀነስ አሁንም ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብን ጤና መጠበቅ ለአገር ዕድገት መሠረት መሆኑን የተናገሩት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር፣ አሁን ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት የአሜሪካው ተራድዖ እየተገበረ ካለው የመጀመርያ ደረጃ ጤና አገልግሎት ፕሮጀክት ጋር እንዲጣመር ተደርጎ የተነደፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተቋማቸው ባለፉት አሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ለጤናው ዘርፍ 2.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በ2014 ዓ.ም. ብቻ በመላው አገሪቱ 1.8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የሰብዓዊና የልማት ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ፕሮጀክት በአሜሪካና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለው ትብብር ቀጣይ መሆኑን እንደሚያመለክት ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ 10,000 እናቶች ከወሊድ ጋር ተያያዥ በሆኑ እክሎች ይሞታሉ ተብሎ እንደሚገመት የማዕከላዊ ስታትስቲክስም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋሞች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜም የእናቶች የሞት ምጣኔ ከሚወልዱ 100 ሺሕ እናቶች መካከል 267፣ እንዲሁም ጨቅላ ሕፃናትን በተመለከተም ከ1000 መካከል 33 ሞት ይመዘገባል፡፡

በሁለት አሠርታት ውስጥ ለውጥ ቢኖርም የእናቶች፣ እንደተወለዱና ከተወለዱ አንድ ሳምንት የሚሆናቸው ጨቅላ ሕፃናት ሞት በጣም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን፣ ይህንንም ለመቀነስ የሚቻለው ጥራቱ በከፍተኛ ደረጃ የተጠበቀ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት መሆኑን መረጃዎቹ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...