እያንዳንዱ ግለሰባዊ ድርጊት የማኅበረሰቡ የባህል ነፀብራቅ ሆኖ ይገኛል። የግለሰብና የቤተሰብ ውጤት የሆነው ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ባህል፣ ወግና ልማድን ይዞ የመጣና ለወደፊትም ያሻውን ጥሎ ይጠቅመኛል ያለውን ይዞ ይቀጥላል።
ነገር ግን እንደ ማኅበረሰብ አንድን ባህል ከሚሰጠው ማኅበራዊና ትውፊታዊ ፋይዳ አንፃር አይቶና በጥሞና ገምግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዘነ በሚል ከባህልነት መዝገብ ለመሰረዝ በርካታ ዓመታትንና ትውልድን ሊሻገር ይችላል።
ባህል ከፍ ሲል አገር ዝቅ ሲል ደግሞ የማኅበረሰብን የአኗኗርና የአመጋገብ የሥልጣኔ የደስታና የሐዘን፣ ወዘተ አመጣጥና አሁን ያለበትን ሁኔታ ወደኋላ በትዝታ እየጨለፈ ወደፊት በትንበያ እየጋለበ ያሳያል፣ ያመላክታል፣ ይመራል።
ታዲያ ይህንን ሁሉ ግሳንግስ የያዘ ታሪክ፣ ወግና ባህል የሆነ ወቅት ተነስቶ ‹‹ይህኛው አይጠቅምም ጣለው፣ ይኼኛውን አንጠልጥለው›› የሚል አካል ቢመጣ ትርፉ ልፋት ነው።

ይኼ ነገር በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሰበዞች ለተሰፋች አገር፣ በጋራ ለተገመዱ፣ እንዲሁም ሥረ መሠረታቸው ባህልና ሃይማኖት ለሆነባቸው ማኅበረሰቦች ይህንን ያዙ ሌላውን ልቀቁ ብሎ ማስረዳት በባንዳነት ከማስፈረጅ ባለፈ ሌላ ነገርም ሊያስከትል ይችላል።
ይህንን ሁሉ በማለፍ አንድ ማኅበረሰብ ያመነበትንና መገለጫዬ ነው፣ የአያት ቅድመ አያቶች ታሪክ ነው ብሎ የሚከተለውን ወግና ባህል በኃይልና በጉልበት ቢያስቆሙት የማታ ማታ አመቺ ሁኔታን ሲያገኝ ያመነበትን ነገር ማስቀጠሉ አይቀርም።
ለአብነት ላለፉት አራት አሠርታት ማኅበረሰቡ ሐዘንና ደስታውን የሚገልጽበትን፣ ሲከፋው መከፋቱን ሲመረው ምሬቱን የሚያሳይበትን ፉከራና ሽለላ ለማደብዘዝ ወይም የነበረውን ዓውድ በማስቀየር በተለይ ብሶቱን በፉከራ መልክ እንዳያቀርብ፣ በአንፃሩ መንግሥትን ለማወደስ እንጂ ለመተቸት እንዳይጠቀምበት ብዙ ጥረት ሲደረግ እንደነበር የሚናገሩት የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን ተሰማ ናቸው።
አቶ ሰለሞን በተለይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተዟዙረው ሽለላና ፉከራ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት መታዘብ መቻላቸውን ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹ጥበብ የምርምርና የጽሞና ማዕከል›› ባደረገው ዓመታዊ ዓውደ ጉባዔ ላይ ተናግረዋል፡፡
በዓውደ ጉባዔው ስለ ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አንዳንድ ነጥቦችና ልዩ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ እንዲሁም የትንቢያ ቀመራትና የታሪክ ጥቅሞች በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመድረኩ ፉከራና ሽለላ በስፋት የተነሳ ሲሆን፣ በተለይ በጎጃምና በጎንደር፣ በሸዋና በትግራይ፣ እንዲሁም በወለጋ አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦች ክፉም ይሁን ደግ ትችትም ይሁን ሙገሳን ለማቅረብ ሲገለገሉበት እንደኖሩ አቶ ሰለሞን አብራርተዋል።
‹ፉከራና ሽለላ ከብሶትና ከእንጉርጉሮ ወጣ› ሲል፣ የአንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ጀግንነትና ጀብደኝነት፣ እንዲሁም ፍርኃትና ስንፍናን በግጥም በማዋዛት እንደሚናገሩት አቶ ሰለሞን አብራርተዋል፡፡
ሽለላና ፉከራን በአንድ በኩል ፀብ አጫሪ ግጥሞችን በመግጠም ሰዎችን ለፀብና ለትንኮሳ የሚያጋልጥ ነው ሲሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፉከራ፣ ቀራርቶ፣ ሽለላ፣ ሙሾና የመሳሰሉት የማኅበረሰብ ትውፊቶችና ቅርሶች እንደሆኑ ይነገራል፡፡
ሲከፋው ሐዘኑን፣ ሲደሰት ደስታውን በግጥም መልክ የሚገልጽበት እንደሆነ ይነገራል፡፡
በየትኛውም የሃይማኖት መጻሕፍትም ሰውን መግደል ኃጢዓት ሆኖ ያስጠይቃል፡፡ በሕግም አስወንጅሎ ያሳስራል፡፡ የቀረርቶና የፉከራ ግጥሞች ግን ሰው መግደልን እንደ ጀግንነት ይቆጥራሉ፣ ገዳዩን ያሞካሻሉ፡፡
‹‹ጎበዝ ሰው ግደሉ፣ ሰው መግደል ይበጃል
ይዋል ይደር ማለት ጠላት ያደረጃል›› በማለት ግድያን ያፋጥናሉ፡፡ ጠላት ተብሎ የተፈረጀው ሰው ከዋለ ካደረ አቅሙ ይፈረጥምና ከባድ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል፡፡
በሌላ አንድ ማኅበረሰብ በግዞት ቀንበር ሲጫንበትና ነገሩ ሁሉ በመለሳለስ አልፈታለት ሲል፣ ሆምጠጥ ብሎ መታገል እንዳለበት በሽለላ መልኩ እንዲህ ሲል ያበረታታል፡፡
‹‹ኧረ ምረር ጎበዝ! ምረር እንደ ኮሶ፣ ምረር እንደ ቅል፣
አልመር ብሎ ነው ዱባ እሚቀቀል›› በማለት ማኅበረሰብን ያነቃቃል፣ ፈሪውን ያጀግናል።
አራስ ነብር ልጇን መንካት ቀርቶ በሩቅ ከተመለከቱባት አፀፋዋ ከባድ ነው፡፡ ልጇን ከጠላት ለመከላከል ሁሉን ታደርጋለች። ይህንን ሰዎች በፉከራ ሲገልጹት፡-
‹‹ቆላ ተወልዶ፣ ቆላ ያደገ››
እንደ አራስ ነብር ጠብ የለመደ›› በማለት በማንነቱ፣ በባህልና በወጉ በሃይማኖቱና በአገሩ የመጣን ጠላት ለማስፈራራት ይጠቀሙበታል።
ከዚህ ባሻገር ቀረርቶ፣ ፉከራና ሽለላ በጦርነት ወቅት ጠላትን ለማንበርከክ የወገን ጦርን ለማበረታታት የደከመን ለማንቃት የፈራን ለማጀገን እንደ ዋነኛ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ኢትዮጵያም ታላቁን የዓድዋን ጦርነት ጨምሮ በርካታ ጦርነቶችን ባካሄደችበት ወቅት ቀረርቶ፣ ፉከራና ሽለላ አንዱ የማሸነፊያ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።
‹‹እነማን ናቸው አገኘው ልቡ
ደረስንባቸው ሳይታጠፉ
እንደ ዝንጀሮ ፀሐይ ሲሞቁ
ሺ ቢወለድ ሺ ነው ጉዱ
የኢትዮጵያ ልጅ ይበቃል አንዱ›› አንዱ ማጃገኛ ነው፡፡
‹‹በለው በለው ሲል ነው የጋሜ ኩራቱ
ሴትም ትመታለች ከጋለ መሬቱ›› በማለት ጦረኞች ወደኋላ እንዳይመለሱ ያደርጋሉ።
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ሽለላ ወይም ቀረርቶን እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ተመክታ፣ በክንዷ ተፈርታ የምትኖር የጎበዞች አገር፣ የጀግኖች አምባ ናት። ኢትዮጵያዊ ግፍንና ጥቃትን አይወድም፡፡ ከዚህም የተነሳ እንኳን እሱ ራሱ ወገኑ ሲበደል ባየ ጊዜ ትዕግሥቱ ያልቅና ጠላትን ለመበቀል እጁ ይፈጥናል። ጀግንነት ሲወርድ ሲዋረድ ተያይዞ ከአባት ወደ ልጅ የተላለፈ ቅርሱ ነው። ወላጆችም ልጆቻቸው ፈለጋቸውን ተከትለው ጎበዝ ሆነው እንዲያድጉላቸው በብርቱ ይጥራሉ፡፡ የቤተሰብም ዝና ተጠብቆ እንዲኖር ሲታገሉ ማየት አዲስ ነገር አይደለም።
‹‹ስለዚህ ኢትዮጵያውያን አባቶች የጀብዱ ሥራ በናላቸው እንዲቀረፅ ልጆቻቸውን ቀረርቶ እያሰሙ ያሳድጓቸዋል። ቀረርቶ ወይም ሽለላ ማለት የጦርነት ዘፈን ነው፡፡ ወይም ወታደር በጌታው ፊት በሠልፍ መካከልና በጨዋታ ላይ የወንዶችን ወኔ ለማነቃቃት በዜማ የሚያሰማው ቃል ነው።
አቅራሪዎች በሠልፍ ውስጥ ወይም በግብር ላይ የጀግኖችን ልቦና በሽለላ እንደ በገና አውታር እየቃኙ በየጦሩ ሜዳ የወደቁትን፣ ለአገራቸው ትልልቅ ጀብዱዎች ሠርተው የሞቱትን የጦር ሥልት በሆነ ዜማ፣ ባማረ ድምፅ ምስጢር ያላቸውን ግጥሞች ባሰሙ ጊዜ፣ ባለ ሱሪዎቹን በልጓም እንደተያዙ ፈረሶች ያቅበጠብጣቸዋል፡፡ ደማቸው እንደፈላ አድርገው መቀመጥ እስኪሳናቸው፣ ቦታ እስኪጠባቸው ያሟሙቋቸዋል።
‹‹በዚህ ጊዜ አላስችል ይላቸውና ባለወኔዎቹ ብድግ ብለው መፎከር ልማዳቸው ነው። ቀረርቶና ፉከራ አይለያይም፡፡ ቀረርቶ ይቀድማል ፉከራ ወይም ድንፋታ ይከተላል። ይህንንም አተኩረን የተመለከትን እንደሆነ፣ ሽለላ ጠብ ማጫሪያ የነገር ማስነሻ ይመስላል። ሸላዮች ጀግኖችን በማመሥገን በመንቀፍና በመገሰፅ ወጣቶችን አነቃቅተው ለመንፈስ ብርታትን ካስገኙም በኋላ እንኳን የወንዶችን የሴቶችንም ቢሆን የቆራጥነት ወኔያቸውን ይቀሰቅሱታል፤›› በማለት ፉከራና ሽለላ የኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶች መገለጫ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡