ኢትዮጵያ በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ሁለት ወርቅን ጨምሮ በዘጠኝ ሜዳሊያዎች በስድስተኛነት አጠናቃለች፡፡ በሃንጋሪ መዲና ቡዳፔስት ለዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው ሩጫ፣ ውርወራና ዝላይን (ሩውዝ) ያካተተውን የአትሌቲክስ ውድድር አሜሪካ በበላይነት ስትፈጽም፣ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችውና በአምስተኛነት ያጠናቀቀችው ኬንያ ናት፡፡
በቡዳፔስት ቅዳሜ ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከናወነው የሴቶች ማራቶን ለኢትዮጵያ ሁለተኛው ወርቅ የተገኘበት ሲሆን፣ አሸናፊዋም አማኔ በሪሶ ናት፡፡ የዓምናዋ ባለ ድል ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ በሁለተኝነት ስታጠናቅቅ፣ ሞሮኳዊቷ ፋጢማ ኢዛህራና እስራኤላዊቷ ሎናህ ቼማቲ 3ኛና 4ኛ ሆነዋል፡፡

እጅግ ሞቃታማ በሆነው የቡዳፔስት አየር አራቱ ኢትዮጵያውያት ከሌሎች አትሌቶች ተነጥለው ከወጡ በኋላ ያሳዩት አሯሯጥ የብዙዎችን ቀልብ እንደሳበ ተዘግቧል፡፡
ውድድሩ በመክፈቻው በተካሄደው የሴቶች 10 ሺሕ ሜትር ፉክክር ሦስቱንም ሜዳሊያዎች በኢትዮጵያውያቱ ጉዳይ ፀጋይ፣ ለተሰንበት ግደይና እጅጋየሁ ታዬ እንደተወሰዱ በማራቶንም የሚደገም አስመስሎት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በሦስተኛነት ትከተል የነበረችው የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ያለምዘርፍ የኋላው ከባዱን ሙቀት መቋቋም ባለመቻሏ በአምስተኛነት ለማጠናቀቅ ተገዳለች፡፡
ውድድሩን በማፍጠን ተወዳዳሪዎች ወደኋላ እንዲቀሩ በማድረግ ቀድማ የሮጠችውና ፀሐይ ገመቹ ለቡድን ሥራው ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ማድረጓ ተነግሮላታል፡፡
በዕለቱ በነበረው የ3000 ሜትር መሰናክል ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን የጨበጠው ለሜቻ ግርማ፣ እንዳለፈው ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በሚያስገኘው ሁለተኛነት ተወስኗል፡፡ አሸናፊው ያምናው አሸናፊ ሞሮኳዊው ኢል ባካሊ ነው፡፡
በመዝጊያው ዕለት በተደረገው የወንዶች ማራቶን ዑጋንዳዊው ቪክቶር ኪፕላጋት ሲያሸንፍ ተከትሎት የገባው ትውልደ ኢትዮጵያ እስራኤላዊው ማሩ ተፈሪ ነው፡፡ ሦስተኛ በመሆን ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘው ልዑል ገብረሥላሴ ነው፡፡ ሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ሚልኬሳ መንገሻ 6ኛ፣ ፀጋዬ ጌታቸው 17ኛ ሲወጡ ያምናው አሸናፊ ታምራት ቶሎ በሕመም ምክንያት አቋርጦ ወጥቷል፡፡
በዘንድሮው ሻምፒዮና ወንዶች አትሌቶች አንድም የወርቅ ሜዳሊያ ያላጠለቁ ሲሆን፣ በ10 ሺሕ ሜትር የተወዳደረው ሰሎሞን ባረጋ 3ኛ በመሆን ነሐሱን አግኝቷል፡፡
በ5000 ሜትር አንድም አትሌት ለሜዳሊያ ያልታደለ ሲሆን ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወትና በሪሁ አረጋዊ በቅደም ተከተል 5ኛ፣ 6ኛና 8ኛ ሆነው ፈጽመዋል፡፡ በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክልና 5000 ሜትር ኢትዮጵያ ለሜዳሊያ ረድፍ ውስጥ አልገባችም፡፡
በመካከለኛና በረዥም ርቀት እንዲሁም በማራቶን በሁለቱ ጾታዎች የተወዳደረችው ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ለማጠናቀቅ የቻለችው በሴቶች ወርቆች ብቻ ታግዛ ነው፡፡ ቀሪዎቹ ሜዳሊያዎች 4 ብርና 6 ነሐስ ናቸው፡፡ ከአራቱ ብር ሦስቱ በሴቶች (በለተሰንበር ግደይ፣ ድርቤ ወልተጂና ጎተይቶም ገብረሥላሴ) የተገኘ ነው፡፡

ዓምና በኦሪገን (አሜሪካ) በተዘጋጀው ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በ4 ወርቅ በ4 ብርና 2 ነሐስ፣ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች ከአሜሪካ ቀጥላ በ2ኛነት ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ 20ኛውን የዓለም ሻምፒዮና የምታዘጋጀው ቶኪዮ ናት፡፡
በሻምፒዮናው የተካፈለው የኢትዮጵያ ልዑክ ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን አዲስ አበባ ሲደርስ የክብር አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
የሜዳሊያ ሠንጠረዥ
ተ.ቁ. |
አገር |
ወርቅ |
ብር |
ነሐስ |
ድምር |
1 |
አሜሪካ |
12 |
8 |
9 |
29 |
2 |
ካናዳ |
4 |
2 |
0 |
6 |
3 |
ስፔን |
4 |
1 |
0 |
5 |
4 |
ጃማይካ |
3 |
5 |
4 |
12 |
5 |
ኬንያ |
3 |
3 |
4 |
10 |
6 |
ኢትዮጵያ |
2 |
4 |
3 |
9 |
7 |
እንግሊዝ |
2 |
3 |
5 |
10 |
8 |
ኔዘርላንድ |
2 |
1 |
2 |
5 |
9 |
ኖርዌይ |
2 |
1 |
1 |
4 |
10 |
ስዊድን |
2 |
1 |
0 |
3 |