Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ የዜጎቿን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት አሳልፋ እንደማትሰጥ የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪዎች ተናገሩ

ኢትዮጵያ የዜጎቿን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት አሳልፋ እንደማትሰጥ የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪዎች ተናገሩ

ቀን:

የኢትዮጵያ የአሁኑም ሆነ የወደፊት ትውልዷን በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት አሳልፋ እንደማትሰጥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ተናገሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የመጀመሪያ ሙሌትና ውኃ አለቃቀቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል በግብፅ ካይሮ ከተማ ከነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት የተካሄደው አዲስ ድርድር የመጀመሪያ ምዕራፍ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የሦስቱ አገሮች ተደራዳሪዎች ቀጣዩን ዙር ውይይት በአዲስ አበባ ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸውንና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድንም ትናንት ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ታውቋል።

የሦስቱ አገሮች አዲስ ድርድር እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በግብፅ ካይሮ ከተማ ሲጀመር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን መሪና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)፣ የሦስትዮሽ ድርድሩ በሦስቱ አገሮች መካከል ትብብርን ለማጠናከር እንደሚረዳ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርድሩ በተጀመረበት ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አምባሳደር ስለሺ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የአሁንና የወደፊት ትውልድ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብትና ጥቅም›› መሠረታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫው አስታወቋል።

በተጨማሪም ግድቡ ለሦስቱ አገሮች የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑንና ኢትዮጵያ በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ አቋሟን አጠናክራ ድርድሩ ሁሉንም በሚያግባባ መልኩ እንዲጠናቀቅ እንደምትሠራ አምባሳደር ስለሺ (ዶ/ር) መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። 

አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በካይሮ የተካሄደው ድርድር ከተጠናቀቀ በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም ይህንኑ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት (ግድቡ በጥቂት ዓመታት ሙሉ ደረጃ እስኪደርስ ያለውን) እና የግድቡ የውኃ አለቃቀቅን የተመለከተው ድርድር ነሐሴ 22 ቀን መጠናቀቁን ያመለከቱት አምባሳደር ስለሺ፣ ካይሮ ላይ በተካሄደው ድርድር ያልተሸፈኑና ስምምነት ባልተደረሰባቸው በርካታ የስምምነት አንቀጾች ላይ ሁለተኛ ዙር ድርድር በመጪው መስከረም ወር 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሁለተኛ ዙር በማድረግ ወደ ስምምነት ለመድረስ ቀጠሮ መያዙን ገልጸዋል።

‹‹የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ወገን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅምና በቀጣይ የዓባይ ውኃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሁም በቀጣናው አገሮች መካከል ትብብርን በሚያጎለብት መልኩ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል።

በግድቡ ዙሪያ የተካሄደው የሁለት ቀናት ድርድር መጠናቀቁን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫም፣ ኢትዮጵያ በፍትሐዊና ምክንያታዊ መርህ መሠረት የራሷን ድርሻና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ድርድሩ በስምምነት እንዲቋጭ ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቋል።

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ምሕንድስና መምህርና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አማካሪ የሆኑት ይልማ ስለሺ (ፕሮፌሰር) ማክሰኞ ነሐሴ 22 ቀን በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተደረገ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ክርክር ተሳትፈው፣ ስለአጠቃላይ የድርድሩ ሒደት ባደረጉት ገለጻ፣ ሦስቱ አገሮች ቀደም ሲል ባደረጓቸው ድርድሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ ያለ ልዩነት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና አሁን በተጀመረው አዲስ ድርድር የግድቡ የውኃ ሙሌት ሊያከራክር የሚችል ነጥብ አይሆንም ብለዋል። 

ይልማ ስለሺ እንደተናገሩት፣ ሦስቱ አገሮች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ድርድሮች የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲከናወንና በውኃ ሙሌቱ ወቅት የድርቅ ሁኔታ ያጋጠመ እንደሆነ ኢትዮጵያ ውኃ እንደማትይዝ ተነጋግረው ያለ ልዩነት መስማማታቸውን አስረድተዋል።

‹‹ነገር ግን በሦስት አገሮች ድርድር ላይ አስቸጋሪ የሆነው የግድቡ ዓመታዊ ኦፕሬሽን ማለትም የግድቡ የውኃ አለቃቀን የተመለከተው ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል።

ይህንን አከራካሪ ጉዳይ በተመለከተ በግብፅ በኩል የሚቀርበው ጥያቄ ለሚቀጥሉት ሁለት አሠርት ዓመታት ከህዳሴ ግድቡ በየዓመቱ የሚለቀቀው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን በቁጥር እንዲገለጽና ለዚህም ኢትዮጵያ በውል የታሰረ ዋስትና እንድትሰጥ በግብፅ በኩል አቋም መያዙን ይልማ ስለሺ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

‹‹ይህ የግብፅ ጥያቄ በሌላ አገላለጽ ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ በላይ ባሉ አካባቢዎች ወይም በዓባይ ገባር ወንዞች ላይ ሌላ ተጨማሪ ልማት ማካሄድ የምትችለው ግብፅና ሱዳንን አሳውቃና ሁለቱ አገሮች የሚያገኙት የውኃ መጠን እንደማይቀንስ መረጋጋጥ አለበት ማለት ነው፤›› ብለዋል።

ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፣ ግብፅ የምትጠይቀው የዓባይ ውኃ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር የተደረገውን የቅኝ ግዛት ውል በመጥቀስ ሲሆን፣ ይህ በሁለቱ አገሮች መካከል ብቻ የተደረገው ውል የዓባይ ውኃ ምንጭና ተፈጥሯዊ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ከማግለሉ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የውኃ ድርሻ የማይሰጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ይህንን ፈጽሞ ልትቀበል አትችልም›› ያሉት የተደራዳሪ ቡድኑ አማካሪ ስለሺ ይልማ (ፕሮፌሰር)፣ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ‹‹በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጥያቄው በቋንቋ አጠቃቀም ተሸፍኖ የቀረበ የውኃ ክፍፍል ጥያቄ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል። 

ይህ የሦስትዮሽ ድርድር እንደ አዲስ እንዲጀመር የተወሰነው ከአንድ ወር በፊት የሱዳንን ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት በግብፅ በተካሄደው ጉባዔ ለመሳተፍ ወደ ሥፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከግብጹ አቻቸው ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት በዚህ ውይይት የህዳሴ ግድቡን ድርድር ዳግም ለማስጀመርና በአራት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ሁለቱ መሪዎች የህዳሴ ግድቡን ድርድር በአራት ወራት ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን በይፋ መግለጻቸውን ተከትሎ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ የሆኑት ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ ነገሩ ድንገተኛና እርሳቸው የማያውቁት ቢሆንም እስካሁን ስምምነት እንዳይደረስ ያደረገውን ክርክር ግብጾች ይዘው የማይቀርቡ ከሆነ በአራት ወር ባይሆንም በአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ገልጸው ነበር።

በግብፅ በኩል የሚነሳውና ስምምነት እንዳይደረስ ምክንያት የሆነው የክርክር ነጥብ በ1959 በተደረገውን የዓባይ ውኃ ክፍፍል ያገኘችውን ድርሻ እንዲጠበቅ፣ በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ በኋላ በዓባይ ውኃ ላይ ምንም ዓይነት ልማት እንዳታካሂድ አሲረው መቅረባቸው እንደሆነ የጠቀሱት ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር)፣ ግብፅ ይህንን ክርክር ከተወች በአጭር ጊዜ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...