Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተሰጣቸው ጊዜ አደረጃጀታቸውን ያላጠናቀቁ ድንበር ተሻጋሪ ትንራስፖርተሮች ጂቡቲ እንዳይገቡ ተከለከሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአክሲዮን ወይም በግል የንግድ ድርጅትነት መደራጀታቸውን በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ያላጠናቀቁና ከአክሲዮን ማኅበራቸው ጋር ውል ያልገቡ ድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ሰጪዎች፣ ጂቡቲ መግቢያ ፈቃድ ተከለከሉ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርተሮች በሚል ባወጣው ማስታወቂያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች አደረጃጀቶቻቸውን አጠናቀው የብቃት ማረጋገጫ ካልወሰዱ፣ ከነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጂቡቲ መግቢያ ፈቃድ እንደተከለከሉ አስታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ የትራንስፖርት ማኅበራት በአክሲዮን ማኅበርነት ወይም በግል ንግድ ድርጅትነት እንዲደራጁ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም የአዋጁን ማስፈጸሚያ መመርያ አዘጋጅቶ ከሁለት ወራት በፊት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

ድንበር ተሻጋሪዎችን ጨምሮ ሁሉም የትራንስፖርት ማኅበራት በመመርያው መሠረት በአክሲዮን ማኅበር ወይም፣ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መደራጀት እንደሚገባቸው ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጣው ማስታወቂያ፣ ‹‹የብቃት ማረጋገጫ ያልወሰደና በውል በታሰረ ኪራይ መልክ ወደ አደረጃጀቱ ያልገባ የተሽከርካሪ ባለንብረት፣ የጂቡቲ መግቢያ ፈቃድ አገልግሎት የማይሰጠው መሆኑን እናሳውቃለን፤›› ይላል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በርካታ የድንበር ተሻጋሪ ትራንስፖርት ሰጪዎች ማኅበራትን ያቀፈው የኢትዮጵያ ትራስንፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን  ከፍተኛ አመራር እንደገለጹት፣ የጂቡቲ መግቢያ መታወቂያ ከተከለከለ ወዲህ በርካታ አሽከርካሪዎች በሚኒስቴሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ተሠልፈዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የችግሩ መንስዔ ብለው የሚያምኑት በሕጉ መሠረት እንደ አክሲዮን ከተደራጁት ማኅበራት ጋር የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶችን ውል ተፈራርማችሁ እንድትመጡ የሚለው አሠራር ነው፡፡

ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ማኅበራቱ ወደ አክሲዮን ማኅበራት መቀየራቸውንና በአክሲዮን መደራጀታቸውን፣ ነገር ግን ባለንብረቶቹ ግለሰቦች በመሆናቸው ወደ አክሲዮንነት ከሚለወጡት ማኅበራት ጋር እንደተጠየቀው የኪራይ ውል የሚፈራረሙበት አሠራር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከአክሲዮን ማኅበራችን ጋር በውልና ማስረጃ ተዋዋሉ ነው የሚባለው፣ በውልና ማስረጃ መዋዋል ደግሞ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ የተጨማሪ አሴት ታክስና የዊዝሆልዲንግ ታክስ ጉዳይን ጨምሮ በኪራይ መዋዋል በርካታ የአሠራር ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶች ሊብሬያቸው ለንግድ አገልግሎት የሚል እንደሆነ፣ የኪራይ ውል የሚፈራረሙ ከሆነ ግን ወደ ኪራይ አገልግሎት የሚል ሊብሬ መቀየር እንደሚኖርባቸው የሚያስገድዳቸው ሌላው ችግር ሊሆን የሚችለውን ችግር አስረድተዋል፡፡  

አክሲዮኑ ከተቋቋመ በኋላ በራሱ ስም ከሚገዛው ተሽከርካሪ ውጪ ሁሉም በማኅበራት ሥር የነበሩ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ሚኒስቴሩ በሚፈልገው መሥፈርት መሠረት ለማስቀየር እንደሚቸገሩ፣ በዚህም ባለንብረቶቹ በጣም አስቸጋሪና ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

‹‹ከአክሲዮን ማኅበር ጋር ውል ስትዋዋል አክሲዮኑን በዓመት ይህን ያህል ወይም በወር ይህን ያህል ለመክፈል ተስማምቻለሁ የሚል ነው የሚሆነው›› የኢትዮጵያ ጭነት ደግሞ ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንደዚያ መሠራት አይቻልም፡፡ በየጭነቱ ነው እንጂ ሊከፈልና ውል መግባት የሚቻለው እንደዚያ መዋዋል አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

የችግሩን መንስዔና መፍትሔውን በሚመለከት ሪፖርተር አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የጠየቃቸው በትራንስፖትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የጭነትና ሎጂስቲክስ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋ ታደሰ፣ ‹‹ይህ የአሠራር ጉዳይ ነው፣ እነሱ ስለፈለጉ ሳይሆን መመርያው ላይ ስላለ ነው ተግባራዊ የሚደረገው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

አዋጁ በግንቦት ወር እንዲተገበር ደንግጎ የነበረ ቢሆንም፣ የመመርያው ዝግጅት ስለዘገየና ዘግይቶ ስለፀደቀ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አቶ ይርጋ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በማኅበር በመቆየት ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን ላለመክፈል ነው እንጂ፣ መመርያው ላይ የተቀመጠ ስለሆነ ተግባራዊ ማድረግ ግዴታ ነው፤›› ሲሉ መሪ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች