- በ7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ ውድድር ላሸነፉ ተማሪዎች ሽልማት ተበረከተ
ሁዋዌ በቻይና ሼንዘን ከተማ በተካሄደው 7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ ውድድር ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ላጠናቀቁ ዘጠኝ ተማሪዎች ታብሌቶች እንዲሁም ለአኅጉር አቀፍ ውድድር አሸናፊዎች ደግሞ የሁዋዌ አርም ባንድ ሽልማት አበረከተ። እ.ኤ.አ. በ2023-24 የሚካሄደው የአይሲቲ ውድድር መከፈቱንም ይፋ አድርጓል፡፡
ሽልማቱ ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲበረከት የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሠረተ ልማት ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር)፣ የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ግንዛቤ የሚያገኙበትና ልምድ የሚቀስሙበት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ነው ብለዋል፡፡
ውድድሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአይሲቲ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንዲሁም ጠቃሚ ልምድና የተወዳዳሪነት ባህል እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚያግዝም አክለዋል፡፡
የሁዋዌ አይሲቲ ወድድር ጥራት ያለው የአይሲቲ ችሎታን ለማፋጠን፣ ለኢንዱስትሪው ብቁ ተሰጥኦዎችን ለማዘጋጅትና ለመምረጥ፣ የመስኩ እንዲሁም ባለ ልዩ ተሰጥኦዎችን ወደፊት ለማቅረብና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ንቁ ተሳታፊዎች ለማድረግ ያግዛል ያሉት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ የመስኩ ፍላጎትና አቅርቦት በቂ እንዲሆን ለማበረታታትና በዘላቂነት አስተዋፅኦ ለማድረግ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ የተለያዩ የአይ ሲ ቲ ርዕሰ ጉዳዮችን ስለሚሸፍን ተሳታፊዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ፅንሰ ሐሳቦችን የመማር ዕድል እንደሚኖራቸው የተናገሩት ደግሞ የሁዋዌ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሊ ሚንግ የ ናችው፡፡
ተማሪዎቹ ባደረጉት የተግባር ልምምድ የተሻለ ልምድና ዕውቀት እንደሚያገኙ በመግለጽ፣ ይህም ተግባራዊ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል፡፡
ሁዋዌ ዘርፉን በእውቀትና ልምድ ወደፊት የሚያራምዱ ተተኪዎችን ለማፈራት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አክለዋል፡፡
ተማሪዎቹ በውድድሩ በመሳተፋቸው የተለያዩ ልምዶችን ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ በተለይ የቴክኖሎጂ ማዕከል የሆነውንና በቻይና የሚገኘውን የሁዋዌ ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘታቸው የተለየ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል።
ለዓለም አቀፉ ውድድር ቻይና ከሄዱት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ስመኘው አደመ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ሞሆኑን ገልጾ፣ ሁዋዌ ኢትዮጵያ በሰጠው ዕድል ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ካጠናቀቁ ተማሪዎች መካከል እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር 2022 እስከ 2023 በኅዳር 2015 ዓ.ም. ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተጀመረ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ1,500 በላይ ተማሪዎች በኦንላይን ቅድመ ፈተና ወስደዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል 63ቱ ተማሪዎች በአዲስ አበባ በታኅሣሥ 2015 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ የአይሲቲ ውድድር የተሳተፉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 18 ተማሪዎች ወደ ሪጅናል ውድድር በማለፍ በአፍሪካ አኅጉራዊ ውድድር ተሳትፈዋል።
ከእነዚሁ ተማሪዎች መካከልም ዘጠኙ ከግንቦት 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በቻይና ሼንዘን ከተማ በተካሄደው 7ኛው የሁዋዌ ዓለምአቀፍ ውድድርም በመሳተፍ ሦስተኛውን ሽልማት አሸንፈዋል። በዛሬው ዕለት ዕውቅና ያገኙትም እነዚሁ ተማሪዎች ናቸው።
የሁዋዌ አይሲቲ ወድድር ጥራት ያለው የአይሲቲ ታለንት ዕድገትን ለማፋጠን፣ ለኢንዱስትሪው ብቁ ተሰጥኦዎችን ለማዘጋጅትና መምረጥ፣ የመስኩ ባለተሰጥኦዎችን ወደፊት ለማቅረብና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ንቁ ተሳታፊዎችን ለማበርከት፣ የመስኩ ፍላጎትና አቅርቦት በቂ እንዲሆን ለማበረታታትና በዘላቂነት አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡