ለአንድ ወር የሚቆይ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ከትናንት ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መጨመሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ አንፃራዊ መረጋጋት እንደታየበት ገልጿል። በዚህም ላለፉት አራት ወራት በችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ለውጥ ሳይደረግ መቆየቱን አስታውሷል።
ሆኖም ግን የዓለም ነዳጅ ዋጋ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ እያሳየ በመምጣቱ ዋጋውን ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉን ገልጿል፡፡ በመሆኑም ቤንዚን በሊትር 74.85 ብር፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 76.34 ብር፣ ኬሮሲን በሊትር 76.34 ብር፣ የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 68.58 ብር፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 62.22 ብር፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 61.07 ብር መሆኑን አስታውቋል፡፡