የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች የሰሊጥ ዘር ባለማግኘታቸው፣ ለሰሊጥ የሚሆን መሬት ሳይታረስ የእርሻ ወቅት እያለፈባቸው መሆኑን ተናገሩ፡፡
የትግራይ አርሶ አደሮችና አምራች ባለሀብቶች የሚገኙበት የትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የዘርፍ ማኅበራት ተወካዮች፣ አርሶ አደሮቹ የገጠሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
ዘንድሮ መዘራት የነበረበት የሰሊጥ ዘር አቅርቦትና ትራክተር ከእነ ማረሻቸው ባለመኖሩ፣ እንዲሁም አንዳንድ የሰሊጥ እርሻ የሚከናወንባቸው ቦታዎች በወረራ በመያዛቸው አርሶ አደሮቹ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተካሄደው የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የትግራይ ክልል የንግዱ ማኅበረሰብና አርሶ አደሮች የደረሰውን ጉዳት መልሶ እንዲያገግም መጠየቃቸውን፣ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርኸ አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ይመረት የነበረው ከፍተኛ የሰሊጥ እርሻ ልማት ላለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠ መሆኑን፣ ዘንድሮ ደግሞ የመልሶ ማቋቋም ሒደቱ በመዘግየቱና በግብርና ሚኒስቴር የሚቀርቡ ድጋፎች በወቅቱ ባለመድረሳቸው የእርሻ ጊዜው እያለፈ ነው ሲሉ አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡
ትግራይ ውስጥ ያሉ የእርሻ ቦታዎች በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በአነስተኛ መጠን ጉዳት የደረሰባቸው ስለሆነ አብዛኞቹ ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት የላቸውም ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚካሄደው ኢንቨስትመንት ከ500 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት አቶ ደስታ፣ የሰሊጥ ምርት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ መሆኑ ስለሚታወቅ፣ በግብርና ሚኒስቴርም ሆነ በሚመለከታቸው ተቋማት መፍትሔ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጋዘን የነበረ ከፍተኛ የሰሊጥ ክምችትና ለመበስበስ የደረሰ ብዛት ያለው የሰሊጥ ሰብል የተዘረፈባቸው ባለሀብቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ከክልሉ የግብርና ቢሮ ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጾ፣ ዘር ማቅረብና ሌሎች ተግባራት በማከናወን ሒደት ላይ መሆኑን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሰሊጥ ምርትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ፣ አርሶ አደሮቹ በክልሉ የተፈጠረውን ችግር በመገንዘብ በእጃቸው የሚገኘውን ማንኛውንም ዘር በመዝራት የክረምቱን ወቅት መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት የሰሊጥ ምርት ማቅረብ አለመቻላቸውን የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ የሚቀጥለው የምርት ዘመን ሲደርስ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውስጥ ያላቸው የግብይት ወንበር ስለመኖሩ ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሰሊጥ ምርት ካለ አርሶ አደሩ በሚቀርበው የምርት ገበያ ቅርንጫፍ በመገኘት ለማገበያየት ዝግጁ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ዳንሻ አካባቢ ያለው ቅርንጫፍ በጦርነቱ ምክንያት መጋዘን፣ የምድር ሚዛን፣ እንዲሁም የላቦራቶሪ አገልግሎት በድጋሚ ሥራ እንዲጀምር ብቻ በማድረግ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል፡፡
በምርት ገበያው የሚገኘውን ወንበር በተመለከተ አርሶ አደሮቹ ሳይገበያዩ በመቆታቸው ወንበራቸው አይወሰድም ያሉት አቶ ወንድማገኝ፣ በሚቀጥሉት ጊዜያት ወንበር ባይኖራቸውም አዲስ የበይነ መረብ አገልግሎት በመዘርጋቱ ምንም ሥጋት አይኖርም ብለዋል፡፡