Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሰመኮ በቀድሞው ደቡብ ክልል በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ተፈጽመዋል ያላቸውን አጠቃላይ የሕግ ጥሰቶች...

ኢሰመኮ በቀድሞው ደቡብ ክልል በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ተፈጽመዋል ያላቸውን አጠቃላይ የሕግ ጥሰቶች ይፋ አደረገ

ቀን:

  • የኮሚሽኑ ሠራተኞች ከፍተኛ እንግልት እንደደረሰባቸው ገልጿል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቀድሞው ደቡብ ክልል ጥር 29 ቀን 2015 እና ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ፣ ሰፋ ያሉ የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመላክት ሪፖርት ይፋ አደረገ፡፡

ኮሚሽኑ ከሁለት ቀናት በፊት ይፋ ባደረገው ባለ 50 ገጽ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት፣ ሕዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከሚገኙ 3,776 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከ200 በላይ ጣቢያዎች ናሙና በመውሰድ ክትትል ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞና ወላይታ ዞኖችችና አሌ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂና ደራሼ የተሰኙ ልዩ ወረዳዎች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልነት እንደ አዲስ እንዲደራጁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡

በዚህም ውሳኔ አዲሱ የክልል ምክር ቤት ከነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥልጣን ተረክቦ፣ የክልሉን የተቋማት ማዕከላት መቀመጫ በስድስት ከተሞች እንዲሆን ውሳኔ ያሰተላለፈ ሲሆን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንትና የመንግሥት ኃላፊዎችን ሹመት ማፅደቁ አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ ኢሰመኮ ይፋ ባደረገው የመብቶችና የሕግ ጥሰቶች ክትትል ሪፖርት፣ በሁለቱም ዙር በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በተለያዩ አካላት ማስፈራራት፣ ድብደባና እስር የመሳሰሉ ልዩ ልዩ የሕግና የመብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል፡፡

የምርጫ ካርዳቸውን በቀበሌ አመራር እንምረጥላችሁ ተብለው ጥያቄ የቀረበላቸው ነዋሪዎች፣ የቀበሌ አመራሩ ድርጊት ሕገወጥ ነው በማለት ስለተቃወሙ ብቻ፣ ከድምፅ መስጫው ዕለት ጀምሮ ጋሌ ቀበሌ ታስረው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ በድኅረ ሕዝበ ውሳኔ ወቅት ጥቆማ ደርሶኛል ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ በተጨማሪም ሦስት ግለሰቦች ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለምን ጎጆ መረጣችሁ በሚል ምክንያት በቁጫ ወረዳ ገራራ ቀበሌ አመራሮች 5,000 ብር ቅጣት እንዲከፍሉ፣ ካልከፈሉ ደግሞ ታስረው እንዲቆዩ በመደረጋቸው፣ የሚከፍሉትን አጥተው በእስር ላይ እንደሚገኙ ለኮሚሽኑ ጥቆማ የደረሰው ቢሆንም ይህንን ሁኔታ ለማጣራት አልቻልኩም ብሏል፡፡

በሁሉም ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች ከሕዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ፣ የአካባቢ የመንግሥትና የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በምርጫ አሠራር ላይ ጣልቃ ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበርም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ ለአብነትም  የመራጭነት ካርድ አመራሮች በመውሰድ ለመራጮች ቤት ለቤት እየዞሩ ለማደል ለምርጫ አስፈጻሚዎች ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ለኮሚሽኑ መናገራቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በቡልቂና ሳውላ ከተማ አስተዳደሮች ነዋሪዎች በአካል ምርጫ ጣቢያ ድረስ በመሄድ የመራጭነት ካርድ መውሰድ ሲገባቸው፣ በአመራር አካላት በኩል የምርጫ ካርድ እስከ መኖሪያ ቤት ድረስ ሲወሰድላቸው እንደነበር በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የኮሚሽኑ ክትትል ቡድን አባላት ሥራቸውን አጠናቀው እየወጡ በነበረበት ወቅት አራት የሚሊሻ አባላት የነበሩበትን መኪና በመክበብና መንገድ በመዝጋት፣ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳታደርጉ በማለት የክትትል ቡድኑ ወደ ቀበሌው እንዲመለስ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ፣ የወረዳው ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ እንዲሁም የወረዳው ዓቃቤ ሕግ በተመሳሳይ በኮሚሽኑና በኮሚሽኑ የክትትል ቡድን ላይ ስድብ፣ ትችትና የማሸማቀቅ ድርጊት መፈጸማቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

የመንግሥት አካላት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በመሰብሰብ ኢሰመኮም ሆነ ባለሙያዎቹ ሕገወጥ ስለሆኑ ዕርምጃ ይወሰድባቸው ከማለታቸውም በላይ፣ የኮሚሽኑን የክትትል ቡድን አባላት ጥፋታችሁን እመኑ በማለት ማስገደዳቸውም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ በኮሚሽኑ ባለሙያዎች ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጉዳት ወይም ጥቃት ኃላፊነት አልወስድም ማለታቸውን፣ ለክትትል ቡድኑ ተገቢውን ድጋፍ ባለማድረግና እንቅፋት በመሆን ተግባርና ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ መቅረታቸውም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የኮሚሽኑን የክትትል ቡድን አባላትን አግደው ለማቆየት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው የስልክ ልውውጥ ጉዳዩ ዕልባት ሊያገኝና ቡድኑም ከሥፍራው ሊወጣ መቻሉን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...