በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ቀበሌዎች፣ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና መረጃን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚረዱ 18 ሺሕ የኢንተርኔት ኪዮስኮች ሊገነባ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ የግብርና ቴክኖሎጂንና የግብዓት አቅርቦትን የሚያመላክቱ ወቅታዊ የግብርና መረጃዎችን በቀላሉ አርሶ አደሮች ጋር ለማገናኘት የሚረዳ የዲጂታል መረብ ግንባታ ከሚያካሂድለት ግሪን አግሮ ሶሎሹን፣ ወይም ለእርሻ ከተባለ አገር በቀል ኩባንያ ጋር ማክሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ስምምነት ፈጽሟል፡፡
ስምምነቱ የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተፈርሟል፡፡ የተፈጸመው ዘመናዊ የግብርና መረጃዎችን በኢንተርኔት አማካይነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ለማቅረብ የሚያስችል የመረጃ ሥርዓት ግንባታ ስምምነት ሲሆን ፕሮግራሙ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይና የሶማሌ ክልሎች በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ይህንን ስምምነት ዕውን ለማድረግ አርሶ አደሮች የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል፡፡ በዚህም በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን በ18 ሺሕ ቀበሌዎች በሚገኙ የግብርና ኪዮስኮች የኢንተርኔት አገልግሎት ይዘረጋል ብለዋል፡፡
የኢንተርኔት መሣሪያዎቹ ተገዝተው መዘጋጀታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ዕቃዎቹን ከኢንተርኔት ኮኔክቲቪቲ ጋር ለማገናኘት በተለይም የቴሌኮም አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ኢንተርኔት ለማስጀመር ከቴሌኮም ተቋማት ጋር ስምምነት ይደረጋል ብለዋል፡፡
በሚከፈቱት የኢንተርኔት አገልግሎት ማቅረቢያ ኪዮስኮች አማካይነት አርሶ አደሮች የግብርና መረጃዎችን በነፃ እንደሚያገኙ፣ እነዚህን የኢንተርኔት ማዕከላት መጠቀም የማይፈልጉ ደግሞ በግል ስልካቸው መረጃውን ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ባደረጉት ስምምነት መሠረት በአነስተኛ መሬት ላይ የግብርና ሥራ ለሚያከናውኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች፣ የግል የዲጂታል ማኅደር በመፍጠር ወቅቱን የጠበቀ የግብርና መረጃ በየጊዜው እንዲደርሳቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡
በዲጂታል መረብ አማካይነት የሚቀርቡት መረጃዎች በአመዛኙ ወቅቱን የጠበቀ የአየር ሁኔታ ትንበያ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የምርጥ ዘር አጠቃቀምና አጠቃላይ ግብርናን የተመለከቱ መረጃዎች ሲሆኑ፣ መረጃውን አርሶ አደሮች ለማድረስና ሥልጠና ለመስጠት ‹‹ለእርሻ›› የተሰኘው ኩባንያ ከ55 ሺሕ በላይ ወጣቶችን አሠልጥኖ እንደሚያሰማራ ተገልጿል፡፡
በአመዛኙ የመንግሥት ተሳትፎ በበዛበት የግብርና ዘርፍ ለአርሶ አደሩ ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መንገድ የተሻለ የዲጂታል የመረጃ አቅርቦትን በቀላሉ ለማድረስ የሚረዳ የመፍትሔ አማራጭ መሆኑን፣ ለእርሻ የተሰኘው ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም እንድርያስ ተናግረዋል፡፡
በተመረጡ 150 ወረዳዎች በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮግራም በአብዛኛው የብቅል ገብስ፣ አኩሪ አተር፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ አቮካዶ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት ምርቶችና በእንስሳት ዕርባታ የተሰማሩ አርብቶ አደሮች ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ አገልግሎቱን ከድርጅቱ ወደ ኢንስቲትዩቱ ሙሉ በሙሉ የሚተላለፍበት መንገድ ይፈጠራል ብለዋል፡፡
በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካይነት ይተገበራል የተባለው ይህ ስምምነት በግብርና ሙያ ተመርቀው ሥራ ያልነበራቸውን ወጣቶች የሞባይል አፕሊኬሽን በመጠቀም በተጠቀሱት አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮችን የመመዝገብ፣ የአርሶ አደሩን ፍላጎት የማሰባሰብና ከአገልግሎት አቅራቢዎች ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚያከናውኑ አቶ አብርሃም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ የሚያስተዳድረው የመሬት ይዞታ ከአንድ ሔክታር በታች መሆኑን የገለጹት አቶ አብርሃም፣ ለዚህ መሬት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን መረጃ ለማግኘት በቀን እስከ ስምንት ሰዓት በመጓዝ አርሶ አደሮች እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ክፍያ እንሚጠብቃቸው፣ በዚህ ስምምነት ግን አርሶ አደሮች በአጠቃላይ ከአምስት እስከ ስምንት በመቶ የሚደርስ የኮሚሽን ክፍያ ብቻ በመክፈል አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው ያገኛሉ ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮች ዘወትር እንደሚያደርጉት ወደ ገበያ ሳይሄዱ፣ እንዲሁም የእርሻ ባለሙያዎች አገልግሎቱን በየአካባቢው ተደራሽ የሚያደርጉበት አሠራር እንደሆነ ተገልጿል፡፡