Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተጨማሪ ንጥረ ምግቦች ለማን?

ተጨማሪ ንጥረ ምግቦች ለማን?

ቀን:

በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችንና ቫይታሚኖችን የያዙ በእንክብልና በዱቄት መልክ የተዘጋጁ ተጨማሪ ምግቦችን (ሰፕለመንት) በመዋቢያ መሸጫ ሱቆችና በፋርማሲዎች ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪ በተለይም በአውሮፓና አሜሪካ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሰፕለመንቶች፣ እዚያ በሚኖሩ ቤተሰብ አማካይነት ወደዚህ አገር በተደጋጋሚ የሚመጡ ስለመሆኑ፣ በሰፊ ጥናት የተደገፈ ጥልቅ መረጃ ባይኖርም፣ ነዋሪዎች በየቤታቸው ቫይታሚኖችና ሚኒራሎች የያዙ እንክብሎችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል፡፡

በመደብሮች ለሽያጭ ከሚቀርበው በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ያለ ጊዜያቸው የተወለዱት ሕፃናትን ጨምሮ ከጨቅላ ሕፃናት እስከ አዛውንት መወሰድ ይችላሉ ተብለው የተለጠፈባቸው ተጨማሪ ምግቦችን፣ ለታመሙና የሚኒራልና ቫይታሚን ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ ማነሱ በሕክምና ሲረጋገጥ የሚሰጡትንም ጭምር ማየቱ የተለመደ ሆኗል፡፡

አንዱ የሞከረው ለሌላው ጥሩ ነው ብሎ በማጋራት፣ ተመርምሮና በሰውነት ውስጥ ያለው ችግር ሳይታወቅ በራስ፣ በጓደኛ ወይም በቤተሰብ ምክር ወይም ግፊት የሚጠቀሙም ብዙ ናቸው፡፡

ስሟ እንዳይጠቀስ የነገረችን እናት ልጇን በክረምት በመውለዷና ፀሐይ አታገኝም ብላ በማሰቧ፣ ከአሜሪካ የቫይታሚን ዲ ሰፕለመንት አስመጥታ እንደነበር፣ ሳፕለመንቱን ለመስጠት ሐኪም ከማማከር ይልቅ ከዩቲዩብና ከተለያዩ ድረ ገጾች ስታነብ መቆየቷን፣ ባለቤቷም ከጭንቀቱ የተነሳ ለሕፃኗ እንዲሰጣት ወስኖ እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡

ሊጠይቋት የመጡትንና ልምድ ያላቸውን ሁሉ ስታማክር እንደነበር፣ ኋላ ላይ ሐኪም ሳላማክር አልሰጥም ብላ እንደተወችውና ፀሐይ ብቅ ባለ ቁጥር ልጇን ለማሞቅ ይዛ ትወጣ እንደነበር ተናግራለች፡፡

በእርግዝናዋ ወቅት ቤተሰቧ የተለያዩ ቫይታሚኖችና ሰፕለመንቶች ይልኩላት እንደነበር፣ ነገር ግን ሐኪሟ ካዘዘላት ውጪ እንዳልተጠቀመች አክላለች፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞችና በድንበር መውጫና መግቢያዎች የሚታዩ መድኃኒትነት ያላቸው ንጥረ ነገሮችና ተጨማሪ ‹‹ምግቦች ለማንና መቼ፣ በምን ያህል መጠን መውሰድ ይገባቸዋል?›› የሚለው ከግምት ሳይገባ ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑም በጤናው ዘርፍ ብቅ እያለ የሚገኝ ተግዳሮት ነው፡፡

ከሰሞኑ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በሚኒስቴሩ ድረ ገጽ እንደገለጹት፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናትን ለማከም የሚውሉ አልሚ ምግቦችን ለምሳሌ ያክል (ፕለምፒነት፣ ኢሹር፣ ሱፐር – ሴሪያል – ፕላስ፣ F-100፣ F-75 የመሳሰሉት) ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ክልል ያሉት ሕፃናት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጁ አልሚ ምግቦች ቢሆኑም፣ እነኚህን በመሠረታዊነት የማያስፈልጋቸው ወይም ያልታዘዘላቸው ዜጎች እየተጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሕፃናት ላይ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮች ለመከላከልና አስፈላጊውን ሕክምና ለመስጠት በሥራ ላይ ከሚውሉ ንጥረ ምግቦች መካከል የተጠቀሱት ዋንኞቹ ሲሆኑ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ እየተስተዋለ ያለው የዘፈቀደ አጠቃቀምና በገበያ ላይ መዋል፣ ግብዓቶቹ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እንዳይደርስ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አክለዋል፡፡

ፉድ ፋክትስ ፎር ሔልዚ ቾይስስ በድረ ገጹ እንዳሠፈረው፣ ተጨማሪ ምግቦች ወይም ሰፕለመንቶች መወሰድ ያለባቸው ንጥረ ነገሮቹ በበቂ ሁኔታ ሳይወሰዱ ሲቀሩ ብቻ ነው፡፡  

ተጨማሪ ምግቦች ማለትም ቫይታሚኖች፣ ሚኒራሎች፣ አሚኖ አሲድ፣ ፋቲ አሲድና ሌሎችንም የያዙት በፒልስ፣ በታብሌት፣ በካፕሱል፣ በፈሳሽና በፓውደር መልክ የሚቀርቡ ሲሆን፣ የተለያየ መጠንና ውህድም አላቸው፡፡

እንደ ፉድ ፋክትስ ፎር ሔልዚ ቾይስስ ገለጻ፣ የሰውነት ክፍል የሚፈልገው ደግሞ ጥቂቱን ንጥረ ነገር ነው፡፡ የዘወትር የአመጋገብ ሥርዓትን የሚተካም አይደለም፡፡

ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በፈቃዳቸው የሚጠቀሟቸው ተጨማሪ ምግቦች እንዲሁ እንደተፈለገ የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም የቫይታሚኖች፣ የሚኒራሎችና የሌሎች ሰፕለመንቶች አወሳሰድን በተመለከተ መመርያ አለው፡፡

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ ምግብ ተመራማሪ አቶ ክፍሌ ሃብቴ እንደሚሉት፣ እንደ ፕለምፒነት፣ ኢንሹር፣ ሱፐር-ሴሪያል-ፕላስ፣ /ፎርሙላ 100/ Formula 100 (F-100) Formula 75 (F-75) የመሳሰሉት ንጥረ ምግቦች የሚሰጡት፣ ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ክልል ላሉ ሕፃናት ሆኖ ከፍተኛ የምግብ እጥረት (Severe Acute Malnutrition (SAM)፣ Moderate Acute Malnutrition (MAM), በጣም አነስተኛ ክብደት (underweight), መሟሸሽ (wasted) ላለባቸው ሕፃናት ነው፡፡ ንጥረ ምግቦቹ የተዘጋጁትም የተጎዳው ሰውነታቸው በፍጥነት እንዲያገግም ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡

እንዲሁም እርጉዝና የሚያጠቡ እናቶች በተለያየ ጊዜ የንጥረ ምግብ እንክብሎች በሐኪም እንደ አስፈላጊነቱ ሊታዘዝላችው ይችላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ንጥረ ምግቦች፣ ቫታሚኖችና ሚኒራሎች የያዙት የንጥረ ምግብ መጠናቸው በማወቅናና በቀን ስንት መወሰድ እንዳለበት በመረዳት የሚወሰዱ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ክፍሌ፣ በሰውነት ላይ ያለው የንጥረ ነገር ጉድለትን አገናዝቦ ሲወሰዱ ደግሞ ጥቅማቸው የጎላ ይሆናል፡፡ ዕድሉ ሲገኝ አንስቶ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምግቦች አይደሉም፡፡

ባለሙያው እንደሚሉት፣ ከሚያስፈልገው በላይ የሚወሰድ ከሆነ የጎንዮሽ ጉዳትም ሊኖራቸው እንደሚችል የሚታወቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ቫይታሚን ዲ የሚወስደው የቪታሚኑ እጥረት ያለበት ሰው ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ዝም ብሎ በተደጋጋሚ መጠቀም በኩላሊትና በጉበት፣ ሌሎችም የውስጥ የሰውነት አካላት ላይ ተከማችቶ ከፍ ያለ የቪታሚን ዲ የሰውነት ክምችት (hypervitaminosis D) ወይም ቪታሚን ዲ ቶክሲሲቲ የሚያስከትል ይሆናል፡፡

የተረጋገጠ ሕመም በሰውነት ውስጥ ከሌለ፣ በእኛ አገር እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዕለት ዕለት ፀሐይ ከማግኘታችን፣ ከምንበላው ምግብና በተፈጥሮ በሰውነት የሚሠራው ቪታሚን ዲ አንፃር ለጤናችን በጣም በቂ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

ሌሎችም ከላይ የተጠቀሱት የንጥረ ምግብ ዓይነቶች እንዲሁ ለታለመለት ዓላማ ብቻ ወይም የታወቀ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እንዲወስዱ በመተው፣ ለጤነኛ ሰውነት ግን ዕለት ዕለት እቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ምግቦችን አመጣጥኖና አፈራርቆ መጠቀም ከበቂ በላይ እንደሆነና ይህንን ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ችግሮቹ በስፋት እየታዩ የሚቀጥሉ ከሆነና ተጨባጭ መረጃ ካለ ለሚዲያዎች፣ ለተቆጣጣሪ አካላትና ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...