Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እጅ መስጠት የለም!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ከረማችሁ ወዳጅ ወገኖቼ? ኧረ ዘንድሮ ኑሮ እንዴት ነው? አልቻልነውም እኮ፡፡ እስኪ አስቡት በዚህ የሰቀቀን ኑሮ ላይ ሌላ አሰቃቂ ነገር እየተጨመረበት አሳራችንን ስናይ። አንችለው የለም፣ ይኼው ይህንን መራር ኑሮንም ግጭቱንም ችለን ሰንብተን ተገናኝተናል። እንዲያው አብዛኛውን ሰው ወክዬ የጊዜውን አቅል የሚያስት ኑሮና አውዳሚ ግጭት ማንሳቴ እንጂ፣ እኔስ እውነት ለመናገር ዕድሜ ለማንጠግቦሽ ፍቅሩን ነው ያልቻልኩት። ሃ…ሃ…ሃ… ይብላኝ ፍቅርና አብሮነት መሀል ፖለቲካና ነገር እየቆሰቆሱ ለተኳረፉ። እንዲያው እናንተ፣ ምነው ሰው ግን እንዲህ የፍቅርና የአንድነት ጠላት ሆነሳ? ‹‹ፍቅርና አብሮነት የሚገኘው በመተሳሰብ ውስጥ እንጂ በመናናቅና በመጠላላት አይደለም…›› ብዬ ለአዛውንቱ ባሻዬ ብሶቴን ባሰማ፣ ‹‹ልፋ ቢልህ እንጂ የአሁን ዘመን ሰው መካሪ የሚያሻው ነው? አውቆ አጥፊ ሁሉ…›› ነበር መልሳቸው። እውነት ነው እኮ፣ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት መቼ ይሰማል? የመስማት ነገር ከተነሳማ መንግሥትስ መቼ ነው ሕዝብን የሚሰማው? ሕዝብስ የማይሰማውን መንግሥት እንዴት አድርጎ ነው የሚሰማው? አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር በመጨረሻው ዘመን ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሳል የተባለው እኮ ለቀልድ አይደለም፡፡ አንዱ ሌላውን በቅጡ ካልሰማው የሚከተለው መጠፋፋት እንደሆነ እኮ ነው መልዕክቱ የሚነግረን…›› የሚሉኝን ሳስታውስ እፈራለሁ፡፡ ወድጄ መሰላችሁ!

እንዳልኳችሁ ሰው በሚያገኘው ቀዳዳ ሁሉ ሥራው ጎራ መለየት ሆኗል። ለሌላው አለማሰብና ለራስና ለቡድን ብቻ መኖር ገኗል። በቀደም ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ የሚከራይ ቪላ ቤት ነበርና ተከራይ ለማግኘት ላይ ታች ስል ውዬ በመጨረሻ ተሳክቶልኝ ቤቱን የሚከራየው ሰው አገኘሁ። ሰውዬው ብቻውን ነው። ልጅም ሚስትም የለውም። ‹‹እንዴት ነው ቤተሰቦችህ በአገር የሉም?›› አልኩት ጎልማሳነቱንና መልከ መልካምነቱን መላልሼ እያየሁ። ‹‹የለም፣ ቤተሰብ ምን ይሠራል?›› ሲለኝ ክው አልኩላችሁ። ይህችን ይወዳል አንበርብር ምንተስኖት? ምነው ተዘጋጅ እንኳ ቢለኝ? እያልኩ፣ ‹‹እንዴ ምን ለማለት ነው?›› አልኩት በደረቀ ድምፅ። ‹‹በዚህ ጊዜ ቤተሰብ? ያምሃል እንዴ? ሚስት ከመፈለግ ነዳጅ ብፈልግ ይሳካልኛል እኮ…›› አይለኝ መሰላችሁ። ሰው አምርሯል ማለት እኮ ይኼ ነው። ቀላል አምርሯል? ወዲያው ከምሬቱ ጀርባ ምን እውነት ቢኖር ይሆን? ብዬ መመራመር ጀመርኩ። እንዲህ ዓይነት ሰው ጠፍቶ እኮ ነው ምሬታችን ገደቡን ያለፈው፡፡ መልሱን ታዲያ አንድ ወዳጄ ድሮና ዘንድሮ በሚለው ጨዋታው ውስጥ ያገኘሁት መስሎኝ፣ ከእሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ ያወጋኝን አሰላስል ጀመር። ትዝታ ማለት ነው!

ጨዋታን በጨዋታ አይደል ደንቡ? ድሮና ዘንድሮ በሚል የቤቱን ድባብ ወዳጄ ያጨወተኝ እንዲህ ብሎ ነበር። ‹‹ድሮ ትዳር ለመያዝ ገና ማቀድህ ሲሰማ ደግሶ ከመዳር አልፎ፣ በርታ እስከምትል ድረስ ቀለብ ሸመታ ሳይቀር ዘመድ ወዳጅ ያግዝሃል። ‘አይዞህ’ የሚልህ የሚጠይቅህ አገር ምድሩ ነው። አንተ አመል ይኑርህ እንጂ ሚስትህም ታዛዥ፣ ግንባርህን ዓይታ የምታስበው የሚገባት፣ ከመብቷ በፊት ትዳሯና ቤቷ የሚበልጥባት ነበረች…›› አለና ጥቂት ራሱን በአሉታ አወዛወዘ። ‹‹አሁንስ?›› እለዋለሁ ወሬው ግላዊ አመለካከትና አስተያየት የሰፈነበት እንደሆነ እየተገነዘብኩ፣ ‹‹አሁንማ ብቸኝነት ቢጠናብህ ከሰልህን ገዝተህ፣ በቆሎህን እየጠበስክ ቲቪህን ስታይ ታድራታለህ እንጂ ከሌለህ ማን ሊጠጋህ? ቲቪ ከሌለህ ደግሞ ዩቲዩብ አለልህ የተጋነኑና የለዘዙ ዜናዎችንና ትንተናዎችን ሲያራግፍብህ ያድራል። እዚህ ላይ ብናበቃስ…›› አለኝ እጁን ወደ ላይ እየዘረጋ። እኔም፣ ‹‹አይ አንተ፣ የእኛንስ የፀባይ ለውጥ መቼ አየኸውና?›› ብዬ ክፉ ሳልናገር ተሳስቄ ዝም። ሰው አመለካከቱንና እምነቱን ሲነኩበት ተርብ ሆኗላ ጎበዝ፡፡ ያውም ተናዳፊ!

ታዲያ ቪላ ቤቱን የተከራየው ደንበኛዬም ይኼን አስተሳሰብ የደገመው ስለመሰለኝ ለማጣራት ደግሜ ብጠይቀው፣ ‹‹ወንድሜ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ሰው ራስ ተኮር ሆኗል። ዕድሜ ግራ ገብቷቸው ግራ ለሚያጋቡን ፖለቲከኞቻችን። ትዳር ለመመሥረት ፍቅር ሳይሆን ገንዘብና ንብረት አለው/አላት በሚባልበት በዚህ ዘመን፣ ቤተሰብ ሳይቀር ሠርተው ያገኛሉ ሳይሆን ምን አለው/አላት እያለ በሚደልልበት በዚህ ጊዜ፣ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ተሠርቶ ስለሚገኝ ሀብት ሳይሆን ተሰርቆ ስለሚከበርበት አቋራጭ በሚጨነቅበት ወቅት ምን አስጨነቀኝ…›› አለኝ። እንዳልክ ብዬ ኮሚሽኔን ተቀበልኩና ተሰናበትኩት።  መቼስ ዘመናችን ምን ያህል እንደ ከበደ ለመረዳት ነጋሪ አያሻንም። የጥቂቶች አዋዋልና አዳር ለብዙዎች መገለጫና ስም ሲሆን ግን ያሳዝናል። በጣም ያሳዝናል! 

እናላችሁ ሰሞኑን ነገር ሲጠናብኝ ወሬ እያስጠላኝ ቤቴ ተጠቅልዬ ከማንጠግቦሽ ጋር ሳወጋ፣ ከዚያም ከዚህም የለቃቀምኩትን የድሮ ወግ እያነሳሁ ሳጫውታት እውላለሁ (‘ሺሕ ዓመት አይኖር’ እያሉ ሥራ መፍታት ካለማመዱን እንግዲህ ምን ይደረግ?)፡፡ ድንገት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ሳላስበው ከአፌ ካመለጠ፣ ‹‹ኧረ አንተ ሰውዬ ተወኝ ስለፈጠረህ? ምንድነው እንደ አገራችን ፖለቲከኞች የሚምታታ ነገር መዘባረቅ? ቀጥ ያለ ነገር አውራ፡፡ ተምታቶ ማምታታት እንኳን ለአንተ ለገዥው ፓርቲና ለተፎካካሪ ተብዬዎችም አልጠቀመ፡፡ ፖለቲከኞቹ እንደሆነ ውኃ ቀጠነ እያሉ ነገር በመቆስቆስ እርስ በርስ ያበላሉናል እንጂ፣ እነሱ ከቶም ጭረት እንደማያገኛቸው ከዚያ የሰሜን ጦርነት ተምረናል፡፡ ችግሩ ምን መሰለህ እነሱ ነገ በፈረንጅ ገላጋይነት ሊታረቁ እኛን ጃስ እያሉ ያፋጁናል፡፡ እኛም ህርም አናውቅ እነሱ በነዱን እየሄድን ሰለባ እንሆናለን…›› ስትለኝ፣ ውዴ ማንጠግቦሽ እኔ ሳላውቅ ከታዋቂ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ መቼ ነው የማስተርስ ዲግሪዋን የያዘችው ብዬ አሰላስል ጀመር። እውነቴን ነው እኮ። የትኛው ምሁር ነው እንዲህ ፖለቲካችንን እየፈተፈተ የሚያጎርሰን፡፡ በዚህ ጊዜ አይታሰብም!

‹‹በቀደመው ሥርዓት ‘ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም’ ከተባለ በኋላ የዘመኑ ተገዳዳሪ ፖለቲከኞች አገሪቱን በደም እያጠቡና ከዴሞክራሲ መርህ ጋር እየተጋጩ በርካታ ሺዎች በነጭና በቀይ ሽብር ታጨዱ። በእነሱ እግር የተተካው ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ ሲል ዴሞክራሲ አለ ብለን ያሻንን ስንናገር ፀረ ልማት፣ አክራሪና ጽንፈኛ ብሎ ፈርጆ ስንቱን ፈጀው፣ ስንቱን እያሰቃየ አሰረው፣ ስንቱን አሰደደው። በቃ ስሙ ተቀይሮ ‘ልማት’ ተባለ እንጂ አብዮት ውስጥ ነን ስንል ሐሳብን በነፃነት ስለመግለጽ፣ ስለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፣ ስለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሰበካው ቢበዛም ውጤቱ አፈና ነበር። ዛሬ ደግሞ ለውጥ ብለን ጀምረን አንድ ላይ ሆ ብለን ብንነሳም፣ ለውጡ የጎራ መደበላለቅና ብዥታ ውስጥ ገብቶ ወዳጅና ጠላት አድርጎን ምን እየሆንን እንደሆነ ታውቀዋለህ፣ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ስለዚህ አንተንም ተምታቶ የሚያምታታ ነገር አያጥቃህ የምልህ ለዚህ ነው…›› ስትለኝ እውነት ማንጠግቦሽ አልመስልህ ብላኝ ፈዝዤ አየኋት፡፡ ‹‹በይ እኔ እንደሰማሁሽ ሌላ ሰው እንዳይሰማሽ አደራ…›› ብያት ልወጣ ስል፣ ‹‹አንበርብር ልብ ብለህ ስማኝ፡፡ ከዘመኑ ሰው ውስጥ እኮ የማይረባ ስትለው ቁምነገረኛ፣ ባለጌ ስትለው ጨዋ፣ አፍራሽ ሲባል ገንቢ ሆኖ የሚገኝ ብዙ አለ። ስለዚህ ሁሉንም በአንድ ፈርጀህ አትፍራ…›› ብላ ስትጨምርልኝ ከጓዳ ሕይወቷና ሥራዋ ባሻገርም ምንም የምታውቀው የማትመስለኝ ውዷ ማንጠግቦሽ በሳል የፖለቲካ ተንታኝ ሆና አረፈች። ጉድ እኮ ነው!   

መቼም ሮጬ ሄጄ የማወራው ለእሱ ስለሆነ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ አግኝቼ የማንጠግቦሽን ወግ ብነግረው፣ ‹‹እውነቷን እኮ ነው!›› ብሎኝ የሚሉት ሌላ የሚሠሩት ሌላ ስለሆነባቸው የዘመኑ ምሁራኖቻችን በሰፊው ተጨዋወትን። በኋላም ‹‹ኔጋቲቭ›› እና ‹‹ፖዘቲቭ›› የሚሉ ቃላትን በስሙ ስላስቀየራቸው ንጉሥ የባሻዬ ልጅ የሚያስቅ ነገር አጫወተኝ፡፡ እኔም ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ›› እያልኩ ሰማሁት፡፡ ሆሊውድ አምባገነኖች ምን ያህል ራስ ወዳድና ህሊና ቢስ ገዥዎች እንዳሉ ለማሳየት ፈልጎ ከሠራው ፊልም ያየው መሆኑን ጠቅሶ የባሻዬ ልጅ ጨዋታውን ቀጥሏል (የእኛ አገር ፊልሞች እንደሆኑ ‘ካሳቁ ይበቃል’ የተባሉ ይመስል ጠንከር ያለ መልዕክት ሲያስተላልፉ ለማየት አልታደል ብለናል)፡፡ ‹‹የንጉሡ ስም አላዲን ይባላል። ሁሉም ነገር በእሱ ስም እንዲቀየር ከማዘዙ የተነሳ ‘ኔጌቲቭ’ እና ‘ፖዘቲቭ’ በስሙ ተዛውረዋል። ታዲያ የኤችአይቪ ምርመራ ውጤት ያደረገ ሰው ውጤቱ የሚነገረው ‘ኤችአይቪ አላዲን’ ወይም ‘ፖዘቲቭ አላዲን’ ተብሎ ነው። ይታይህ እንግዲህ…›› አለኝ ፈገግ ብሎ። ጨዋታችን በምድራችን ላይ የተነሱ አምባገነንና ጨካኝ መሪዎችን አስታወሰኝ። ከማናለብኝ ስሜታቸው የተነሳ የሰው መብት የደፈሩ ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ጎድፎ ተጽፎ ትውልድ ሲሳለቅባቸው የሚኖሩ በአዕምሮዬ ተዘረዘሩ። ብልህ መሪና መንግሥት ግን በታሪክ ተወቃሽ መሆንን ስለማይሻ ከልብ ለሕዝብ መሥራትና መቆርቆር መገለጫ ባህሪው ነው፡፡ የሚሰማ ካለ ለማለት ያህል ነው!   

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ቀኑ አልቆ ምሽት ሊቃረብ ሲል እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን አመራን። ግሮሰሪያችን ከወትሮ የተለየ ድባብ አይታይባትም። ሳቅ፣ ጨዋታና ብሽሽቁ እንደ ተለመደው አለ። እንደ ወትሮው ያልነበረው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፣ ድንገት ተለውጧል። ‹‹ምነው? ምን ሆነሃል?›› አልኩት ከፍቶት እያየሁት። ‹‹እ… እንዲያው ዝም ብዬ ነው እባክህ፣ ብቻዬን የምፈጥረው ነገር ያለ ይመስል…›› አለኝ። ‹‹በእርግጥ መፍጠር የፈጣሪ ተግባር ነው። ልዩነት ማምጣት ግን መቻሉን አትርሳ…›› አልኩት ትከሻውን ቸብ እያደረግኩ። አሁንም ዝምታው ቀጠለ። ‹‹ኤጭ ትነግረኝ እንደሆነ ንገረኝ። ለጨዋታ እንጂ የሚያስቆዝምማ መቼ ጠፋ?›› ስለው ደንገጥ ብሎ፣ ‹‹አንዳንዴ ለራሴም ጭምር ስለሚገርመኝ እኮ ነው…›› አለኝ በተጨነቀ ድምፅ። ‹‹ምኑ?›› ጠየቅኩት መልሼ። ‹‹የዚህች አገር እንቆቅልሽ ነዋ፡፡ ሌላ ምን አለብን አንበርብር?›› ብሎ መልሶ ጠየቀኝ። ‹‹ምነው የሰማኸው አዲስ ነገር አለ እንዴ?›› ስለው፣ ‹‹አዲስ ነገር ባንሰማስ ያልፈታነው ችግር ተጠራቅሞ አይደል እንዴ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ዕድሜያችንን እያገባደድን ያለነው?›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ዝም ብዬ ስታዘብ ወዴት ይሆን እየተጓዝን ያለነው ስል መሽቶ ይነጋል። ተመልከት እስኪ ኢትዮጵያ ከጦርነት ወጥታ ፊቷን ወደ ልማት አዙራ ልትመነደግ ነው ስንል ግጭት ይከሰታል፡፡ ስግብግብ ነጋዴ ከዚህም ከዚያም እያምታታ የአገሩን ሕዝብ እያስራበ ይዘርፋል፡፡ በሐሰተኛ ደረሰኝ አገር እየዘረፈ የሀብት ቁልል ላይ ሆኖ አገር በድህነት መቅኖ ታጣለች። በዚህ በኩል ሌብነቱ፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦቱን ታየዋለህ። ሁሉም ለራሱ ጎርሶ ለራሱ ሊድን ብቻ እየሮጠ የአገር ችግር የሚፈታ ጠፋ። እውነት ማን ነው ከራሱ አስቀድሞ የዚህችን አገር ጥቅም እያስቀደመ ያለው? እንጃ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ይመስለኛል…›› ብሎኝ ካስቀዳው ተጎነጨ። ነገሩ ያስጠጣል!

‹‹አንተስ ታዲያ ምን ይሁን ትላለህ?›› አለው ፊት ለፊታችን ተቀምጦ የምናወራውን ሲሰማ የነበረ ጎልማሳ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከአንገቱ ቀና ብሎ ድምፁን ጎርነን አድርጎ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› ብሎ ሲመልስ የግሮሰሪዋ ታዳሚዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ቀና ብለው አዩት። ጠያቂው ብርጭቆውን ወደ ላይ አንስቶ፣ ‹‹ከራስ ጥቅም በፊት ለአገር!›› አለው ፈገግ ብሎ። ድራማ የማይ እስኪመስለኝ ድረስ የምሰማውንም ሆነ የምመለከተውን ማመን አልቻልኩም። ሁሉም የሚጎነጨውን አንስቶ በአንድ ድምፅ መፈክር ያወርዳል፡፡ ከራስ ወዳድነት እስከ ጽንፈኝነት የመረረው ሁሉ ወደኋላው እያየ ነገን የናፈቀ ይመስላል፡፡ ራስ ወዳድነትና ቡድንተኝነት ፋሽን በሆነበት በዚህ ዘመን ጠያቂና መርማሪ ትውልድ ካልተፈጠረ ነገም ያስፈራል፡፡ ለዚህም ይመስላል ከራስ በፊት ለአገር የሚለው የግሮሰሪዋን ሰዎች ‹‹ቺርስ›› የሚያስብለው፡፡ ከራስ ወዳድነት እስከ ጽንፈኝነት ድረስ ያሉት በሽታዎች ይወገዱ ዘንድ ስንቴ ቺርስ እንደተባለ አላስታውስም፡፡ ነገር ግን የእኛ ሰው በአገሩ ላይ የሚያሴሩ ሰዎች ድርጊት የመረረው ይመስላል፡፡ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ፣ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ እጦት እየተንገሸገሸ፣ ነገ ደህና ሊሆን ይችላል ብሎ ሲመኝ ዛሬ እየተበላሸ፣ ሰላም ጠፍቶ ግጭት በየቦታው እየናኘ፣ በአጠቃላይ ከተስፋ ይልቅ ተስፋ መቁረጥ እያንዣበበ እየከፋው ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን እጅ መስጠት የለም! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት