ዕንቁጣጣሽ ወይም ዘመን መለወጫ በዓል እንደ ሌሎች የሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በሕዝቡ ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓልን ለመቀበል ሰዎች አቅማቸው በፈቀደው መጠን የቤታቸውን ቁሳቁስ የሚቀይሩበት እንዲሁም መንፈሳዊም ሆነ አዕምሯዊ ለውጥ ለማምጣት ቃል የሚገቡበት በዓል እንደሆነ ይታመናል፡፡
በዓሉም ሕፃናት ልጃገረዶች ‹‹አበባ አየሽ ወይ›› እያሉ የሚጨፍሩበት፣ የመልካም ምኞት መገለጫ የሆነውን የአበባ ሥዕልና ለምለም ቄጤማ የሚያበረክቱበት መሆኑ ከሌሎች በዓሎች ልዩ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በተለይ አዲስ ዘመን መምጫው ሲደርስ የአሸንዳ፣ የሻደይ፣ የሶለል፣ የአሸንድዬ፣ የቡሔና የእንግጫ ነቀላ ክንውኖች ለበዓሉ ልዩ ድባብ የሚያላብሱ ናቸው፡፡ በግ፣ ዶሮ፣ ቅቤና ሌሎች የበዓል ግብዓቶችን ለመፈጸም የሚሯሯጡ ሰዎች በዓሉን የበለጠ ያደምቁታል፡፡
እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መስከረም 1 ለሚከበረው ‹‹ዕንቁጣጣሽ›› ቀን የሚሆኑ አልባሳት፣ ምግብና መጠጦች ከወዲሁ ገዝቶ ለማስቀመጥ በርካቶች ልዩ ዝግጅት ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ለበዓሉ ልዩ ድባብ ከሚፈጥሩ ሁነቶች መካከልም ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ይገኙበታል፡፡
ሪፖርተርም የ2016 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ቅኝት አድርጓል፡፡
በኤግዚቢሽን ማዕከል ውስጥ ለበዓል የሚሆኑ ግብዓቶችን ለመሸጥ ከገቡት ከትንሽ እስከ ትልቅ ጣባዎችን፣ መሶቦችን፣ የክትፎ መመገቢያ ጅባና ጌጣጌጦችን የሚሸጡ ይገኙበታል፡፡ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ መጪው የዘመን መለወጫ በዓልን ለማክበር የሚሸምቱ ሰዎች እምብዛም ናቸው፡፡
‹‹አዲስ ዓመትን ከሌሎች በዓላት ለየት የሚያደርገው በርካታ ሰዎች የቤትም ሆነ የልጆችን አልባሳት ለመግዛት ከታች ላይ ጎርደድ ሲሉ ማየቱ ነው ያለው ይህ ወጣት እንቅስቃሴው እምብዛም እንዳልሆነ ይናገራል፡፡
ከዘመን መለወጫ ቀጥሎ የመስቀል በዓል በመሆኑ፣ የክትፎ መመገቢያና ማዘጋጃ ጣባዎችን ለመሸጥ ገበያ መወጣቱንም ይናገራል፡፡
የመመገቢያ ቁሳቁሶቹ በባህላዊ መንገድ የተሠሩ እንደመሆናቸው ዋጋቸውም ከፍ ያለ መሆኑን ገልጾ፣ ለክትፎ ማቅረቢያና መሥሪያ የሚሆኑ ጣባዎች ከ25 እስከ 1,000 ብር እየተሸጠ ነው ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች በጋራ ሆነው የሚበሉበት ጅባ ከ5,500 እስከ 8,000 ብር ድረስ እየተሸጠ ሲሆን፣ የእንጀራ ማስቀመጫ መሶብ ከ2,500 እስከ 6,000 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡
የእንጀራ ማውጫ ሰፌድ ከ150 እስከ 200 ብር እየተሸጠና የቡና ቁርስ ማቅረቢያዎችም በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆኑን ይናገራል፡፡
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ አብዛኛው ሰው እየገዛ አለመሆኑንና የኑሮ ውድነቱም ሰው ላይ ጫና ማሳደሩን ያብራራል፡፡ ከዚህ በፊት የተለያዩ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ መሳተፉን የሚናገረው ወጣቱ፣ የዘንድሮ ዘመን መለወጫ ግን እንደሌሎች ባዛሮች ብዙም የደመቀ አይደለም ይላል፡፡
ኤግዚቢሽኑ ገና መከፈቱ በመሆኑ ሞቅ ሞቅ ለማለት ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም፣ የሰዎች የመግዛት ፍላጎት መቀነስንና አቅም ማነስን መታዘቡን ገልጿል፡፡ በተመሳሳይም የፕላስቲክ ጆግ፣ ማስታጠቢያ፣ የምሳ ዕቃ፣ ደብተርና ሌሎች ቁሳቁሶችን የያዘው ወጣት እስክንድር አበራ እንደገለጸው፣ ሸማቾች የ2016 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓልን በአዲስ ነገር ተቀብለው እንዲያከብሩ የተለያዩ ግብዓቶችን ይዘው ቀርበዋል፡፡
የተለያዩ የፕላስቲክ ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን የሚናገረው ወጣቱ፣ ለተለያየ ነገር የሚያገለግሉ ጆጎችን ከ250 ብር ጀምሮ እየሸጠ መሆኑንና የውኃ መያዣ ኮዳ ደርዘኑን በ150 ብር ሒሳብ እየተሸጠ ሲሆን የተለያዩ ሰርቪሶችን 150 ብር እየተሸጠ ነው ይላል፡፡
ከዚህ በፊት የተለያዩ ባዛሮች ላይ መሳተፋቸውን፣ ይህም አምስተኛ ኤግዚቢሽንና ባዛራቸው እንደሆነ የተናገረው ወጣቱ፣ የአሁኑ የተሻለ መሆኑን ለሪፖርተር ይናገራል፡፡
በዘንድሮም የኤግዚበሽንና ባዛር በርካታ ሰዎች እየመጡ እየተገበያዩ መሆኑንና ባዛሩ እስኪያልቅ ድረስ የሰው ተሳትፎ እንዲህ ከሆነ የበዓሉን ድምቀት የተሻለ ያደርገዋል ብሏል፡፡
አልባሳት ይዞ የቀረበው አቶ ደጀኔ ይንሳ እንዳስረዳው፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የገበያ ሁኔታ ቀዝቀዝ ያለ ነው፡፡
የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት የተለያዩ የሴት፣ የሕፃናት ልጆች እንዲሁም የወንዶች አልባሳት ይዞ መቅረቡን የሚናገረው አቶ ደረጄ፣ በኑሮ ውድነት የተነሳ ገበያው ቀዝቀዝ ያለ መሆኑን ያስረዳል፡፡
አብዛኛው ሸማች አልባሳቱን ከመግዛት ይልቅ ለምግብነት የሚውሉ ነገሮች ላይ ማዘውተር መጀመሩን ጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የልጆች ልብስ ከ600 እስከ 800 ብር እየሸጠ ሲሆን፣ የአዋቂ ሴቶች ደግሞ ከ1,300 ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከአሥር ዓመት በላይ በኤግዚቢሽን ባዛሮች ላይ መሳተፉን የተናገረው አቶ ደጀኔ፣ ወላጆች የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የልጆች የትምህርት ቤት ወጪ እንዲሁም የአስቤዛና የበዓል ወጪ ስላለባቸው ብዙም ላይገበያዩ ይችላሉ ብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ብዙኃኑን የማኅበረሰብ ክፍል አቅም እየፈተነ መሆኑን የገለጸው አቶ ደጀኔ፣ ይህ ማኅበረሰቡ እንዲህ ዓይነት ቦታዎች ውስጥ ከፍሎ ገብቶ ከመገበያየት ያግደዋል ሲል ያስረዳል፡፡
የሴንቸሪ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከዚህ በፊት በነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ለረዥም ጊዜ ያህል ኤግዚቢሽን ሳያዘጋጅ ቀርቷል፡፡
የ2016 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀውና እስከ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ የሚቆየው ኤግዚቢሽንና ባዛር ከ500 በላይ ነጋዴዎች መሳተፋቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የጨርቃ ጨርቅና የምግብ ኢንዱስትሪዎች በተዋዋሉት መሠረት እየሸጡ መሆኑን ክትትል እያደረጉ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ነጋዴዎች ከውጪው ገበያ ዝቅ አድርገው በመሸጥ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸው፣ የበርካታ ማኅበረሰብ ሥጋት የዋጋ ሁኔታ እንደሆነ አክለዋል፡፡
ተመዝግበው ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከሉ ያልገቡ ነጋዴዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ዘውገ፣ የገቡት የኤግዚቢሽንና ባዛር ሥራ ውድድር ስለሚጠይቅ ጥራት ያለው ዕቃ ይዘው መጥተዋል ብለዋል፡፡