Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሥራ አጥነት የፈተናቸው

ሥራ አጥነት የፈተናቸው

ቀን:

ወጣትነት ለሥራ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት ዕድሜ እንደመሆኑ፣ የአንዲት አገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት በየዘመኑ ባለው ወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተሞች የሚፈልሱ፣ እንዲሁም ከመጀመርያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በተለያያ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ፣ ከተሞች የሥራ አጥ ወጣቶች መናኸሪያዎች ሆነዋል።

 ከተሞችን ያጨናነቁ፣ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮባቸዋል። በአገራቸው ሥራ አግኝተው የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች፣ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ስደትና በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ላይ በስፋት ሲሳተፉ ይስተዋላሉ፡፡

ችግሩን ለመፍታት የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ እየሠራን ነው የሚለው ንግግር አይጠፋም፡፡ ይሁን እንጂ የሚሠሩ ሥራዎች የወጣቱን ጥም ማርካት አልቻሉም የሚሉ ትችቶች ይቀርባሉ። 

በየዓመቱ በእጅጉ እየጨመረ ለሚመጣው ለዚህ አምራች ኃይል ተመጣጣኝ የሆነ በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አልተቻለም።

በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመንግሥት ራስ ምታት የሆነው የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍም ዘርፈ ብዙና መጠነ ሰፊ የሆኑ አማራጮችን መዘርጋትና መጠቀም ለችግሩ እንደ መፍትሔ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ 

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተያዘውን ዓመት የዕቅድ የአፈጻጸም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት፣ ለ2.6 ሚሊዮን ሥራ አጥ ወገኖች የሥራ ዕድልን ለመፍጠር አስቦ፣ ለሁለት ሚሊዮኑ የሥራ ዕድል መፍጠሩን መናገሩ ይታወሳል። በአንፃሩ በወቅቱ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሥራ አጥ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር።

 በሌላ በኩል ደግሞ እንኳን አዳዲስ ሠራተኛ ለመቅጠር ቀርቶ በየሲቨል ሰርቪሱ ያሉትን ሠራተኞች  ጭምር የመዋቅር ማስተካከያ  በማድረግ ላይ መሆኑን  የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

 በዋናነት በአገር ውስጥ ከሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች በተጨማሪ ሥራ ፈላጊዎችን ወደ ውጭ አገሮች መላክ ለጊዜውም ቢሆን ችግሩን የሚያቃልል ከመሆኑም በላይ፣ የአገርንም ኢኮኖሚ እንደሚደግፍ ይነገራል፡፡ ለዚህም ከአምስት መቶ ሺሕ በላይ ዜጎችን  ወደ ተለያዩ አገሮች ለመላክ ታቅዶ  60 ሺሕ  መሄዳቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

   ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ ወጣቶች በሥራ ፍለጋ ሲንከራተቱ ይስተዋላሉ፡፡ ለችግሩ ተጋላጭ ከሆኑት መካከል ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በየዓመቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተመርቀው ይወጣሉ፡፡ ከምርቃት በኋላ የሚገጥማችው ፈተና ከባድ እንደሆነም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ።

 በተመረቁበት ሙያም ሆነ ማንኛውንም ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችል ሥራን አግኝተው ለመሥራት ተቸግረው አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ መቀበል እንዳላቆሙ የሚናገሩ ወጣቶች አሉ፡፡ በየጎዳናው ባሉ የሥራ ማስታወቂያ ሠሌዳዎች ከመመልከት ያልቦዘኑም በርካቶች ናቸው፡፡

መሰንበቻውን ሪፖርተር ቲዩብ በመዲናዋ በመዘዋወር ከሥራ ፈላጊ ወጣቶች ጋር በነበረው ቆይታ ወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር ከልክ በላይ እንደሆነባቸው መናገራቸውን ታዝቧል፡፡ ወጣት ታምራት ታደሰ እንደሚለው፣ የኑሮ ውድነቱ ምንም ሥራ ለሌለው ሰው ይቅርና  ለደመወዝ ተከፋዮችም ከቤት ኪራይና ከምግብ ፍጆታ ሳያልፍ እየቀረ የተቀደደ ካልሲ  እስከመልበስ ደርሰዋል፡፡  አሁን ባለው ሁኔታ  እንኳን ያለ ሥራ በሥራም ተሆኖ ለመኖር በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ለበርካታ ዓመታት በትምህርት ጊዜውን ያሳለፈ ወጣት፣ በመጨረሻም በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅት ተቀጥሮ ራሱንና ቤተሰቡን ከችግር ማውጣት፣ አልያም በግሉ ሥራ ፈጥሮ በስኬት መንገድ መጓዝ  ህልሙ ነው።

ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከምርቃት በኋላ መሥራት እየቻሉ ራሳቸውን በቤት ውስጥ ሲያገኙት፣ ልፋታቸው መና ሆኖ የቀረ ሲመስላቸው፣ ጭንቀትና ብስጭት በራስና በአገር ላይ ተስፋ መቁረጥ  ይንፀባረቅባቸዋል፡፡

ነገሩ በዚህ አያበቃም ወጣት ልዑል ሞገስ እንዳለው ከሁሉም ነገር ከባዱ የአዕምሮ ሥራ ነው፡፡ ይህንን የአዕምሮ ሥራ የሚጠይቀው ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት ተምሮ ሥራ ካልተገኘ ከቤት መዋል ይመጣል፡፡ በቤት ውስጥ መቀመጥ ጭንቀትና ድብርትን እንደሚያስከትል ይናገራል።

አንድ ሰው ተምሮ ሥራ ካላገኘ በተለያዩ ሱሶች የመጠመድ ዕድሉ ሰፊ ነው ይላል፡፡ ይህ እንዳይሆን ተማሪ ለፍቶ ተምሮ ሲጨርስ ሥራ ማግኘት ግዴታ ነው ባይ ነው።

‹‹አንድ ሰው የ25 ዓመት ወጣት ሆኖ ከቤተሰብ የካርድ ስጡኝ ብሎ መማፀን በጣም የሚያሳፍር ነው፤›› የሚለው ደግሞ ወጣት ጵንኤል ታመነ ነው።

ቤተሰብ ልጄ ተመረቀ ለወግ ለማዕረግ በቃ፣ ራሱን ጠቅሞ እኛንም ይረዳል በማለት ዘመድ ጎረቤቱን ደግሶ አብልቶ ሲያበቃ፣ አሁንም ተመልሶ የቤተሰብ ሸክም ዛሬም እንደ ሕፃን ልጅ መልሶ ማስቸገር ከባድ ነው ይላል።

ገና የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ መንግሥት አዲስ ለሚመረቁ ተማሪዎች የሥራ ቅጥር እንደማይኖር ሲናገር፣ በትምህርት ላይ ያለው ተስፋ ተሟጧል። ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ…›› እንደሚባለው መንግሥት የሥራ ቅጥር እንደማይፈጽም ቢገልጽም፣ ቀድሞውንም አጥጋቢ የሆነ የሥራ ቅጥር የሌለበት ሁኔታ እንደነበር ይናገራል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ በወቅቱ በመንግሥት በኩል የሥራ ቅጥር እንደሌለ መነገሩ፣ ‘ከ17 ዓመታት በላይ የተለፋበት ትምህርት ዋጋው ምን ሊሆን? ነው’ ብለው ምሩቃኑ ተጨንቀው እንደነበር ያስታውሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...