ለስድስት አሠርታት ያህል በጋዜጠኝነት ያገለገሉ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው የዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ ጋዜጣ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አቶ ያዕቆብ ወልደ ማርያም ሥርዓተ ቀብር፣ ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖች ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ተፈጽሟል፡፡
በሦስት መንግሥታት ውስጥ በማለፍ በፕሬሱ ለ37 ዓመታት ያገለገሉት ልሂቅ የፕሬስ ሰው አቶ ያዕቆብ፣ ከዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ በተጨማሪ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (ቅድመ 1967) ይታተሙ በነበሩት በቮይስ ኦቭ ኢትዮጵያ [መሪ ቃሉ ‹‹ነፃ ጋዜጣ ለነፃ ሕዝብ›› የሚል ነበር]፣ በመነንና በየካቲት መጽሔቶችም በዋና አዘጋጅነት ሠርተዋል፡፡
በጋዜጣው በሠሩባቸው ዓመታት በርካታ የኤዲቶሪያል ውሳኔዎችንና ጽሑፎችን ማበርከታቸው፣ በተለይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤት እንዲቋቋምና ዘመናዊ የሰው ኃይል አደረጃጀት በአገሪቱ እንዲኖር በርካታ ጽሑፎችን መጻፋቸው፣ የመሬት ይዞታው ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለድህነት አጋልጦታል የሚል አቋም ስለነበራቸውም ይሄው እንዲስተካከል በጽሑፎቻቸው ግፊት ያደርጉ እንደነበር በገጸ ታሪካቸው ተወስቷል፡፡
የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት (1923- 1967) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ንግግሮችንም በግሩም እንግሊዝኛ እየተረጐሙ ለውጪው ማኅበረሰብ መልዕክቱ እንዲደርስ ያደርጉም ነበር፡፡
ሌላው በተለይ የንጉሡ ሹመኞች በሕዝብ ላይ በደል እያደረሱ ነው የሚል ይዘት ያለው የሰላ ትችትም ያቀርቡ እንደነበር፣ ከዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ጽሑፋቸው ‹‹Rotten at the Root›› [ከሥር መሠረቱ የበሰበሰ] በሚል ርዕስ የጻፉት ኤዲቶሪያል (ርዕሰ አንቀጽ) ነው፡፡
በፀረ ኮሎኒያሊዝምና ፀረ ኒዮኮሎኒያሊዝም አቋማቸውም የሚታወቁት አቶ ያዕቆብ, በአዲስ አበባ ካሉ ኤምባሲዎችም በዚህ ከፍተኛ ነቀፌታ ይደርስባቸው እንደነበር፣ እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን እንዲያቆሙ ማስገንዘቢያ እንደደረሳቸውና እሳቸውም በምላሻቸው ሊቆም የሚችለው እነሱም እኩይ ተግባራቸውንና አስተሳሰባቸውን ሲተዉ እንደሆነ በወቅቱ አስረግጠው መናገራቸው የአቋማቸውን ፅኑነት ያሳያል፡፡
ምንም እንኳ በርካታ ዓመታት በመንግሥትና የሕዝብ ጋዜጣ ላይ ቢሠሩም፣ ለሐሳብ ብዝኃነት ያላቸው ፅኑ አቋም በሥራዎቻቸው እንደሚንፀባረቅ፣ ሕዝቡና መንግሥት ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙም ይሠሩ እንደነበር ሥራቸው ይገልጻል የተባለላቸው አቶ ያዕቆብ፣ ለምሳሌ ያልተሳካውን የንዋይ ወንድማማቾች [መንግሥቱና ገርማሜ] የመንግሥት ግልበጣን (የታኅሣሡ ግርግር) በተመለከተ አንዱ ሌላውን ለመወንጀልና በንጉሡ ፊት ለማሳጣት ይሞክር እንደነበረ ይህንንም ተከትሎም ‹Lack of Information is a fundamental problem of the country› [የመረጃ ዕጦት የአገሪቱ መሠረታዊ ችግር ነው] የሚል ጠንካራ ኤዲቶሪያል መጻፋቸው ተጠቅሷል፡፡
‹‹የሩሲያን የየካቲት (ፌብሬዋሪ) እና የጥቅምት (ኦክቶበር) አብዮቶች አድንቀውም በስማቸው ጽሑፎችን ያትሙ ነበር፡፡ ምናልባትም ይህ ጽሑፍና ሌሎች የኤዲቶሪያል አቋሞቻቸው በዋና አዘጋጅነት ሥራቸው እንዳይቆዩ አድርጓቸዋል፡፡
‹‹አንዳንዶች የጋዜጠኛ ያዕቆብ እንግሊዝኛ ጠጠር እንደሚል ይናገራሉ፡፡ እሳቸውም ይህንን ሆን ብለው እንደሚያደርጉትና ተራ ካድሬ በቀላሉ እንዳይገነዘብና እንዳያስቆማቸው እንደሆነ የተናገሩበት አጋጣሚ አለ፡፡
በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ በጋዜጠኛ ሚሊዮን ተረፈ በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው እንደተገለጸው፣ በሽግግር መንግሥት ዘመን በ1986 ዓ.ም. ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በሚኒስቴሩ ይታይ የነበረውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት በፕሬስና ኢንፎርሜሸን ክፍል ለሰባት ዓመታት አገልግለዋል፡፡
ከመንግሥታዊ ተግባራቸው ጡረታ ከወጡ በኋላ በተለያዩ በእንግሊዝኛ በሚታተሙ የግል ጋዜጦች ላይም ሠርተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የሚጠቀሱት አዲስ ትሪቢዩን እና ዘ ሪፖርተር ጋዜጦች በከፍተኛ አዘጋጅነት ጭምር ሠርተዋል፡፡
አቶ ያዕቆብ የጋዜጠኝነት ሙያ ወደ ውስጣቸው ዘልቆ የገባው በእንግሊዝ አገር የከፍተኛ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ነበር፡፡
በዜና ሕይወት ወዕረፍታቸው ላይ እንዲህም ተነበበ፡-
‹‹እንግሊዝ አገር በነበሩበት ጊዜ ሲሊቪያ ፓንክረስት ያዘጋጁት በነበረው ‹ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያን ኒውስ› በሚባል የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ መጣጥፎቻቸውን ያወጡ ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ወደ ውስጣቸው ዘልቆ የገባው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ስለዚህ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ የማኦ ማኦ የነፃነት ትግል በኬንያ ሲካሄድ እዚያው ኬንያ ሆነው ሁኔታውን መታዘባቸው ነበር፡፡ ነጮቹ በሚጽፏቸው መጣጥፎች አፍሪካውያን ሰብዕና ላይ ጭራና ቀንድ እየቀጠሉ እንዴት አድርገው ከሰውነት በታች (ዲ-ሂውማናይዝ) እንደሚያደርጉ አንብበዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በእንግሊዝኛ መጻፍና ትክክለኛውን የአፍሪካውያን ሥዕል መስጠት የግድ መሆኑን አምነው በስፋት ሠርተዋል፡፡››
አቶ ያዕቆብ ጋዜጠኛ ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ ሙያዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ በዋናነት የሚጠቀሱት በወለጋ ጠቅላይ ግዛት ነቀምቴ ከተማና በአዲስ አበባ በአምሀ ደስታ ትምህርት ቤቶች ለአንድ አንድ ዓመት በመምህርነት፣ በቀድሞ የኢትዮጵያ መብራት ኃይልና በውኃ ክፍል ለአንድ ለአንድ ዓመት ሠርተዋል፡፡
ለዘመናት በዘለቀው አገልግሎታቸው ባከናወኗቸው ሥሉጥ ተግባራት ካገኟቸው ሽልማቶች መካከል፣ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ [የኢትዮጵያ ድምፅ] ጋዜጣ ባሳዩት ትጋትና የአሥር ዓመት አገልግሎት የፈረሰኛ ኮኮብ ኒሻን ከንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እጅ መቀበላቸው፣ ከስምንት ዓመታት በፊትም በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት አሸናፊም ነበሩ፡፡
ግለ ታሪካቸውንና የተመረጡ መጣጥፎቻቸውን የያዘ Yacob Wolde-Mariam brief Autobiography and Selected Article የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ በ1995 ዓ.ም. ያሳተሙት አቶ ያዕቆብ፣ በትዳር ሕይወታቸው 10 ልጆች ሲያፈሩ፣ በሕይወት ካሉት 4 ወንድና 3 ሴቶች ልጆቻቸው ስምንት የልጅ ልጅ እንዲሁም አንድ የልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል፡፡
ነፍስ ኄር ያዕቆብ ወልደ ማርያም በ94 ዓመታቸው ያረፉት ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡