Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሠዓሊና መምህሩ አብዱራህማን መሐመድ ሸሪፍ ሲታወሱ

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

አቶ አብዱራህማን መሐመድ ሸሪፍ መስከረም 5 ቀን 1931 ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ መርካቶ፣ አደሬ ሠፈር እየተባለ በሚጠራው ሠፈር ተወለዱ፡፡ የአቶ አብዱራህማን  የረዥም ጊዜ ወዳጅ የሆኑት አህመድ ዘካሪያ (ረዳት ፕሮፌሰር) ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደገለጹት፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሥዕል የመሣል ዝንባሌ ነበራቸው፡፡ በዓይን ዕይታ የሚስተዋሉትን ቅርፆች ብቻ ሳይሆን አንድን ፎቶግራፍ በወረቀት ላይ ለመሣል በሥዕሉ ላይ አግድምና ቋሚ መስመሮችን እንደ ስኩዌር ወረቀት በማስመር፣ (ስኬል በማውጣት) መሥራት ሲጀምሩ የአካባቢው ሰው በግርምት ይመለከታቸው ጀመር፡፡

በኋላም ያለ መስመር የሰዎችንና የአካባቢያቸውን ምስል መሣል ጀመሩ፡፡ ይልቁንም በየመንገዱ ሥራ ፈትቶ በወረቀት ላይ ሲሞነጫጭሩ ማየት በአካባቢው እንግዳ ነገር ስለነበር ‹‹ልጄ ሰዎች አብደሃል እንዳይሉህ ሌላ ትምህርትህን አጥና›› በማለት ከመምከር እስከ ‹‹ሥዕል መሥራት በኢስላም ሐራም ነው›› በሚል መከልከል ተፅዕኖ አሳዳሩባቸው፡፡ በኋላ ግን አቶ ጡኃ ሸሪፍ የሚባሉ ነጋዴ ዘመዳቸው የውጭውን ዓለም የሚያውቁ፣ ዘመናዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች አንዱ የነበሩና አንድን ሕፃን በዝንባሌው እንዳይሠራ መከልከል አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ፣ በሌሎች አገሮች ያዩትን ልምድ ጨምረው ለአባታቸው በመንገር እንዲቀጥሉ አደረጓቸው፡፡ ከዚያም በአንድ በኩል መደበኛ ትምህርታቸውን በሌላ መልኩ ደግሞ ሥዕላቸውን እየሣሉ የልጅነት ዕድሜያቸውን ማሳለፍ ቀጠሉ፡፡

ሆኖም በወቅቱ የሥዕል ትምህርት ቤት ስላልነበረ ሊሆን ይችላል የገቡት ኮሜርስ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በዚህ የትምህርት ቆይታቸውም በወቅቱ ሲሰጥ የነበረውን ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ እሳቸው በኮሜርስ ትምህርት ቤት ይከታተሉ በነበሩበት ጊዜ እንደ ባለቅኔው ፀጋዬ ገብረ መድኅን ያሉ ወጣቶችም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ ትምህርታቸውን  እንዳጠናቀቁም ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ሱዳን ተላኩ፡፡ ሆኖም ሱዳን ሲደርሱ የምዝገባ ጊዜው አልፎ ስለነበር የኮሜርስ ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም ያሉ አህመድ ዘካሪያ፣ ለአንድ ዓመት ሥራ እንዳይፈቱ ሥዕል ትምህርት ቤት በመግባት መከታተላቸውን፣ ከአንድ ዓመት በኋላም ወደ አገራቸው በመመለስ በሥዕል ትምህርት ቤት እያስተማሩ እንዲማሩ እንደፈቀደላቸውና የተማሪ አስተማሪ እንደሆኑ አህመድ ዘካርያ (ረዳት ፕሮፌሰር) ያወሳሉ፡፡

አቶ አብዱራህማን  በኮተቤ ትምህርት ቤት የሥነ ጥበብ አስተማሪ በመሆን እስከ 1962 ዓ.ም. ድረስ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ1967 እስከ 1985 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት (ዛሬ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት) ከመምህርነት እስከ ዳይሬክተርነት ሠርተዋል። በርካታ ተማሪዎችን አማክረዋል። በተለያዩ አገሮች በተካሄዱ ሲምፖዚየሞች ጥናታቸውን ከማቅረባቸው ባለፈ ሥራዎቻቸውም በምርምር መጽሔቶች ታትመውላቸዋል። 

ገረመው ፈይሳ (ዶ/ር) እና ዓይናለም እምሩ፣ በአብራክ ቤተ ሥዕል መጽሔት ውስጥ የአቶ አብዱራህማንን ታሪክ አትተዋል፡፡ በመጽሔቱ በሰፈረው ትንታኔ መሠረት፣ አቶ አብዱራህማን  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮሜርስ ትምህርት ቤት እንደጨረሱ፣ በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትና  የሱዳን መንግሥት ባደረጉት የመጀመርያ የባህል ስምምነት መሠረት ቻርተር አካውንታንት ለመሆን በነፃ እንዲማሩ  ከሌሎች ሦስት ወጣቶች ጋር ወደ ካርቱም ተልከዋል፡፡  በተላኩበት ወቅትም የቻርተር አካውንታንት ትምህርት ሳይሆን በራሳቸው ውሳኔ ካርቱም በሚገኝ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ነፃ የትምህርት ዕድል አገኙ፡፡ በዚያም ተቋም የዕውቁ ሱዳናዊ ሠዓሊና የአፍሪካ ሞድርኒዚም አቀንቃኝ በነበረው ኢብራሂም አልሳላዊ ተማሪ ሆኑ፡፡

በመጽሔቱ መረጃ መሠረት፣ የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደሚጎበኙ ስለታወቀ፣ አብዱራህማን የንጉሡን ምስለ አካል በአጭር ቀን እንዲሥሉ በአቶ አለ ፈለገ ሰላም ታዘዙ፡፡ እሳቸውም በከሰል (ቻርኮል) የአሣሣል ሥልት ተጠቅመው ያቀረቡትን ምስል ንጉሠ ነገሥቱ አደነቁላቸው፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ በመደነቃቸውም መልካም ዕድል ተፈጠረላቸው፡፡ በ1957 እስከ 1962 ዓ.ም. በጀርመን  በሚገኙት የኬሰልና የበርሊን የሥነ ጥበብ አካዴሚዎች ነፃ ትምህርት በማግኘት  በዘመናዊ ሥነ ሥዕልና ግራፊክስ ትምህርት ሠልጥነዋል፡፡

አቶ አብዱራህማን  ከፍተኛ የሥነ ጥበብ ትምህርታቸውን የስክሪን ፕሪንቲንግ ትምህርትን ጨምሮ የተከታተሉበት የበርሊኑ አካዴሚ በዓለም ከታወቁት የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡

በአስተማሪነትና በዳይሬክተርነት የሕይወት ዘመናቸውም በአዲስ አበባና በተለያዩ አገሮች  ቤልጂየም፣ በቀድሞዋ ቺኮዝሎቫኪያ፣ በጀርመን፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት፣ በናይጀሪያና በአሜሪካ የሥዕል ኤግዚቢሽን አቅርበዋል።

አህመድ ዘካሪያ አቶ አብዱራህማን  ሸሪፍን በሦስት መንገድ ሲገልጿቸው ‹‹አንደኛው ሥራቸው ላይ የሚያተኩሩ፣ ሁለተኛ በሌላ ሰው ሥራ ጣልቃ የማይገቡ፣ ሦስተኛው የቤተሰብ ፍቅር ያላቸው ናቸው፤›› ይሏቸዋል።

ሁለተኛውን ባህሪያቸውን በምሳሌ ሲያቀርቡ ወደ ሥዕል ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው ሲመጡ የገቡት በአገሪቱ ግዙፍ ሆነው ከሚታዩት የሥነ ጥበብ ሰዎች መካከል ነበር፡፡ ከነዚህም ሰዎች መካከል አንደኛው ዛሬ ትምህርት ቤቱ በስማቸው  የተሰየመላቸው አለ ፈለገ ሰላም፣ ሁለተኛው ደግሞ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ናቸው። እነዚህ ምሁራን የየራሳቸው የሆነ አመለካከት (የሥዕል አስተምህሮ) ነበራቸው። በእነዚህና በሌሎቹም አስተማሪዎች መካከል የነበረው የአስተሳሰብ ልዩነት በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡ ከዚህ ላይ ልዩ ልዩ ርዕዮተ ዓለም ይከተሉ በነበሩ የውጭ አገር መምህራን ሲጨመሩ ልዩነቱን ከፍ እንደሚያደርገው እሙን ነው፡፡

ይህም የአስተምህሮ ልዩነት እስከ ተማሪውና አስተዳደሩ ስለሚዘረጋ ሁሉንም አቻችሎ መምራት ከፍተኛ ሥራና ጥረት  ይጠይቅ ነበር። ይልቁንም የአስተሳሰብ ልዩነቱን አቻችሎ ለሥነ ጥበብ ዕድገት አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ በመረጣቸው የሁሉም ወዳጅ ነበሩ ማለት በሌላ ሰው ሥራ ጣልቃ የማይገቡ እንደነበሩ የሚያመለክት ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡

ረዳት ፕሮፌሰሩ ጨምረው እንዳብራሩት፣ ቤታቸው ከትምህርት ቤታቸው ሩቅ ስላልነበረ ትምህርት ቤቱን በዳይሬክተርነት ከመምራታቸውም በላይ አምሽተው የሥነ ጥበብ ሥራቸውን ለመሥራትና ከሰዓቱ በፊት ጠዋት ገብተው የቀኑን ሥራ ለማመቻቸት ረድቷቸው ነበር።

በሐረሪ ቤተሰብ ተኮትኩተው ማደጋቸው፣ በልጅነታቸው ያገኙት የሃይማኖት ትምህርት ሥነ ምግባር፣ የሐረሪ ባህል ተፅዕኖ (የሱፊ ባህል) በራሳቸው ሥራ ማተኮር እንጂ በሌሎች ሕይወት ጣልቃ እንዳይገቡ ያደረጋቸው ይመስለኛል።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አቶ አብዱራህማን ን የሚያውቃቸው ከ1980 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። በነበረው ዕውቂያም ወደ አዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት በመሄድ ቢሮዋቸውንና የትምህርት ቤቱን ክፍሎች ተዘዋውሮ ጎብኝቷል። በወቅቱም የሥዕል ትምህርት ቤቱን የበለጠ ለማዘመን ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለው የመምህራንና የአስተዳደር ችግሮች በተለይም ትምህርት ሚኒስቴር ለዕድገት ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑን ቢያውቅም ሊሆን ከሚገባው የመጨረሻው በጀት እንኳን ስለማይመድብለት የሚታሰበውን ያህል ለመሥራት እንዳልተቻለ ገልጸውለታል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአብዮቱ በፊት ምዕራባውያን አስተማሪዎች ሲመጡ የአገራቸው ትምህርት ቤቶች ፈንድ እያስፈቀዱ ይሠሩ የነበሩ ሲሆን፣ ይህም ለአገር ውስጥ መምህራኑም በትንሹም ቢሆን ይጠቅም ነበር። ምሥራቅ አውሮፓውያን ግን በዚህ ረገድ ብዙ አይረዱም። ተማሪዎቹ  በሚገባው የሥነ ጥበብ ዕውቀት ለማነፅ የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ በትምህርት ቤቱ ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ ተምረው አስተማሪ ከመሆን በስተቀር ሌላ ዕድል ስለማይጠብቃቸው ብዙዎቹ የጨፈገጉ ናቸው። ከዚህ ላይ የአስተማሪዎቹ ቁጥር ሲጨመር ችግሩን የበለጠ ውስብስብ እንዳደረገው አስረድተውታል።

‹‹ማን ያውጋ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንዲሉ ስለ አቶ አብዱራህማን  መሐመድ ሸሪፍ  ከሚነግሩን  ተማሪዎቻቸው መካከል፣ ስመ ጥሩ  ከሆኑት የሥነ ጥበብ ሰዎች አንዱ የሆኑት እሸቱ ጥሩነህ ናቸው። አቶ እሸቱ በማኅበራዊ  ገጻቸው ስለ መምህራቸው ትውስታቸውን በጥቂቱ ያጋሩት ከ1962 እስከ 1966 ዓ.ም. ከነበረው በመገደብ ነው፡፡

‹‹የቀይ ዳማና መልከ መልካም ገጽታን የተላበሰው ፊቱ፣ አዘውትሮ ፂሙንና ሪዙን የሚላጭ፣ ሙሉ ሱፍ ልብስ ከነከረባቱ ከሚለብሰው ተክለ ሰውነቱ ጋር፣ ሲናገር ድምፁ ለስለስና ረጋ ያሉ፣  ነጣ ያሉ ዓይኖቹ የዋህነትንና ትህትናን የሚያንፀባርቁ ዓይን አፋር፣ ግን  ጥንቁቅነትን ያልዘነጉ  እንደነበሩ ዛሬም ድረስ ይታወሰኛል፤›› በማለት ስለ አቶ አብዱራህማን  ሥዕላዊ መግለጫቸውን ይሰጡናል።

አያይዘውም ‹‹እኔና የክፍል ጓደኞቼ የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበርንበት ጊዜ፣ ሠዓሊ አብዱራህማን (እኛ ጋሼ ነው የምንለው) ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ የኪነ ኅትመት ጥበብ  (Graphic Art) ትምህርት መምህራችን ነበር። ይህን ትምህርት ቀደም ብሎ በተለያዩ  ዓመታት ያስተምሩ የነበሩት የውጭ አገር ዜጋዎች ነበሩ፡፡  ከእነሱ ቀጥሎ (ከ1962 ዓ.ም. አንስቶ) በትምህርት ቤቱ በቋሚነት ማስተማር  የጀመረ ኢትዮጵያዊ መምህር ነበር ለማለት ይቻላል፤›› ይላሉ። 

አስተማሪው ከሌሎች አስተማሪዎች የሚለዩበትን  መሠረታዊ ባህሪያት ሲገልጹም፣ ‹‹ወደ ትምህርት ቤቱ አጥር ግቢ  በአንዲት ቡናማ ታኑስ መኪና እንደመጣ ወዲያው  ወደ አስተዳዳሪው ቢሮ ይገባና ፊርማውን ያኖራል። ከዚያም ይወጣና ወደ ራሱ ቢሮ ይሄዳል፡፡ ኮቱን አወላልቆ የሥራ ልብሱን (ጋዋን) በመልበስና የማስተማሪያ ቁስ  ጥበባትንና በታይፕ የተጻፉ ጽሑፎችን ይዞ ወደ ማስተማሪያ ኪነ ኅትመት ክፍሉ ይመጣል። እኛም ተማሪዎቹ በክፍሉ ውስጥ ቀደም ብለን ገብተን  ስለምንጠብቀው፣ እንደገባ የኪነ ኅትመት ማተሚያ ሰሌዳውንና የመፈልፈያ የብረት ሰንጢዎቹን የያዘውን ማኅደር (ፎልደር) ለእያንዳንዳችን እንዲታደል ካደረገ በኋላ፣ በተግባር ስለምንማረው የትምህርት ሒደት በቅደም ተከተል ያስረዳናል፡፡ በዓይነትም ከተሠሩ ኪነ ኅትመቶች በናሙናነት ያሳየናል፣ ያስጀምረናል፣ ለጥቂት ደቂቃዎች የጀመርነውን  እየዞረ  ያያል፣ አስተያየትን ይሰጣል፡፡ ቀጥሉ ብሎ ወደ ቢሮው በሥዕል ቋንቋ ወደ ቤተ ሥዕል ማዘጋጃው ይገባል፡፡ የግሉን የፈጠራ ሥዕል ጥበቡን ያከናውናል፣ በመጨረሻም ሰዓቱ ሲደርስ ይመጣል። ያደለውን መልሶ ይሰበስባል፣ ያስገባል፣ በቃ ወደ ቤቱ ወይም ወደ ሌላ ይሄዳል፣ አጥር ግቢውን ለቆ ይበራል፤›› ይሉናል። 

ካስተምሯቸው የኪነ ኅትመት ጥበብ ትምህርት መካከል  የእንጨት ሰሌዳ ቁርጥ ኅትመት፣ ጥቁርና ነጭ ወይም የኅብረ ቀለማት፣  የሐር ጨርቅ ኅትመት፣ ክርክም ቁርጥ ኅትመት/ስቴንስል/ በሐር ጨርቅ የሻማ ማቅለጥ  ኅትመት፣ እንዲሁም የሥዕል አስተማሪነት ሥልጠና እንደሚገኙበት ሠዓሊ እሸቱ አውስተዋል፡፡

አቶ አብዱራህማን ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡ የሚከተሉትንም ፍልስፍና በሥዕሎቻቸው ላይ አስቀምጠዋል፡፡ በፍልስፍና የተጫኑ ስለነበሩም ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን አላከናወኑም ይሆናል፡፡ እንደሌሎች እኩያዎቻቸውም እየተጨዋወቱ አላሳለፉም ይሆናል፡፡ ለረዥም ጊዜ በውጭ በመኖራቸው ምክንያትም ዘመዶቻቸው የሚፈልጉትን አላደረጉም ይሆናል፡፡ አንድ ሀቅ ግን አለ፡፡ ትልቅ የሥነ ጥበብ ሰው ነበሩ፡፡ እኝህም ሰው ሥነ ጥበብን ለግማሽ ምዕት ዓመት አገለገሉ፡፡ በመጨረሻም መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ለማሟላት ወደ ሐጅ ሄዱ፡፡ እዚያም አለፉ፡፡ ለአንድ ሙስሊም ከዚህ የበለጠ ትልቅ ነገር ከቶ የለም፡፡ ትልቁንም ዕድል አላህ አጎናፀፋቸው፡፡ በጀነት ከደጋጎች ጋር ያኑራቸው፡፡ አሚን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles