Tuesday, September 26, 2023

የብሪክስ አባልነት አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃንና ፖለቲከኞች በሩሲያው የጦር ድርጅት ዋግነር መሪ ዬቭጌኒ ፕሪጎዢን ሞት ሐዘን የተቀመጡ ይመስላል፡፡ ለሰውዬው ድንገተኛ ሞት መንስዔ ከሆነው ከአውሮፕላኑ አደጋ በስተጀርባ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እጅ አለበት የሚለውን ውንጀላ ምዕራባዊያኑ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን ብዙ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን ከደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የተሰማውን ዜና የፕሪጎዢን መርዶ ፈጽሞ ሊጋርደው አልቻለም ነበር፡፡

ከ35 አገሮች በላይ መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት 15ኛው የብሪክስ ጉባዔ የዓለምን ትኩረት በተለየ ሁኔታ የሳበ ሁነት ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ረቡዕና ሐሙስ የተካሄደው የብሪክስ የጆሃንስበርግ ጉባዔ፣ መላው ዓለም በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው ውሳኔ የተላለፈበት በመሆኑ ብዙ ትኩረት ለማግኘት ችሏል፡፡

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና እ.ኤ.አ. በ2009 የፈጠሩት የፈጣን አዳጊ አገሮች ማኅበር የሆነው ብሪክስ በቀጣይ ዓመት 2010 ደቡብ አፍሪካን በማከል የአምስት አገሮች ስብስብ ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡ ማኅበሩ ለረዥም ጊዜ የአባላቱን ቁጥር በመጨመር ራሱን የበለጠ እያጠናከረ እንደሚሄድ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ ከረዥም ጊዜ በፊት የማኅበር አባል የመሆን ፍላጎት አንዳንድ አገሮች ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ በቅርብ ጊዜያት ደግሞ ወደ 40 አገሮች የማኅበሩ አባል ለመሆን ፍላጎት አላቸው ሲባል ነበር፡፡

የብሪክስ አባልነት አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በብሪክስ ጉባዔ ተሳታፊ ነበሩ

በይፋ የብሪክስ ማኅበረተኛ ለመሆን 22 አገሮች ጥያቄ ማቅረባቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሪክስን ለመቀላቀል ያለው ፍላጎት መጨመሩን ጠቋሚ ተደርጎ ይታያል፡፡ ማኅበሩ ለዚህ የረዥም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ የያዘው ደግሞ በሰሞኑ የደቡብ አፍሪካው ጉባዔ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በጆሃንስበርጉ የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ የአባል አገሮችን ቁጥር በማሳደግ ጉዳይ ላይ የሚተላለፈው ውሳኔ በጉጉት ተጠባቂ ነበር፡፡

የብሪክስ ማኅበር አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረቡ አገሮች አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ያገኝ ይሆን? የሚለው ጉዳይ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተጠባቂ ጉዳይ የሆነውም ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

‹‹በርካቶች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ይገባሉ ብለው አልጠበቁም ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ተለቅ ያሉ አገሮች ይመረጣሉ ተብሎ ነበር፡፡ እንደ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያና ኢንዶኔዥያ ያሉ አገሮች የአባልነት ቅድሚያ ያገኛሉ ተብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከብዙዎች ግምት በተቃራኒው ኢትዮጵያ አባል ሆና ተመርጣለች፤›› በማለት ይናገራል ጋዜጠኛና የውጭ ግንኙነት ተንታኙ ፍትሕአወቅ የወንድወሰን፡፡ እንደ አልጄሪያ ያሉ አገሮች እ.ኤ.አ. ከ2022 ጀምሮ የአባልነት ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚያወሳው ፍትሕአወቅ፣ ኢትዮጵያ የአባልነት ቅድሚያ ለማግኘት ተጨማሪ ምክንያቶች ያላት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ እንደ ባህል ይዛው የቆየችው የዲፕሎማሲ አካሄድ ድምር ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከርዕዮተ ዓለማዊ ጎራ ነፃ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫ ስትከተል መቆየቷ፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ መሆኗ፣ የአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት በር መሆኗ፣ እንዲሁም ቅኝ ሳትገዛ ነፃነቷን ጠብቃ መዝለቋ ሁሉ ከሌሎች ቀድማ እንድትመረጥ እንዳደረጋት እገምታለሁ፤›› በማለትም ሐሳቡን ያክላል፡፡

ብሪክስ በደቡብ አፍሪካ ጉባዔው ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አገሮችን በአባልነት መቀበሉን ይፋ አድርጓል፡፡ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኢራን፣ አርጀንቲና፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አዲሶቹ የብሪክስ አባል አገሮች መሆናቸው ይፋ ሆኗል፡፡ ውሳኔውን ይፋ ያደረጉት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የአባል አገሮችን ቁጥር የማሳደጉ ጉዳይ በተለያየ ምዕራፍ የሚካሄድ መሆኑን በማስታወቅ፣ በመጀመሪያው ዙር ስድስቱን አገሮች ለማስገባት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

የስድስቱ አገሮችን መቀላቀልና የብሪክስ አባላት አገሮች ቁጥር ወደ 11 ማደጉን ተከትሎ በርካታ ጉዳይ እየተነሳ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ወገኖች የማኅበሩን ስም ብሪክስ ሲደመር ወይስ ብሪክስ 11 ሊሉት ነው እያሉ ተከራክረዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ስለአባላቱ አመራረጥ ትኩረት ሰጥተው እያወጉ ሲሆን፣ ሌሎች በበኩላቸው ስለማኅበሩ ማደግና መፈርጠም ብዙ እያሉ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር)፣ ‹‹የብሪክስ አባል መሆን በረከትም መርገምትም ይዞ የሚመጣ ነው፤›› ይሉታል፡፡ የፋይናንስ ምንጭ አማራጮች ማግኘት መቻልን ይዞ ከሚመጣቸው በረከቶች አንዱና ትልቁ ነው የሚሉት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ይህም የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግር የሚያቀል መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ለልማት የሚውል ፋይናንስ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ማግኘት ሲፈትነን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ የማደግ ትልቅ ተስፋና ሰፊ ዕድሎች ያለን ብንሆንም የልማት ፋይናንስ ለማግኘት ተቸግረናል፡፡ የብሪክስ አባል በመሆናችን ግን የፋይናንስ አማራጫችን እንደሚያሰፋው ይጠበቃል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የብሪክስ አባል በመሆናችን በሌላ ወገን አደጋ ሊጋብዝ የሚችል ስለመሆኑ ምሁሩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የብሪክስ አባል ስንሆን ጎራ መርጠናል/ለይተናል ማለት ነው፡፡ የምዕራቡን ዓለም ጎራ ጥለን እነሱ ባላንጣ (ተፎካካሪ) ወደ የሚሏቸው የእነ ቻይናና ሩሲያ ብሎክ ገብተናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ ጎራ በዋናነት በምዕራቡ ዓለም ፍፁም የበላይነት የሚዘወረው ዓለም አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓተ ማኅበር ይቀየር የሚል ትግል አለ፡፡ ፍትሐዊና ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ይፈጠር የሚለው ሐሳብ ጎልቶ ይነሳል፤›› ሲሉ የሚናገሩት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ወደ እዚህ ካምፕ በአባልነት መቀላቀል ደግሞ ምናልባትም ከምዕራባዊያኑ ጋር ሊያጋጭ የሚችል ችግር ይዞ እንደሚመጣ ይጠቅሳሉ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያ ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የብሪክስ አባል በመሆን የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚያነሱት፡፡ ‹‹የመጀመሪያው ጥቅም የብሪክስ አገሮች ጉልህ የኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂያዊ አቅም የፈጠሩ ናቸው፡፡ እኛ ወደ 70 ሚሊዮን ሔክታር የሚታረስ መሬት አለን፡፡ በግብርና ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ቴክኖሎጂ ለማግኘት እንችላለን፡፡ ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ በሚል ብሪክስ የፈጠረው ባንክ ጥሩ ጅማሮ እያደረገ ነው፡፡ ለደቡብ አፍሪካ እስካሁን 5.5 ቢሊዮን ዶላር ያበደረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ 16 ቢሊዮን ዶላር ለብድር ፈቅዷል፡፡ አሁን እኛም የማኅበሩ አባል በመሆናችን ይህን ዓይነት ፋይናንስ ለማግኘት ዕድል ይፈጥራል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል  በመሆኗ በምዕራባዊያን ወገን ሊፈጠርባት የሚችል ጫናና ተፅዕኖ ሊኖር ይችላል በሚለው ጉዳይ ላይ ምሁራኑ የተለያየ ምልከታቸውን ነው ያጋሩት፡፡ ብሪክስ በተናጠል ሉዓላዊ የሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚከተሉ አገሮችን ያሰባሰበ የአገሮች ማኅበር እንጂ፣ ፖለቲካዊ ድርጅት አለመሆኑ ይነገራል፡፡ ያም ቢሆን ግን ማኅበሩ እንደ ቻይናና ሩሲያ ያሉ አገሮች ያሉበት በመሆኑ የማኅበሩ አባል መሆን ምናልባትም ከምዕራቡ ካምፕ የተለየ ተፅዕኖ የሚጋብዝ ጉዳይ ስለመሆኑ ሥጋት አለ፡፡

ይህ ተጨባጭነት ያለው ሥጋት መሆኑን የሚጋሩት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ብሪክስ ከአመሠራረቱ በዓለም ላይ አዲስ ዓይነት ሥርዓት እንዲገነባ ውጥን የያዘ መሆኑ ምዕራባዊያኑ በዓይነ ቁራኛ እንዲያዩት የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ፍትሐዊ፣ ሁሉን ያቀፈና አዲስ ዓይነት የዓለም ሥርዓት ይፈጠር የሚሉ አገሮች ስብስብ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ ዓለም በምዕራባዊያኑ አገሮች ፍላጎትና ተፅዕኖ ሲዘወር ነው የቆየው፡፡ የብሪክስ ፍላጎት ደግሞ ይህን ነባር አስተሳሰብ የሚገዳደር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የብሪክስ አባል መሆን ከምዕራባዊያኑ ወገን በጠላትነት የመታየት ዕድል የሚፈጥርና ጫና የሚያስከትል ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡ በእሳቸው እምነት በቀጣናው ባለው ጂኦ ፖለቲካ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፉ ሥርዓት የኃይል አሠላለፍ ላይ ከፍ ያለ ጫና ሊፈጠር ይችላል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ግን የብሪክስ አባል መሆን ምናልባትም የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዳ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ ‹‹ህንድ ወይም ብራዚል የምዕራባዊያኑ አጋር ሆነው የብሪክስ አባል ናቸው፡፡ ራሷ ቻይናም ብትሆን የምዕራባዊያኑ ጥብቅ የንግድ አጋር ናት፡፡ ብሪክስ የኢኮኖሚ ወይም የልማት ማኅበር እንጂ የፖለቲካ ተቋም አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ እኛ ደግሞ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓውያን ጋር ከመቶ ዓመታት ያላነሰ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለን፡፡ የብሪክስ አባል መሆናችን ጭቅጭቅ ያመጣብናል ብዬ አላምንም፡፡ ዋናው ነገር የእኛ ሚዛንን ጠብቆ የመጓዝ ጉዳይ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ብሪክስ የአባል አገሮች ቁጥርን ማሳደጉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች አዲስ የዲፕሎማሲና የገበያ አማራጭ ይዞ የሚመጣ ጉዳይ ስለመሆኑ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ማኅበሩን መቀላቀሏን በተመለከተ ‹‹ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል፤›› ብለውታል፡፡

‹‹አገሪቱ ታሪኳ፣ የሕዝብ ብዛቷ፣ ፈጣን ዕድገቷ ሁሉ ታይቶ ነው አባል የመሆን ጥያቄዋ ተቀባይነት ያገኘው፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ አጋጣሚውን ከኢትዮጵያ የመደመጥ አቅም ማደግ ጋር አቆራኝተውታል፡፡

የብሪክስ አባል አገሮች ቁጥር መጨመር ማኅበሩ በብዙ መንገድ የምዕራባዊያኑ ጎራ ተገዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ስለመሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የጋራ ባንክ ምሥረታ፣ የጋራ መገበያያ ገንዘብ የመፍጠር፣ እንዲሁም የጋራ ገበያ ማስፋት ከዚህ ማኅበር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ዕድገቶች ስለመሆናቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን በአንድ ማኅበር አብሮ ለመቆየት የሚቸገሩ የጂኦፖለቲካ ሽኩቻ ያላቸው አገሮች የተሰባሰቡበት ማኅበር ስለመሆኑ በሥጋትነት እየተነሳ ነው፡፡ ቻይናና ህንድ መግባባት አይችሉም ሲሉ የቆዩ ወገኖች አሁን ደግሞ ፍፁም የማይገጣጠሙት ኢራንና የገልፍ አገሮች ወደ ስብስቡ መጨመራቸውን ያወሳሉ፡፡ በሌላ በኩል እንደ ግብፅና ኢትዮጵያ ያሉ የረዥም ጊዜ የጂኦፖለቲካ ሽኩቻ ያለባቸው አገሮች አባል መሆናቸው፣ ብሪክስ በአጠቃላይ በተቃርኖ የተሞላ የጋራ ማኅበር እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል የሚል ሥጋት ከወዲሁ እንዲሰማ አድርጎታል፡፡

የብሪክስ አባል ከሆኑ አገሮች በብዙ መንገዶች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል የሚናገረው ጋዜጠኛ ፍትሕአወቅ፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር ያደረጉትን የብድር ማራዘም ስምምነት ‹‹ሕይወት አድን ስምምነት›› ሲል ይጠራዋል፡፡ ‹‹ለአንድ ዓመት ዕዳ ማራዘም ማለት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ከወራት በኋላ የዩሮ ቦንድ ዕዳችንን መክፈል እንጀምራለን፡፡ የዕዳ ሽግሽግ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ መላው ዓለም ኢትዮጵያ ዕዳዋን በመክፈል ሒደት ሊገጥማት የሚችለውን ችግር በሥጋት እየተከታተለው ነው፡፡ የቻይና ለአንድ ዓመት ዕዳ ለማራዘም መወሰን ከዚህ አንፃር ለአገሪቱ ትልቅ ዕፎይታ ነው፤›› ይላል፡፡

በሌላ በኩል ከሌሎች የብሪክስ አባል አገሮች ሊገኝ የሚችል ሰፊ ተጠቃሚነት መኖሩን ፍትሕአወቅ ይገልጻል፡፡ ‹‹ለምሳሌ በማዳበሪያና በእህል ግዥ ከሩሲያ ሊገኝ የሚችል ተጠቃሚነት አለ፡፡ የብሪክስ ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ደግሞ 30 በመቶውን በተለያዩ መገበያያ ገንዘቦች አደርገዋለሁ ቢልም፣ አሥር ቢሊዮን ዶላር ብድር በዚህ ዓመት መመደቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ ከዚህ ባንክ የመጠቀም ዕድልም ታገኛለች፤›› በማለት ሐሳቡን ያክላል፡፡

ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ያጋሩ ተንታኞች እንደሚናገሩት፣ የብሪክስ አባል በመሆን ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለው ዲፕሎማሲያዊ (ጂኦ ፖለቲካዊ) ውጤት ከፍተኛ ነው፡፡

የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ‹‹የብሪክስ ማኅበር በአባልነት እያሰባሰበ ያለው ከየቀጣናው ተፅዕኖ በመፍጠርና በኢኮኖሚ እየፈረጠሙ የሚሄዱ አገሮችን ነው፡፡ ምዕራባዊያኑ የዚህን ማኅበር እየፈረጠመ መሄድ ዝም ብለው ይመለከታሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ብሪክስ አሁን ላይ አባል ያደረጋቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብፅ፣ ሳዑዲ፣ ኢራን፣ ዓረብ ኤምሬትስ ሆኑ አርጀንቲና ከየቀጣናቸው ጠንካራ እየሆኑ የሚሄዱ መሆናቸው ይጠበቃል፤›› በማለት፣ የአባልነት ምርጫው ጥንቃቄ የተሞላበትና ማኅበሩን የበለጠ የሚያፈረጥም ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

የሺጥላ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ የብሪክስ ማኅበር መጠናከር የምዕራባዊያኑን ዓለም አቀፍ ሚናና ተፈላጊነት እንደሚቀንሰው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹አገሮች ነገ ከነገ ወዲያ በብሪክስ ማዕቀፍ እንወያይ ሊሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያና ግብፅ ያሉ አገሮች በጋራ ማኅበራችን በብሪክስ በኩል ችግራችንን እንፍታ የሚል ነገር ቀስ ብሎ ሊመጣ ይችላል፤›› ሲሉ ግምታቸውን የሚናገሩት ምሁሩ፣ ይህ ደግሞ ምዕራባዊያኑ የማይፈልጉት እንደሆነ ያክላሉ፡፡

ይህ ከመምጣቱ በፊት ምዕራባዊያኑ የብሪክስን መጠናከር ለመቅጨት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹ለዚህና ሊመጣ ለሚችል ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ራሷን ማዘጋጀት አለባት፤›› የሚሉት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ይህንን ጥንካሬ መፍጠር የሚያስችል አገራዊ ሁኔታን መፍጠር ቅድሚያ እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሁለቱም መንገድ ማለትም በምዕራቡም ሆነ በብሪክስ ወገን ኢትዮጵያ ያላትን ግንኙነት ሚዛኑን ጠብቃ ማስቀጠል እንዳለባት ነው የሚያሳስቡት፡፡

ይህን የሚጋራ አስተያየት የሚሰጠው ፍትሕአወቅ በበኩሉ፣ ‹‹የብሪክስ አባል መሆናችን ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው ሊባል የሚችለው አባል በመሆናችን ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞችን አሟጦ መጠቀም የሚያስችል አቅም ስንገነባ ነው፤›› ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ ከእነ ሥጋቱ ብዙ በረከቶችን ይዞ የመጣ ዕድል መሆኑን በርካቶች እየገለጹ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 1 ቀን 2024 የሚጀምረው የኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባልነት ከሚያመጣው በረከት ለመጠቀም ምን ያህል ተዘጋጅታለች የሚለው የወቅቱ ወሳኝ ጥያቄ ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -