የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ብልጫ ያለውን የገበያ ድርሻ በመያዝ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አጠቃላይ የመድን ሽፋን መጠኑ ከ4.4 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው በመላ አገሪቱ እያቀረበ በሚገኘው አገልግሎት የመድን ሽፋን ያገኙ ንብረቶችና አገልግሎቶች 4.4 ትሪሊዮን ብር የሚገመቱ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ11.7 በመቶ ከፍ ማለቱን ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ አየር መንግድ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን መሠረተ ልማቶች፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ሜጋ ለሚባሉ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች የመድን ሽፋን ያገዙት ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ነው።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2015 ሒሳብ ዓመት በአጠቃላይ የ161,315 ውሎች ሽያጭና ዕድሳት ማከናወን መቻሉን የሚያመለክተው ሪፖርቱ፣ ይህ የሥራ አፈጻጸም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት በ31 በመቶ ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ የሰጠው የንብረትና የኢንሹራንስ ሽፋን መጠን ግን ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በተጠናቀው የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 6.9 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን የሚያመለክተው ይሄው ሪፖርት፣ ይህ አፈጻጸሙ የዕቅዱን 94.1 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያሳያል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው የዓረቦን መጠን ካለፈው በሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ የ5.4 በመቶ ወይም 354.8 ሚሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ስለመሆኑም የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
ድርጅቱ በሒሳብ ዓመቱ ካስመዘገበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 6.7 ቢሊዮን ብር ወይም 96.4 በመቶው ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተመዘገበ ሲሆን፣ ቀሪው 247.2 ሚሊዮን ብር ወይም 3.6 በመቶ ደግሞ ከረዥም ጊዜ መድን ወይም ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበ ነው፡፡ ድርጅቱ ያስመዘገበው ዓረቦን ከኢንዱስትሪው ጠቅላላ ዓረቦን ያለው የገበያ ድርሻ 30.4 በመቶ መሆኑን የሚያመለክተው የድርጅቱ ዓመታዊ ሪፖርት፣ የዓረቦን ገቢው ከዕቅድም ሆነ ካለፈው የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲገመገም አፈጻጸሙ መልካም መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አመልክተዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን የድርጅቱ የዓረቦን ገቢ ከዚህ በላይ እንዳይሆን የተለያዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ማድረጋቸውን አቶ ነፃነት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የዓረቦን ገቢውን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ እንዳይቻል ካደረጉ ተግዳሮቶች መካከል በዋናነት የጠቀሱት የአቪዬሽን የመድን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስን ነው፡፡
እንደ አቶ ነፃነት ገለጻ፣ የአቪዬሺን የመድን ሽፋን ካለፈው ሒሳብ ዓመት የ716.9 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከዕቅዱ ደግሞ የ714.7 ሚሊዮን ብር ቅናሽ በማሳየቱ የዓረቦን ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡
በአቪዬሽን ዘርፍ ድርጅቱ ሲያገኝ የነበረው የዓረቦን ገቢ የቀነሰበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የተጎዳ በመሆኑ ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት የአቪዬሽን መድን የዓረቦን ምጣኔ (Premium Rate) በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ በድርጅቱ አፈጻጸም ላይ ጉዳት ማድረሱን የዋና ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ ይህ ተግዳሮት ባይኖር ኖሮ የድርጅቱ የዓረቦን ገቢ የሚያድግበት መጠንም ሆነ የገበያ ድርሻ ከዚህ እጅግ ይልቅ እንደነበር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
በ2015 የሒሳብ ዓመት ከቀደሙት ዓመታት በተለይ በአቪዬሽን የመድን ሽፋን የታየውን ቅናሽ በተመለከተ አቶ ነፃነት ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በቀደሙት ሁለት ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ስለደረሰበትና ከዚሁ ምክንያት የዘርፉ እንቅስቃሴ ተገድቦ በመቆየቱ፣ የመድን ሽፋን ሰጪ ኩባንያዎችም ይህንን ያገናዘበ የዓረቦን ቅናሽ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአቪዬሸን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሆነ የዓረቦን ቅናሽ በማድረጉ፣ ከዘርፉ ያገኝ የነበረው የዓረቦን ገቢው ዝቅ እያለ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይከፍል የነበረው ዓረቦን ላይ ቅናሽ የተደረገለት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከዘርፉ ያገኝ የነበው ዓረቦን ከዓምናው ከ717 ሚሊዮን ብር በላይ መቀነሱን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2013 ከአቪዬሽን የመድን ሽፋን አሰባስቦት የነበረው የዓረቦን ገቢ 2.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2014 ደግሞ ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር ዝቅ ብሏል፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ደግሞ ከዓምነው በግማሽ መቀነሱን (ወደ 700 ሚሊዮን ብር መውረዱን) ጠቅሰዋል፡፡ በተያዘው 2016 የሒሳብ ዓመት ግን ከአቪዬሽን የሚገኘው ገቢ እንደሚጨምር ተስፋ አድርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አየር መንገዶች በአብዛኛው ወደ መደበኛው ሥራቸው በመግባታቸው፣ የተጓዦች እንቅስቃሴም በመጨመሩ፣ የአውሮፕላኖች በረራና ሥምሪታቸው በማደጉና መዳረሻቸው በመጨመሩ እንዲሁም የአውሮፕላኖች ምርት ዕድገት ማሳየት በመጀመሩ ከአቪዬሽን የሚገኘው ዓረቦን በመላው ዓለም ይጨምራል ተብሎ እንደሚገመት አቶ ነፃነት አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በተለይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኝ የነበረው ዓረቦንም የአየር መንገዱ እንቅስቃሴ ከመጨመሩ አኳያ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ቀጣይ ዓመት ዕቅድን በተመለከተ አቶ ነፃነት ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ ከዓረቦን ገቢ አሰባሰብ አንፃር በ2016 የሒሳብ ዓመት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ለማግኘት ተቅዷል፡፡ ይህ ዕቅድ አገሪቱ ውስጥ የታዩ ግጭቶች ወደ ሰላም ይመለሳሉ ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
‹‹ሁሉም ቦታ እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን ልንሠራ እንችላለን ብለን እናስባለን፤›› ያሉት አቶ ነፃነት፣ ከዚህ ጎን ለጎን ሌሎች በርካታ የሪፎርም ሥራዎች የሚከናወን በመሆኑ ዕቅዳቸው ይሳካል ብለው ያምናሉ፡፡
የጉዳት ካሳ ክፍያን በተመለከተ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ ድርጅቱ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የከፈለው አጠቃላይ ካሳ ከቀዳሚው ዓመት ያነሰ ነው፡፡ በደንበኞች ንብረትና ሕይወት ላይ ለደረሰ አደጋ፣ እንዲሁም ከሕጋዊ ኃላፊነት ጋር ለተያያዙ የካሳ ጥያቄዎች እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በአጠቃላይ 3.5 ቢሊዮን ብር ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ ይህ የካሳ ክፍያ መጠን ከዕቅዱ የ9.3 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ነው፡፡ ከባለፈው የሒሳብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ36.4 በመቶ ያነሰ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ከተከፈለው የካሳ ክፍያ ውስጥ የጠቅላላ መድን ድርሻ 3.4 ቢሊዮን ብር ወይም 97.1 በመቶ ሲሆን፣ የረዥም ጊዜ መድን ዘርፍ 98.8 ሚሊዮን ብር ወይም 2.9 በመቶ ድርሻ እንደነበረውም ታውቋል፡፡
ድርጀቱ ከኢንቨስትመንትና ከሌሎች ገቢዎች ማለትም ከወለድ፣ ከሕንፃ ኪራይና 603.4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ሪፖርቱ ያመለክታል። ይህም ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር የ5.2 ሚሊዮን ብር ወይም 0.8 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ ካለፈው ሒሳብ ዓመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ75.1 ሚሊዮን ብር ወይም 14.2 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የትርፍ ምጠን አሁንም በኢንዱስትሪው ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ እንዲቀጥል አስችሎታል። አቶ ነፃነት በሪፖርታቸው እንዳሠፈሩት፣ ድርጅታቸው በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የዘጠኝ በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፣ ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር ግን በ0.1 በመቶ ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ ድርጅቱ በሒሳብ ዓመቱ አስመዝግቤዋለሁ ያላቸው ውጤቶች እንደ መልካም የሚታዩ ናቸው ቢባልም፣ ውጤቱ የተገኘው ግን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ታልፎ እንደሆነ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡
አቶ ነፃነት በበጀት ዓመቱ ድርጅቱን ገጥመውት ነበር ካሏቸው ተግዳሮቶች መካከል በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የሚስተዋለው አለመረጋጋት ዋነኛው ነው። በእነዚህ አለመረጋጋቶች ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በሰሜኑ የጦርነቱ ቀጣና አካባቢ የሚገኙ ቅርንጫፋቸው በበቂ ሁኔታ ሥራ ለመሥራት ያለመቻላቸውም የበለጠ ውጤት እንዳይገኝ ጋሬጣ መፍጠሩን አስታውሰዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ከዩክሬንና ከሩሲያ ጦርነት ጋርና ከዓለም አቀፍ ደረጃ ከታየው የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ የመለዋወጫ ዋጋና የጥገና ወጪ መናር፣ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደፈጠረም ጠቅሰዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወቅታዊ የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴና የፖሊሲ ለውጦች አንፃር ድርጅቱ አዲስ ስትራቴጂ እንዲቀርፅ ያስገደደው ስለመሆኑ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ እንደብራሩት፣ ከዚህ ቀደም ድርጅታቸው ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካትና የተቋቋመበትን ተልዕኮ ለመወጣት የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቀየስና ግቦችን በመጣል ለተግባራዊነታቸው ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ባለፉት ዓመታት የተጠናቀቁት የስትራቴጂካዊ ዕቅዶቻቸው ለውጭ ገበያው ዝግ የነበረውን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የአገር ውስጥ ገበያ ውድድር መነሻ አድርገው የነበሩ በመሆናቸው ስትራቴጂውን መከለስ አስገድዶታል፡፡
አሁን ላይ ከቀድሞ የተለየ ፖሊሲ በመቅረፁ ድርጅቱም ከዚህ ጋር የሚጣጣም አዲስ ስትራቴጂክ ቀርፆ ለውድድር ስለመዘጋጀቱ አመልክተዋል፡፡ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ገበያ ክፍት ሊያደርግ የሚችልባቸው የሪፎርም ሥራዎች የሚጠበቁ በመሆኑ ስትራቴጂ ዕቅዱ ይህንኑ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በአፍሪካ እየተፈጠሩ ያሉት ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የሚፈጥሩትን ዕድሎችና ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተግዳሮቶች ግምት ውስጥ ያስገባ ሥልታዊ ዕቅድ ማዘጋጀት የግድ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሥልታዊ ላሉት ዕቅድ ቢጋር የተዘጋጀና በየደረጃው ለሚሳተፉ አካላት በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ የሥልጠና፣ የልምድ ልውውጥና ሙያዊ ድጋፎችን ከአገር ውስጥና ከውጭ አጋር አካላት ጋር በማመቻቸት ወደ ሥራ እየተገባ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ብቸኛው የመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የካፒታል መጠኑ ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በመላ አገሪቱ ያሉትን ቅርንጫፎች 108 አድርሷል፡፡