Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትካላዳላሁ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ነገር አለ እንዴ?

ካላዳላሁ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ነገር አለ እንዴ?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ከጁላይ 20 እስከ ኦውገስት 20 የተካሄው የ2023 የሴቶች የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር በሚከናነውበት ጊዜ ውስጥ ከዕለታት በአንድ ቀን፣ ሲኤንኤን ወርልድ ስፖርት ፕሮግራም ላይ አንድ የሴት አጫዋች (ሪፌሪ) የፕሮግራሙ አዘጋጅ እንዳለው የራሷን ታሪክ በገዛ ራሷ ቃል ስትተርክ ሰማሁ፡፡ ‹‹ቶሬ ፔንሶ እባላለሁ፣ ፕሮፌሽናል ሪፌሪ ነኝ፣ የፊፋ ሪፌሪ ነኝ፡፡ የዓለም ዋንጫ ሪፌሪ ነኝ፡፡ በዚህ ታላቅ ግዙፍ መድረክ በዓመቱ ታላቅ ስፖርታዊ ሁነት ላይ አገርን እንድወክል ስመረጥ በጣም ደስ ብሎኛል፣ ደስታውንም አልችለውም፣ … ከ14 ዓመቴ ጀምሮ ለዚህ ስሠራ ኖሬያለሁ፣ ብዙ ደፋ ቀና ነው፣ መዓት ውጣ ውረድ ነው፣ የጨዋታው ባለሥልጣናት ናቸው አውስትራሊያ ኒውዚላንድ የጨዋታ ሜዳ ላይ አገሬን ወክዬ እንድቆም ያስቻሉኝ፤›› አለች፡፡ የአገራችን የስፖርት፣ በተለይም  የእግር ኳስ ቋንቋ እንደሚለው አርቢተር ቶሪ ፔንሶ (በነገራችን ላይ አርቢትር ወይ አልቢትር በመዝገበ ቃላት ትርጉሙ አጫዋች ነው) ለሲኤንኤን የተናገረችውንና እኔም ድንገት እንደ አጋጣሚ የሰማሁትን፣ በተለይም የአገር ውክልናውን ነገር እንዳለ ማመን አቃተኝ፡፡ አገሬን ወክዬ አጫዋች/አርቢትር መሆኔ ያለችውን፣ አለችው ያልኩትን ተጠራጠርኩ፡፡ ጆሮዬን አላምነው አልኩ፡፡ በአገራችን የሚዲያ ቋንቋ እንኳንስ ዓለም ዋንጫን የመሰለ ነገር ላይ ይቅርና ግለሰቦች በሚወዳደሩበት ተራ ፍልሚያ ዓይነት ሪያሊቲ ሾውም ላይ ሳይቀር፣ ኢትዮጵያን ወክለው/ወክላ፣ ወክሎ ሲባል እሰማለሁና የዚህ ስሜት አታልሎኝ፣ አርቢትሯ ያለች መስሎኝ እንዳይሆን ብዬ በትክክል መስማቴን ተጠራጠርኩት፡፡ ስለዚህም በአንድ ጊዜ ስሚ/መስማት ብቻ ጆሮዬን ማመን አልፈለግሁም፡፡ በዚህ ምክንያት የሲኤንኤንን ወርልድ ስፖርት መፈለግ ነበረብኝ፡፡ ዕድሜ ለደረስንበት የቴክኖሎጂ የዕድገት ደረጃ እንጂ (ያም ቢሆን ልፋቱ ቀላል አልነበረም) የተባለውን ዲጂታል ሰነድ ራሱን አገኘሁት፡፡ ደጋግሜም ሰማሁት፡፡ ልክ ነኝ፣ አርቢተር ቶሪ ፔንሶ አገሬን ወክዬ፣ አሜሪካን ወክዬ ማለቷን መስማቴ እውነት ነው፡፡

እዚህ ‹ልፋቴ› ውስጥ ሁለት ነገሮች ልብ እንዲባሉልኝ እፈልጋለሁ፡፡ አንባቢዎቼ ፈቃዳቸውና ደንታቸው ከሆነ አንደኛው ልብ እንዲሉልኝና እንዲመዘግቡልኝ የምፈልገው፣ ብላለች አላለችም ብዬ ማጣራቴንና ማረጋገጤን ነው፡፡ እንኳን በሚዲያ ብዙ ሰው በሚሰማውና ለሕዝብ በሚነገር በሕዝብ ጉዳይ ባለበት ጉዳይ ለግለሰብም የሚነገር ያልተጣራ አሉ፣ አሉ  ነው፣ አሉባልታ ነው፣ ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ነው፡፡ እና ይህንን አደጋ ለመከላከል፣ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ጆሮዬን ተጠራጠርኩት፣ ሞገትኩትም፡፡ ያንን ዝግጅት ሂድና ፈልገው፣ እንደገና ስማው አልኩት፡፡ እንዳልኩትም አድርገን አረጋገጥን፡፡ አሁን የሲኤንኤን ወርልድ ስፖርት የዚያ ቀን የአርቢትሯ ቃለ ምልልስ በእጄ አለ፣ ከእነ ትራንስክሪፕቱ፡፡ ስለዚህም አንድ የድሮ፣ የጥንት የአገራችንን ሕግ ቋንቋ ለመጠቀም ‹‹…ነገር እየፈጠርህ ያልሆነ ወሬ ታወራለህ… አየሁ ብሎ የማይመሰክሩበትን ሐሰት ነገር አውርቶ የተገኘ እንደሆነ… ቅጣት ይፈጸምበታል›› እንዳልባል፣ ራሴን ከአደጋ ለማዳን ብቻ ሳይሆን የመናገር፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሚጠይቀውን ኃላፊነትና ጨዋነት የመወጣት ጉዳይ ግዴታ እንጂ የቢሻኝ ጉዳይ አለመሆኑ የዚህ ሙያና የዚህ ነፃነት የጥበብ መጀመርያ ነው፡፡

ሌላም ልብ አድርጉልኝ ያልኩት ሁለተኛ ጉዳይ አለ፡፡ የመጀመርያውና አንደኛው ከዚህ በላይ የገለጽኩት ነው፡፡ እሱም ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ‹‹ሳያጣሩ ወሬ ሳይገድሉ ጎፈሬ›› ተብሎ የሚቋጨው ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው አሜሪካም ውስጥ፣ የፊፋ አርቢትርም ዘንድ እንደተገለጸውና እንደሚታመንበት አገሬን ወክዬ አጫውታለሁ፣ አሜሪካን ወክዬ አጫውታለሁ ማለት በጣም አደገኛ መሆኑን ማሳየት፣ ቢያንስ ቢያንስ ልክ አለመሆኑን ማሳጣት ነው፡፡ የዚህም አቻና አጫፋሪ የሆነ የተጫዋቾች/የአትሌቶች የተሳሳተ፣ አቅጣጫ የሳተ ‹‹የውክልና›› ዕሳቤም አለ፡፡

እነዚህን አንድ በአንድና በተራ ለማስረዳት ልሞክር፡፡ ዳኛዋ ወይም ሪፌሪዋ ያንን ሁሉ ብላ የፊፋ ሪፌሪ ነኝ፣ ፕሮፌሽናል ሪፌሪ ነኝ፣ ኢንተርናሽናል አጫዋች ነኝ ብላ እውነቱንና አቅጩን አሳምራ የገለጸችውን ያህል አገሬን ወክዬ ስትል ግን ሁሉን ነገር አበላሸችው፡፡ በተለይም ዳኝነት የውክልና ሥራ አይደለም፡፡ የአደራ፣ የተልዕኮ፣ የመልዕክተኛ ሥራ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉንም ዓይነት ዳኝነት፣ ጨዋታን የመዳኘትም ሆነ ሌላውን ይገዛል፡፡ ዳኝነት የየትኛውም ወገን የውክልና ሥራ አይደለም፡፡ ዳኝነት የ‹የእግዜር ነው› እንዲሉ ገለልተኛነትን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ ፊፋ የሚከተለውና የሚገዛበት፣ የዓለም ዋንጫ አጫዋቾችን የሚመርጥበት ባለብዙ ደረጃ አሠራርና ሥርዓት አለው፡፡ እዚህ ውስጥ ብሔራዊ የእግር ኳስ ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች ዳኞችን መልምሎ የማቅረብ ሚናና ድርሻ አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢ ኮታ የሚባል ነገር አለ፡፡ የዚህ ዓላማ እያንዳንዱ አካባቢ/አኅጉር ወይም አገር ወኪሉን እንዲልክ ሳይሆን፣ አጫዋችነት መላውን ዓለም እንዲመስል ለማድረግ ነው፡፡ በአጠቃላይ እዚህም ያለው ዳኝነት ነውና ኢአድሏዊነትን ወይም ገለልተኝነትን ለመመሰል ዓይኗን እንደተጋረደቸው ሴት፣ የፊፋ ዳኞች ለአኅጉርም ሆነ ለአገር አድልኦ ዓይናቸውን የተጋረደ ሆኖ፣ የሁሉም አለኝታ ተደርገው ለመታየት የበቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ረዥም ጊዜ በሚወስድ ምርጫ ሒደት ውስጥ ያልፋሉ፡፡

ገለልተኛ ዳኝነትን የማረጋገጥ አንዱ ቀዳሚ ቁም ነገር ከሁሉ በፊት እዚህ ጨዋታ፣ እዚህ ስፖርትም ውስጥ ያለው የዳኝነት ሥራ የማንም ወገን፣ የማንም ተከራካሪ/ተጫዋች ወገን አለመሆኑን፣ ይልቁንም ከዚያ ውጪና በተቃራኒ የነፃ ገለልተኛ አካል መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ በምንነጋገርበት ጉዳይ ላይ ዳኝነት የፊፋ ነው፣ የአሜሪካ አይደለም፣ ወይም ዳኛዋ የተመረጠችበት የዜግነት አገር መንግሥትም የስፖርት ፌዴሬሽንም አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው አሜሪካዊቷ አርቢትር ቶሪ ፔንሶ ሳትቀር፣ እሷም ጭምር ለዚያውም ፕሮፌሽናል ሪፈሪ ነኝ፣ የፊፋ ሪፈሪ ነኝ፣ የዓለም ዋንጫ ሪፈሪ ነኝ እያለች ‹‹…አገሬን ወክዬ›› ስትል ክው ያልኩት፡፡ ‹‹አገሬን ወክዬ…›› ያለችው አርቢትሯ ሳትሆን የእግር ኳስ ተጨዋች ብትሆን ጉዳዩ ላይ ልዩነት አለው፡፡ እዚያም ውስጥ ቢሆን ‹‹ውክልና››ው የግለሰብ አይደለም፡፡ የቲሙ/የስኳዱ ነው የሚል ‹‹የቁንጫ ሌጦ የማውጣት›› የሚመስል ምላሽ አለው፡፡

ይህ አገሬን ወክዬ ዳኛ በመሆኔ ተደስቻለሁ የኦርቢትሯ ቃል ይህንን ያህል ክው ያደረገኝ፣ የከነከነኝ፣ ያመመኝ፣ ምናልባትም በተለየ ሁኔታ አገሬ ውስጥ ይህ ጉዳይ ከሕመም በላይ የአገር ህልውና አደጋ እስከመሆን ድረስ ሥር የሰደደ ችግር በመሆኑ ነው፡፡ ይህ 30 ዓመት በላይ የሆነው ችግራችን የተፈጠረው ከዚያ በፊት የነበረውን የአገር ሕመም ያድን ዘንድ ከታዘዘልን ‹‹መድኃኒት›› ነው (ዝርዝሩ ውስጥ አልገባም)፡፡ እዚህ አዲሱ የክፍልፋይነት የጎጆኝነት ሕመምና በሸታ ውስጥ ሳንገባ በፊት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን በመላው ዓለም ጭምር፣ በተለይ በኢትዮጵያ ደግሞ ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኤምፔሪያሊስት ትግል በሚካሄድበት ወቅት የእኩልነት የመብት፣ የነፃነት፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የሁሉም የጋራ አካፋይ ነበሩ፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ በአጋጣሚ በተለይ በ1964 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ መጨረሻ ሳምንት ድረስ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሲቪል ሰርቨስ ሥርዓትና ፖለቲካ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ኢትዮጵዊ ስም ርዕሰ ዜና ነበር፣ እንዳልካቸው መኮንን፡፡ እንዳልካቸው መኮንን ከፍተኛ ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ እንዲሁም በንጉሡ ዘመን መዳረሻ ላይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ወታደራዊው መንግሥት በ1967 ዓ.ም. ኅዳር ወር ውስጥ በጅምላ ከገደላቸው ስድሳዎቹ መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በ1964 ዓ.ም. በተጠቀሰው ጊዜ የእንዳልካቸው መኮንን ስም እንደ ነገሩ በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ገንኖ የተሰማው ግን ከአገር ፖለቲካ ውጪ በሆነ ምክንያትና ጉዳይ ነው፡፡

ከኡ ታንት ቀጥሎ ያሉትን ማለትም ኡ ታንትን የሚተኩትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለመምረጥ በሚደረገው የምርጫ ሥርዓት ውስጥ እንዳልካቸው መኮንን ተወዳዳሪ ዕጩ ሆነው ቀርበው ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ምንያት የእንዳልካቸው ስም በአገራችን በኢትዮጵያም የያኔው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሚያስተናግደውና በሚፈቅደው ልክ፣ በውጭ አገር ደግሞ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ዜና ነበር፡፡ አራተኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት ግን ኢትዮጵያዊው እንዳልካቸው መኮንን ሳይሆኑ ኦስትሪያዊው ኩርት ቫልድሃይም ነበሩ፡፡ እንዳልካቸው መኮንን ቢመረጡ ኖሮ፣ አሁን እንደለመደብን ኢትዮጵያን ወክለው የተመረጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ እንል ነበር? ኦስትሪያውያን ቫልድሃይምን አገራቸውን የወከሉ ዋና ጸሐፊ ይላሉ? ዛሬ የተመድ ዋና ጸሐፊ ጉተሬስ  ናቸው፣ የፖርቹጋል ዜጋ ናቸው፡፡ ‹‹ፖርቹጋልን ወክለው›› መባል ቀርቶ የዋና ጸሐፊነታቸው ሥራ ከፖርቹጋል፣ ከአኅጉሪቱ ከአውሮፓም ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውም፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊነትና በአጠቃላይ ተመድን የማገረው ዓለም አቀፋዊ ሲቪል ሰርቪስ ጉዳይ የድርጅቱን ሥራ የሚሠሩ ገለልተኛና ፕሮፌሽናል ሠራተኛውና የሰው ኃይል የመቅጠርና የማስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡

የእኛ አገር ፖለቲካና ሁለመናችን ግን፣ እንዲያውም ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ጭምር ገና፣ ገና ነፃና ገለልተኛ የሚባል ነገር ስለማይታወቅ ኩርት ቫልድሃይምም ሆኑ እንዳልካቸው መኮንን የማንም አገር ውክልና የላቸውም፣ ኢንተርናሽናል ሲቪል ሰርቫንት ናቸው ብሎ ምሳሌ ማቅረብና ማስረዳት የማይቻለውን ነገር መሞከር ነው፡፡ አገራችን መንግሥታዊ አውታራትን (እነሱን ብቻ ሳይሆን የወንድ፣ የሴት፣ የሙያ፣ የስፖርት፣ የሲቪክ ማኅበራትን ጭምር) ከገዥው ፓርቲ ወይም ከገዥው ቡድን፣ ወይም ከገዥው ግለሰብ መለየት እስኪሳነን ድረስ የአንድ ቡድን/ፓርቲ አገዛዝ ተንሰራፍቶ ስለኖረ ዳኞች፣ ሲቪል ሰርቫንቶች ወይም የመንግሥት ሠራተኞች ነፃና ገለልተኛ ናቸው ብሎ መናገር ‹ይህ ሰው ጤነኛ ነው?› ያሰኛል፡፡ የእኛ አገር ነገር ደግሞ የተለየ ነው፡፡ ስለገለልተኛነት፣ ስለነፃነት መናገር በጭራሽ አልተለመደም፡፡ ይህ የሆነው ሲጀመር ‹የጠቅል አሽከር› ብለን ስለጀመርን አይደለም፡፡ ይህንንም እያሉ፣ ማለትም ለአገሪቱ ወኪል (በአገር ውስጥም በውጭም) እየማሉ፣ የእሱ አሽከር/ሠራተኛ ነን እያሉ በዚያ ማዕቀፍ ውስጥ አዛዥ፣ ሕግና ደንብ ብቻ ነው፣ ማንም አያዘኝም ማለት ይቻላል፣ ይገባልም፣ ደንቡም ይህ ነው፡፡ እንጂማ የመንግሥት ሠራተኛ ማለት መንግሥት የሚለውን የሚሠራ ነው፡፡ መንግሥት የሚፈልገውን የሚልበት መንገድ ደግሞ ሕግ ነው፡፡ ስለነፃነት ስንናገር የመንግሥት ሠራተኞች አስቀድሞ የተሠራ/የወጣ ሕግ ያለውን፣ የመንግሥትን ፍላጎት ለምን ያስፈጽማሉ፣ ማስፈጸም የለባቸውም እያልን አይደለም፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ ትዕዛዞችና ተፅዕኖዎች አሉ፡፡ ከእነሱ መጠበቅ ከእነሱ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡

ለምሳሌ በአዋጅ ቁጥር 1148/2011 የተቋቋመ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የሚባል ተቋም አለ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በታች ሌላም ሚኒስቴር ‹‹አለበት››፡፡ ግን በተቋቋመበት አዋጅ/ሕግ እንደተገለጸው፣ ‹‹ራሱን የቻለ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያስችል ነፃና ገለልተኛ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት …›› ነው፡፡ ሕጉ ስለነፃ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በ‹‹ማስተዋወቅ›› እና በማቋቋም ላይ ብቻ ይበቃኛል አላለም፡፡ ከዚህ ቀደም ባልነበረና ባልተለመደ ሁኔታ ‹‹ነፃና ገለልተኛ›› ማለት በሕግ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹በአሠራር ተለይቶ የተቋቋመ… የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ከማንኛውም ወገን ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚፈጽምና ውሳኔ የሚሰጥ የመንግሥት ተቋም ነው››፡፡ ይህ ማለት ነፃና ገለልተኛ ስለተባለ የመንግሥት መሆኑ ቀረ፣ የመንግሥት ሕግ አይገዛውም ማለት አይደለም፡፡ ዋናው የዓይን ብርሃንና የእግሩ መንገድ እንዲያውም ሕግ ነው፡፡ ሕግና ሕግ ብቻ ነው፡፡ ሕግም ሲወጣ ሕግን ተከትሎ በሕግ ብቻ ነው፡፡ ሠራተኛው ላይ፣ የሰው ኃይሉ ላይ (ከመንግሥት ተቋማት የሚመጡ አራት፣ ከግሉ ዘርፍና ከትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚመረጡትን ሦስት፣ በድምሩ ሰባት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የባለሥልጣኑን ዳይሬክተሮችና ሌሎች ሠራተኞች ጨምሮ) እዚህ ሰው ኃይል ላይ ለጊዜው ላተኩር፡፡

ተቋሙ ወይም ባለሥልጣኑ ነፃና ገለልተኛ ነው ማለት ሠራተኛውና አመራሩን የመንግሥት ሕግ ‹‹አይመለከተውም›› ማለት አይደለም፡፡ ለሕግ መገዛትማ ሕጉን ለሚያወጣውም የመንግሥት የሥልጣን አካል ጭምር ዋነኛው የጥበብ መጀመርያ ነው፡፡ ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ ነው፣ ከሕግ በስተቀር በሌላ አይገዛም ማለት እዚህ ውስጥ ‹‹ሕግ›› ነኝ ብሎ ሕግን ተገን አድርጎ፣ ሕግ መስሎ የሚመጣ ሌላ ጣጣ ስላለ ነው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር፣ የሥራ አመራር ቦርዱ ሊቀመንበር ይህንን አድርጉ አታድርጉ ማለት አይችሉም፡፡ ድንገት ማለት እንችላለን የሚል ቢኖር ደግሞ የሠራተኞች አቀጣጠር/የአመራሮች አመዳደብና አሿሿም ይህንን መከላከል፣ የሚያነውር ሆኖ መሠራት አለበት፡፡ ለምሳሌ አድርጉ የተባሉትን ለማድረግም ሆነ አስቀድሞ አድርጉ የሚል እንዳይኖር ዝም ብሎ እበላ ባዮች የሚሰባሰቡበት ወይም የሚግበሰበሱብ ቦታ አይደረግም፡፡ ወይም የትኛውም የተመደበው፣ የተቀመጠው ሰው ከመጣበት ከመነጨበት ‹‹ማንነት›› ወይም ‹‹ላከኝ›› ከሚለው ሰው ዓላማ ተነስቶ የእከሌ ወኪል ነኝ እንዳይል ሥርዓት ይበጃል፣ ሥርዓት አለ ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ እነዚህ ሰባት ሰዎች መነሻ ምንጫቸውን፣ የተመለመሉበት መድረክ ምክንያት አድርገው አሁን ለምሳሌ ‹‹እኔ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ወኪል ነኝ››፣ ‹‹እኔ የሚትሱቢሺ ኢትዮጵያ ወኪል ነኝ››፣ ‹‹እኔ የጤና ጥበቃ ወኪል ነኝ››፣ ወዘተ›› ቢሉ መሳቂያ ማፈሪያ ይሆናሉ፡፡ የሰው ኃይሉ እንዳስፈለገው እንዳይሆን፣ ዝም ብሎ ተነስቶም ሆነ ይህ ነው ምኞቴ ብሎ የዚህ ወይም የዚያ ‹‹ወኪል› ነኝ እንዳይል፣ ወይም እንደሚፈለገው እንዳይታገዝ የሚያደርገው ነፃና ገለልተኛ ነህ ስለተባለ ብቻ አይደለም፡፡ አዎ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ መጀመርያውም እሱ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ፖሊቲካውም ይህንን እንዲያግዝ ተደርጎ መበጃጀት አለበት፡፡ የአዕምሮ አጠባው፣ መልከ ብዙው የደኅንነት ዓይንና ጆሮ፣ የእንጀራ ገመዱ ሁሉ እዚህ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ማደራጀት ተግባር ውስጥ ከቁጥር መግባት አለባቸው፡፡

አሜሪካ በምትባል አገር ውስጥ እግር ኳስ አጫዋችነት ውስጥ ሳይቀር እንደ ዋዛም ቢሆን ኮርቶ ሲነገር የሰማነው፣ ‹‹አገሬን ወክዬ›› ባይነት በኢትዮጵያ ሁኔታ ምን ዓይነት አደገኛነትና ጭራቅነት አግኝቶ ምን መስሎ እንደነበር በ2013 ዓ.ም. የውስጥ ወረራ ወቅትና ከዚያ ጀምሮ እስኪበቃን ድረስ ዓይተነዋል፡፡ በተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ሥርዓት ውስጥ መላውን የሰው ልጅን በሙሉ ያለ አድልኦ የሚያገለግል ተቋም/ድርጀት የሥራ ተልዕኮ በሥራ ውል/በቅጥር የተቀበለ ወይም ተቀበልኩ ያለ ሰው ለአገሬ አይደለም፣ ለጎራዬ፣ ለጎጥ ለመንደሬ ካላደላሁ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ፣ ከዚህ ዕሳቤ መላቀቅ/መጀመርያም ነፃ መውጣት የሥራ ውሉ ህልውና ዋናው መሠረት መሆኑን ረስቶ አገሩ ላይ ሲተኩስ ዓይተናል፡፡ ከዚያ በመለስ ባለ የሥራ ቦታ ኢንፎርሜሽን የማሠራጨት፣ እውነት የመናገር፣ ሕዝብ የማሳወቅ ተልዕኮ ባለው ትንሽም ትልቅም፣ የውጭ አገርም የአገር ውስጥም የሥራ ድርሻ የተቀበሉ ሰዎች ለተቋሙ ዓላማ መታመን አቅቷቸው በአገርም በቀጣሪ ተቋማቸውም ላይ ክህደት ሲፈጽሙ ዓይተናል፡፡

የአሜሪካዊቷ አርቢትር (የእግር ኳስ  አጫዋች/ዳኛ) አገሬን አሜሪካን ወክዬ ለአጫዋችነት በመመረጤ ደስ ብሎኛል ያለችበት አጋጣሚና ንግግሯም የዚህ ጽሑፍ መነሻ እንደሆነ ገልጫለሁ፡፡ ደግሜ ደጋግሜም የአጫዋችነት ሥልጣን የአሜሪካም፣ የማንም አገር እንዳልሆነ፣ የዳኝነት ሥልጣን የፊፋ እንደሆነ አመላክቻለሁ፡፡ የዳኝነት ሥልጣን የማንም አገር አለመሆኑን፣ እንዳይሆንም ለማረጋገጥና የፊፋ ብቻ ለመሆኑ መተማመኛም ለመስጠት አሜሪካ ተጫዋች በሆነችበት ግጥሚያ ‹‹ድንገት›› ይህች አርቢትር ዳኛ እንዳትሆን የሚከላከል ሕግ አለ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊነት የሥራ ድርሻ ክፍት ቦታ የሚሞላው በምርጫና በቅጥር ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ዕጩዎችን ያቀርባል፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ዋና ጸሐፊውን ይመርጣል፡፡ እዚህ ሥራና ሥርዓት ውስጥ ኢንተርናሽናል ሲቪል ሰርቫንትነትን ረስቶ፣ የዚህን ትርጉም ዘንግቶና ከእነ ጭራሹም አላውቅም ብሎ የአገሬ/የመንደሬ ‹‹ወኪል›› ነገረ ፈጅ ነኝ የሚል ጉድ እንዳይመጣና እንዳይፈላ የመጨረሻው መጠበቂያ (በተቋቋመ አሠራር መሠረት) የዋና ጸሐፊነት ሥራ ለየትኛውም የአምስቱ ቋሚ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገሮች ዜጋ የማይሰጥ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹አገሬን ወክዬ›› ዳኛ ሆኛለሁ ብሎ ነገር ዓይን አውጥቶ፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ አሜሪካ እጅ እንዳይገባ ለመከላከል ነው፡፡

በአገራችን ሁኔታ ችግራችንና ጣጣችን ብዙ ነው፡፡ የጠቀስኩት ዓይነት የቋንቋ አጠቃቀማችን ዘርግፎ የሚሳየው ይህንን ነው፡፡ ማከናወን፣ መሥራትና መፈጸም ካለብን ተግባር አኳያ ችግራችን፣ ‹መከራ››ችን፣ ‹‹ፍዳ››ችን ገና ብዙ ነው፡፡ ከ60ዎቹ ወዲህ ሲደድር የኖረውን የጠላትነት ፖለቲካ ገና አላፈረስንም፡፡ ለማንምና ለየትኛውም ወገን ወይም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል የመንግሥት አውታር የማነፅ ሥራ ውስጥ ብንገባም፣ ይህ ግዳጅ ይህ አደራ የሁሉንም የጋራ መግባባት አላገኘም፡፡ ይህንን ሁሉ ሳናሳካ፣ መጀመርያ ይህ ሁሉ መከናወኑን ሳያረጋግጥ ነው ሌላ ጣጣ፣ ሌላ ቀውስ የሚፈጥር ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያና ራስን በራስ የማስተዳደርን አገራዊ አሸናሸን ለውጥ ውስጥ ካልገባን የምንለው፡፡ እዚህ ውስጥ ለመግባት መጀመርያ ዴሞክራሲን ማደላደል ያስፈልጋል፡፡ ወደ ተነሳንበት ዋና ነገር ስመለስ ይህንን ሁሉ አሳክተናል ብንል እንኳን፣ ማለትም የጠላትነት ፖለቲካን አፍርሰናል፣ ገለልተኛ አውታረ መንግሥትም የማቋቋምና የማነፅ ሥራ ውስጥም ገብተናል፣ የዚህም ‹‹ምስክርነት›› አግኝተናል ብንልም እንኳን በተመደቡበት ቦታ፣ በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ፖለቲካዊ ዝንባሌን፣ ብሔረሰባዊ  ሠፈርን፣ ሌላም ሌላም ዓይነት ዝንባሌ በልጦ፣ ተሻግሮ እስኪፀና ድረስ ለምሳሌ የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የፖሊስ አባላት፣ የዳኞች፣ የዓቃቢያነ ሕጎች፣ ወዘተ ከፓርቲ አባልነት መከልከል ባለፈ፣ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ተሳትፎ የተገለሉ እንዲሆኑ በሕግ መገደብ፣ ፈልገውም ወገናዊ ከሆነ አመለካከት ነፃ ለመሆን እንዲጣጣሩ ማሳመን ሳያስፈልግ ይቀራል? ቋንቋችን ውስጥ ገብቼ አገሬን ወክዬ ዳኛ ሆንኩ ማለትን መሞገት ያስፈለገኝ በዚህ መነሻና ምክንያት ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...