Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ በቂ አይደለም

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ በቂ አይደለም

ቀን:

ከዚህ ቀደም በጋዜጦችና በመጽሔቶች ለንባብ ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ከኢኮኖሚ ሊቃውንትና ባለሙያዎች ባሻገርም፣ ቭላዲሚር ሌኒንና ሮናልድ ሬጋንን የመሳሰሉ የሶቭየት ኅብረትና የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችም የዋጋ ንረት የሰይጣኖች ሁሉ ሰይጣንና ሰው ገዳይ ነው ብለው እንደ መሰከሩ መግለጼን አስታውሳለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ስለዋጋ ንረት ያልተጮኸበት ጊዜ የለም፡፡ የሕዝቡ ጩኸት በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይም ተጋብቶ ከመደበቅ ተላቀው፣ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ እንዳሉ እየነገሩን ይገኛሉ፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ፖሊሲዎቹን በመደገፍና በመንቀፍ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም. በጀትን ባስፀደቀበት ወቅት ስለፊስካል ፖሊሲው ገለጻ አድርጎ ከባለሙያዎች ድጋፍና ነቀፋ አስተናግዷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን የዋጋ ንረትን በ2016 ዓ.ም. ወደ ሃያ በመቶ እና በ2017 ዓ.ም. ወደ አሥር በመቶ ዝቅ ላደርግ ነው ያለበትን ፖሊሲ አስተዋውቋል፡፡ ይህም ከኢኮኖሚ ባለሙያዎች ድጋፍንም ነቀፌታንም አስተናግዷል፣ የመገናኛ ብዙኃንም ባሹት መንገድ አራግበውታል፡፡

በብሔራዊ ባንኩ ገዥ ሰሞኑን በሞኒተሪ ፖሊሲው ላይ የተሰጠው ትንታኔ ለብርቱ ትችት የተጋለጠ ነበር፡፡ የፖሊሲ ትንታኔውና ገለጻው የእኔን ትኩረት የሳበው በሦስት መልክ ስለሆነ፣ ሦስቱንም በቅደም ተከተል በየተራ አቀርባለሁ፡፡

አንደኛው የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲዎች አንድምታና ውጤት የሚገለጸው ፍላጎትን ከመግራት ፖሊሲ (Demand Management Poicy) የአጭር ጊዜ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ ግንዛቤ አንፃር ቢሆንም፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥው የፖሊሲውን አንድምታና ውጤት በቀጥታ ያገናኙት ከረዥም ጊዜ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ (Supply Side Policy) ትንታኔ አንፃር ስለሆነ የፖሊሲዎች ግንዛቤ ተደበላልቋል፡፡ የአጭር ጊዜ ፖሊሲዎችና የረዥም ጊዜ ፖሊሲዎች የሚደጋገፉ ቢሆንም፣ መደጋገፍ ማለት ግን መደበላለቅ ማለት አይደለም፡፡ የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ባለቤት የሆነው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአሥር ዓመቱ ዕቅድ ከከሸፈበት በኋላ፣ በሁኔታዎች ግራ ተጋብቶ የለሁም ብሎ በዝምታ ድምፁን አጥፍቷል፡፡

ሰዎቹ ምክር አይሰሙም እንጂ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ባለሙያ እንደ መሆኔ የአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ረቂቅ በሚዘጋጅበትና በሚፀድቅበት ወቅት አንድ ጊዜ በሪፖርተር ጋዜጣ፣ ሌላ ጊዜ በሲራራ ጋዜጣ ሁለቴ ዕቅዱ ወቅቱን የጠበቀ ካለመሆኑም ባሻገር በቅርፅ፣ በይዘትና በተሳትፎ ከረዥም ጊዜ መሪ ዕቅድ ይልቅ የምርት መጠን ላይ ያተኮረ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ዕቅዶችን እንደሚመስልና ትክክል እንዳልሆነ አሳስቤ ነበር፡፡

ከወቅታዊነት አንፃር ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች በጦዙበት ወቅት የወደፊቱን ለመተንበይና ለማቀድ እንደማይቻል ያሳሰብኩ ሲሆን፣ ከይዘት አንፃር የረዥም ጊዜ ዕቅድ ትኩረት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገትና ዕምቅ የማምረት አቅምን ከማጎልበት አንፃር የሚታይ የልማት አቅጣጫ አመላካች ጠቋሚ ስለሆነ፣ ዝርዝር የምርት መጠን ዕቅድ ላይ እንደማያተኩር አስገንዝቤአለሁ፡፡ በተሳትፎም ከአቃጆች፣ ከፈጻሚዎችና ከአስፈጻሚ ባለሙያዎች ባሻገር፣ የአገሪቱ ገጸ ምድርና ከርሰ ምድር መልከዓ ምድራዊ ዕምቅ ሀብትና ዕምቅ የሰው ኃይል ሀብት መጠንና ሥርጭት ላይ ምርምር ባደረጉ በሳል ሰዎች መከናወን ይገባው እንደነበረ አስገንዝቤአለሁ፡፡ በደርግ ጊዜ በተዘጋጀው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌና ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንን የመሳሰሉ በሳል ሰዎች የኮሚቴ አባል በመሆን ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ አብነት ጠቅሼ አስረድቼአለሁ፡፡

ሁለተኛውን ትችቴን ለማቅረብ የዋጋ ንረት ምጣኔ (Inflation Rate) እና አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ (General Price Level) ጽንሰ ሐሳቦችን ማብራራት ይኖርብኛል፡፡ ብዙ አገሮች የዋጋ ንረት ምጣኔን እንደ ግብ የሚይዙ (Targeting Inflation Rate) ሲሆን፣ አጠቃላይ የዋጋ ደረጃን እንደ ግብ የሚይዙ (Targeting the General Price Level) ጥቂት አገሮችም አሉ፡፡ የዋጋ ንረት ምጣኔ የቀድሞ ዋጋ ንረትን ያለፈው አልፏል ብሎ ሲወስድ፣ አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ ግን የቀድሞ ስህተትን ለማረም ይሞክራል፡፡ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ መቼ የትኛውን መጠቀም እንደሚገባ ለማገናዘብ እንተንትናቸው፡፡

በ2015 ዓ.ም. መቶ ብር የነበረ የአጠቃላይ ዋጋ ደረጃ በ2016 ዓ.ም. አንድ መቶ አሥር ብር ቢደርስ የዋጋ ንረቱ ምጣኔ አሥር በመቶ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም. መቶ ብር የነበረ የአጠቃላይ ዋጋ ደረጃ በ2017 ዓ.ም. አንድ መቶ አምስት ብር ቢሆን የዋጋ ንረቱ ምጣኔ አምስት በመቶ ነው፡፡ ከ2016 ዓ.ም. ወደ 2017 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ በአምስት ብር ጨምሯል፣ የ2017/16 ዓ.ም. የዋጋ ንረት ምጣኔ ግን ከ2016/2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ቀንሷል፡፡ ከዋጋ ንረት ምጣኔ ግብ አኳያ በ2017 ዓ.ም. ሞኒተሪ ፖሊሲው ተሳክቷል፣ ባንኩ ያለመውን ውዳሴ ያገኝበታል፣ የአጠቃላይ ዋጋ ደረጃ ግን አልቀነሰም፣ ኑሮም አልተሻሻለም፡፡

ከዚህ ንፅፅር አንፃር የኢትዮጵያ ገበያዎችን ሁኔታ ለመመርመር ጤፍን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፡፡ አንድ ኩንታል ጤፍ በዚህ 2015 ዓ.ም. ከነበረበት ሦስት ሺሕ ብር በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሥር ሺሕ ብር ተሰቅሎ እዚያው ፀንቷል፡፡

ብሔራዊ ባንኩ በ2016 ዓ.ም. የዋጋ ንረትን ወደ ሃያ በመቶ ዝቅ አደርጋለሁ፣ በ2017 ዓ.ም. ደግሞ ወደ አሥር በመቶ ዝቅ አደርጋለሁ ሲል፣ የጤፍ ዋጋ በ2015 ዓ.ም. ከነበረበት አሥር ሺሕ ብር በ2016 ዓ.ም. አሥራ ሁለት ሺሕ ብር ይሆናል ማለት ሲሆን፣ በ2017 ዓ.ም. ደግሞ በአሥር በመቶ አድጎ አሥራ ሦስት ሺሕ ሁለት መቶ ብር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዓመት ዓመት በመቶኛ ምጣኔ የተለካው የዋጋ ንረት ምጣኔው ቀንሷል ሊባል ነው፡፡ በመጠን የተለካው አጠቃላይ የዋጋ ደረጃ ግን እየጨመረ ነው፡፡ እኛ የምንጠብቀው የሪፖርት ማሞቂያ ቁጥሮቹን ሳይሆን የጤፍ ዋጋ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ነበር፡፡

የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲዎች የአጭር ጊዜ የፍላጎት አስተዳደር ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ሚና በገቢ መጠንና በወለድ ምጣኔ ጣምራ ወሳኝነት የወሳኝ ተወሳኝ ሥሌታዊ ተዛምዶ የብሔራዊ ኢኮኖሚው የፍጆታ፣ የመዋዕለ ንዋይ፣ የመንግሥት፣ የተጣራ ኤክስፖርት ወጪዎችና ገቢ ወይም ምርት የሚመጣጠኑበትን፣ ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ የሚመጣጠኑበትን፣ የገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት የሚመጣጠኑበትን ዘዴ መሻት ነው፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው በተደጋጋሚ ሲያነሱ የሰማሁት የሞኒተሪ ፖሊሲን የአጭር ጊዜ የፍላጎት አስተዳደር ሚና ሳይሆን፣ የፕላን ሚኒስቴር ሚና ስለሆነው ምርምርን በማስረፅ፣ የሠራተኛ ገበያን በማሻሻል፣ የምርት ግብረ ኃይሎችን (Factors of Production) ድልድልና ዋጋ አወሳሰን በማሻሻል፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ምርትን የማሳደግ የረዥም ጊዜ መዋቅራዊ (Structural) የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ ንዝረቶች (Supply Side Policy Shocks) ነው፡፡ ለዚህ ነው የፖሊሲዎች ግንዛቤ ተደበላልቋል ያልኩት፡፡

ምንም እንኳ ከላይ በጠቀስኩት መሠረት የፍላጎት አስተዳደር የአጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፖሊሲ አንጻር ባይተነተንም፣ ብሔራዊ ባንኩ ነደፍኩት የሚለው የአጭር ጊዜ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ የዋጋ ንረት ፖሊሲ የረዥም ጊዜ ምርት አቅርቦትን የሚያሳድግ ነው ወይስ የሚያቀጭጭ? የአጭር ጊዜውና የረዥም ጊዜው ፖሊሲዎች ይደጋገፋሉ ወይስ ይቃረናሉ? ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ብሔራዊ ባንኩ አጠቃላይ የዋጋ ደረጃን እንደ ግብ ቢይዝ ይሻል ነበር? ወይስ የዋጋ ንረት ምጣኔን መወሰኑ በቂ ነው? የሚሉና ተመሳሳይ በርካታ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን ልናነሳ እንችላለን፡፡  

በኢኮኖሚ ጥናት ማረጋገጫ አንዴ የተሰቀለ ዋጋና በስምምነት የተወሰነ ደመወዝ በፍላጎትና በአቅርቦት የገበያው ውስጣዊ መስተጋብር እንደማይቀለበሱ (Price and Wage Stickyness) ቢታመንም፣ ፖሊሲ ሁኔታውን ሊያሻሽል እንደሚችል ስለሚታወቅ እኛ መንግሥት ጤፍን ወደ ነበረበት ሦስት ሺሕ ብር ባይመልስም እንኳ ወደ አምስትና ስድስት ሺሕ ብር ዝቅ ያደርግልናል ብለን ስናስብ፣ ብሔራዊ ባንኩ የነገረን ግን በ2016 ዓ.ም. እና በ2017 ዓ.ም. በቅደም ተከተል አሥራ ሁለት ሺሕ ብርና አሥራ ሦስት ሺሕ ብር አደርጋለሁ የሚል ነው፡፡

የብሔራዊ ባንኩ ሞኒተሪ ፖሊሲ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ንረት በኢኮኖሚ ሳይንስ ከሚታወቀው የንግድ ሥራ ዑደት (Business Cycle) ኢኮኖሚው ሲቀዘቅዝ የዋጋ ንረት ይቀንሳል፡፡ ኢኮኖሚው ሲሞቅና ገበያው ሲደራ የዋጋ ንረት ይጨምራል፡፡ ከሳይንሳዊ ኢኮኖሚ ትንታኔ ያፈነገጠ ነው፡፡ በመሆኑም ለሳይንሳዊ ትንታኔ የተሰጠ ሳይንሳዊ ፖሊሲ ጽንሰ ሐሳብን እንዳለ ወስዶ ከመጠቀም በፊት፣ የተጨባጭ ሁኔታ ጥልቅ ጥናት እንደሚሻ መገንዘብ ያሻል፡፡ እሾህን በእሾህ መንቀልም ያስፈልጋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ያየሁት የብሔራዊ ባንኩ ፖሊሲ ምን ያህል መረጃ ላይ እንደተመረኮዘ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንኩ የሚያወጣቸውን ዓመታዊ ሪፖርቶች እከታተላለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ፖሊሲዎቹ ምን ያህል የራሱ የውስጥ መረጃዎች ላይ እንደተመረኮዙ እንመልከት፡፡

በፖሊሲው ከተጠቀሱት ነጥቦች አንዱ ብሔራዊ ባንኩ ለንግድ ባንኮች የሚያበድርበትን የብድር ተቀናሽ ምጣኔ (Discount Rate) ከአሥራ ስድስት ወደ አሥራ ስምንት ከፍ ማድረጉን የሚገልጽ ነው፡፡ እስካሁን ከተመለከትኳቸው የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርቶች ንግድ ባንኮች ምን ያህል ለአጭር ጊዜ ወይም ለአዳር ከብሔራዊ ባንክ ወይም እርስ በራስ እንደሚበዳደሩ የሚያመለክት መረጃ አላየሁም፡፡ መረጃ ከሌለ ደግሞ የፖሊሲ አንድምታን ወይም ውጤትን ለመገመት ያስቸግራል፡፡ ንግድ ባንኮች ከሚፈለግባቸው የመጠባበቂያ ተቀማጭ እጥፍ በብሔራዊ ባንክ እንደሚያስቀምጡ በእነዚሁ ዓመታዊ ሪፖርቶች በመመልከቱ ውጤት አልባ ነው በሚል ዕሳቤ ብሔራዊ ባንኩ የመጠባበቂያ ተቀማጭ ጥምርታውን (Reserve Ratio) ለመከለስ አልፈለገም፡፡

ብሔራዊ ባንክ ገበያ ውስጥ የሚዘዋወረውን ብር መጠን የሚቀንስበትና የሚጨምርበት ከገበያ ውስጥ የመንግሥት ቦንድን የመግዛትና የመሸጥ የገበያ ተሳትፎ ፖሊሲን (Open Market Operation) ተግባራዊ እንዳያደርግ፣ በሕዝብና በግል ድርጅቶች የተያዘ በቂ የመንግሥት ቦንድ የለም፡፡ አዲስ ቦንድ ከመንግሥት እንዳይገዛም ይህ በቀጥታ ለመንግሥት ከማበደር ተለይቶ ስለማይታይ ገበያ ውስጥ የሚዘዋወረውን የብር መጠን ይጨምራል፡፡ በዚህ ፋንታ ብሔራዊ ባንኩ ከተለምዶ ፖሊሲዎች ወጣ ባለ መንገድ በጊዜያዊ አስተዳደራዊ መመርያ የምታበድሩት ገንዘብ ዕድገት መጠን ከአምናው ብድራችሁ ከአሥራ አራት በመቶ በላይ እንዳይሆን የሚሉ ትዕዛዞችን ሰጥቷል፡፡ አሥራ አራት በመቶው ለምን አሥር ወይም ሃያ እንዳልሆነ ብሔራዊ ባንኩ ያሰላበትን መንገድ ሊነግረን የሚችል አይመስለኝም፡፡ ብሔራዊ ባንኩ ከዓመት በኋላ የወለድ ምጣኔን ዘዴ ለመጠቀም ማሰቡ ስንወተውተው የቆየነው ጉዳይ ነውና ይበረታታል፡፡

መንግሥት ኢኮኖሚውን በማኮማተር የፊስካልና የሞኒተሪ ፖሊሲዎች (Contractionary Fiscal and Monetary Policies) ፍጆታንና መዋዕለ ንዋይን ለመቀነስ እንዳቀደ መገመት አያቅትም፡፡ በዚህ መልክ ኢኮኖሚን የማኮማተር አንድምታን ግን የተገነዘበ አይመስልም፡፡ በፍጆታና በመዋዕለ ንዋይ አርቢ ውጤቶች ምክንያት (Multiplier Effects) ኢኮኖሚው መንግሥት ካሰበው ሁለትና ሦስት እጥፍ ተኮማትሮ በሰላም መታጣትና በፖለቲካዊ ጉዳዮች የቀዘቀዘው ኢኮኖሚ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ምክንያትም የባሰውን ቀዝቅዞ ወደ ዝቅጠት እንደማያመራ በምን እንተማመን፡፡

ነገና ዛሬ ትናንትን ስለሚከተሉ ኢኮኖሚ በያለፈው አልፏል (Bygones are Bygones) ብሂል አይሄድም፡፡ ያለ ምክንያት ያበጡት የአንዳንድ ሸቀጦች ዋጋዎች መፍረጥ አለባቸው፡፡ አለበለዚያም ወደኋላ የቀሩት የሠራተኛው ዋጋና ገቢም መስተካከል አለባቸው፡፡ በአክሲዮን የተደራጁ የሕዝብና የመንግሥት ንብረትን በውክልና የሚያስተዳድሩ ተቋማት ለኃላፊዎቻቸውና ለሠራተኞቻቸው ይህን እንዳደረጉ ባለፈው ጊዜ ገልጬያለሁ፡፡

ኢኮኖሚውን አረጋግቶ ለማሳደግ የሚቻለው ግራ ቀኙን በሚያዩ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በሚረዱ ከጽንሰ ሐሳብ ጋርም በሚያዋህዱ በሳል ኢኮኖሚስቶች እንጂ በፈረንጅ ቋንቋ የሰሙትን በራሳቸው ቋንቋ መናገር በማይችሉ፣ ያለ ጥናትና ምርምር በሽምደዳ ተለጉመው ተምረው ያለ ጥናትና ምርምር በቢሮክራሲ ተለጉመው በሚሠሩ፣ የወደፊቱን ብቻ ለማየት በፖለቲካል ኢኮኖሚው በተለጎሙ ኢኮኖሚስቶች አይደለም፡፡ በጥናትና ምርምር ልጓሙ ተበጥሶ ሐሳብ በነፃነት ተንሸራሽሮ የተበጠበጠው ሳይጠራ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ራስን በመቻል አንድ ስንዝር እንኳ ወደፊት መራመድ በማትችልበት ወጥመድ ውስጥ ገብታለች፡፡

ከአዘጋጁ ጸሐፊው የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያና የማክሮ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመላከከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...