ለገጠመኜ እንደ መግቢያ ይሆነኝ ዘንድ ይህችን አጭር ሀተታ አንብቡልኝ፡፡ አዋቂዎች ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተመጋጋቢ ናቸው ይላሉ፡፡ በሥርዓት የሚመራ ፖለቲካ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሲሆን፣ ኢኮኖሚውም በአዋጭ ፖሊሲ ሲከናወን ፖለቲካውም መደላድሉ ምቹ ይሆናል፡፡ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ›› እየተባለ የፖለቲካው ምኅዳር ለካድሬዎች የሚተው ሳይሆን፣ በሀብትም ሆነ በዕውቀት የዳበረ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች ብርቱ ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፖለቲካን በሚገባ የተካኑበት ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ስለማያዳግታቸው ነው፡፡ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በፍፁም ሊለያዩ የማይችሉ ሲሆኑ፣ የአንዱ ሕመም ለሌላው ጦስ ይዞ ከተፍ ማለቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ሁለቱን በሚዛናዊነት ይዞ ለመቆየት ብልሆች ይተጋሉ፣ ያልገባቸው ደግሞ አንዱን ከሌላው ጋር እያዋጉ አገር ይበድላሉ፡፡ ሞኞች ግን ሁሉንም እርግፍ አድርገው ትተው የዳር ተመልካች ይሆናሉ፡፡
ከላይ ያነሳሁትን መንደርደሪያ በመንተራስ በቅርቡ ከገጠመኝ ልጀምር፡፡ መኖሪያ ሠፈሬ ውስጥ የሚገኝ አንድ ዘመናዊ ዳቦ መጋገሪያ መደብር ደርሻለሁ፡፡ ከእኔ ቀደም ብለው ዳቦ በመግዛት ላይ የነበሩ አራት ሰዎች በተራ እየተስተናገዱ ስለሆነ፣ እኔም ተራዬን እየጠበቅኩ ነበር፡፡ አንዲት በግምት 60 ዓመት የሚሆናቸው ዘመናዊ ወይዘሮ፣ ‹‹ድሮ ይህንን ዳቦ ቤት ልንገዛ በምንችልበት ዋጋ ዳቦ መግዛት እንጀምር…›› ሲሉ አስተናጋጇ፣ ‹‹እናንተስ በደህና ጊዜ በልታችኋል፣ እኛ ነን እንጂ መቅኖ ቢስ የሆነው…›› እያለች ትመልሳለች፡፡ ‹‹እውነትሽን ነው እኛስ በልተን ነበር፣ ሆድ ግን አየሁ አይልም…›› ብለው ሒሳባቸውን ከፍለው ወጡ፡፡ እኔም ተራዬ ደርሶ የምፈልገውን ያህል በውድ ዋጋ ገዝቼ ሄድኩ፡፡
የዳቦ ነገር አይደል የተነሳው? የዛሬ 40 ዓመት ገደማ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት አማካይነት የተገነቡት ዘመናዊ ዳቦ መጋገሪያዎች ትዝ አሉኝ፡፡ ከእነሱ በፊት እነ ሸዋ ዳቦና ሳምሶን ዳቦ፣ በአነስተኛ ደረጃ የነበሩ በርካታ መጋገሪያዎች እንደነበሩ አይረሳኝም፡፡ በአምስት ሳንቲም ሁሉት ባለመቶ ግራም ዳቦ መግዛት ይቻል ነበር፡፡ ከአሥር ሳንቲም ጀምሮ እስከ ሃምሳ ሳንቲም የተለያዩ መጠን ያላቸው ትልልቅ ዳቦዎች በከተማው ውስጥ በስፋት ነበሩ፡፡ ቃሊቲ አካባቢ የሄደ ሰው ደግሞ ኮኖናልቤ ይባል የነበረውን አንዳች የሚያህል ምርጥ ዳቦ በአሥር ሳንቲም ሒሳብ ገዝቶ ይመጣ ነበር፡፡ በወቅቱ ዳቦ ወረፋ ተይዞ በሠልፍ ይገዛ የነበረ ቢሆንም እንደ ዛሬው እንደ ላስቲክ የሚጨማደድ ሳይሆን፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ትክክለኛ መጠን ያለው ዳቦ እንገዛ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡
ዳቦን እንደ መነሻ አነሳሁ እንጂ ሌሎች የምግብ ምርቶች ማለትም ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሽንብራ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ አትክልትና ፍራፍሬ በተመጣጠነ ዋጋ በትክክለኛ መጠን መግዛት የወቅቱ አሠራር ነበር፡፡ ይህንን ስል ምንም ችግር አልነበረም፣ ጥጋብ በጥጋብ ነበርን ለማለት አይደለም፡፡ ቢያንስ በጊዜው የምናገኘው ገቢ ከወጪያችን የተሻለ ነበር ለማለት ነው፡፡ የሁለት መቶ ብር ደመወዝተኛ የነበረ ግለሰብ ቢያንስ ከወር እስከ ወር ከትዳር አጋሩና ከልጆቹ ጋር በቀን ሦስቴ በልቶ ይኖር ነበር፡፡ ይህ ማለት በሳምንት አንዴ አንድ ኪሎ ሥጋ ማግኘት ይችል ነበር፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ ቢበዛ በስምንት ብር ስለሚያገኝ ማለት ነው፡፡
በወቅቱ እንዳሁኑ ገበያው ልቅ ተደርጎ የሕገወጦች መጫወቻ ስላልነበር በዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ጠንካራ ቁጥጥር ይደረግ ነበር፡፡ ጎረቤታችን አነስተኛ ኪዮስክ የነበረው ግለሰብ በአምስት ሳንቲም መሸጥ የነበረበትን ክብሪት በአሥር ሳንቲም ሲሸጥ ተይዞ፣ በቀበሌ ፍርድ ሸንጎ የሦስት ወራት እስራት ተፈርዶበት ነበር፡፡ በርበሬና እህል አከማችተው ደብቀዋል የተባሉ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ተረሽነው ‹‹የፍየል ወጠጤ…›› እንደተዘፈነባቸው አገር ምድሩ የሚያውቀው የታሪካችን አካል ነው፡፡ ያ ምስኪን ባለኪዮስክ በቀበሌ ፍርድ ሸንጎ ሦስት ወራት ተፈርዶበት ቢለቀቅም፣ በየክፍለ አገሩ እንደ እሱ ዕድል ያልቀናቸው የጥይት እራት መደረጋቸውን እናውቃለን፡፡ ፖለቲካው ውስጥ የነበሩ ኮስታራ ሰዎች ገበያውን በጉልበት ተቆጣጥረው ዘረፋን ማስቆማቸው እስካሁን ቢደንቀኝም፣ የወቅቱ ያልተመጣጠነ ዕርምጃ አሁን ቢሆን ኖሮ ስንቶች ምን እንደሚደርስባቸው ሳስብ ያስደነግጠኛል፡፡
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ሥልጣን የሚፈልጉ ብልሆች፣ ለራሳቸው ሥልጣን ዋስትና ሲሉ ገበያውን በሕግ ለመምራት ይተጋሉ፡፡ ነፃ ገበያ ሲባል መንግሥት፣ ሸማቾችና ነጋዴዎች እየተናበቡ የግብይት ሥርዓቱ በፍትሐዊነት እንዲከናወን ዕገዛ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት ጣልቃ ሳይገባ ሒደቱን የሚከታተል ሲሆን፣ ነጋዴዎች ደግሞ በጤናማ ፉክክር ምርትና አገልግሎታቸውን ለሸማቹ ያቀርባሉ፡፡ ሸማቹም በነፃነት የመረጠው ቦታ ሄዶ በተመጣጣኝ ዋጋ የመግዛት መብት ይኖረዋል፡፡ መንግሥት በተጨማሪ የትርፍ ህዳግ ምጣኔ በማውጣት ያላግባብ ብዝበዛን ያስቀራል፡፡ ይህ ግን ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ ሸማቾች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፡፡
ኢኮኖሚክስ ተምረው የሚያስተምሩ ወዳጆቼ እንደሚነግሩኝ የአገራችን የግብይት ዋነኛ ችግር፣ ገበያው ውስጥ ሰተት ብለው የገቡ ጣልቃ ገቦች መብዛት ነው፡፡ ለምሳሌ ብለው ከሚያነሱት መካከል አንዱ በእህል፣ በቁም እንስሳት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ንግድ ውስጥ የአቅርቦት ሰንሰለቱን የተቆጣጠሩ ጣልቃ ገቦች (ደላሎች) መብዛት ለዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑን ነው፡፡ እነዚህ ጣልቃ ገቦች ከሕገወጥ ነጋዴዎችና ሥልጣናቸውን ከሚባልጉበት ባለሥልጣናት ጋር በመቀናጀት፣ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር ላልተገባ የዋጋ ንረት ሸማቾችን ይዳርጋሉ፡፡ በተጨማሪም የባለሥልጣናት ቤተሰቦች ሳይቀሩ የንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ገብተው፣ ጤናማ ፉክክር እንዳይኖር ያደርጋሉ ነው የሚሉት፡፡
በየሞሉና በየገበያ አዳራሹ ትንንሽ ኪዮስኮችን ይዘው ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ንግድ የሚያካሂዱ፣ ኪዮስኮቹን ከተሽከርካሪ ሽያጭ እስከ ሲሚንቶና ዘይት ድረስ የድለላ ኮሚሽን መቀበያያ የሚያደርጉ፣ እንዲሁም ከሐሰተኛ ደረሰኝ ኅትመት እስከ ሥርጭት ድረስ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶችን ያከናውናሉ፡፡ ምርቶች ከማሳ ጀምሮ በእነዚህ ደላሎች ቁጥጥር ሥር ውለው አቅርቦታቸው ሲስተጓጎል፣ የፖለቲካውን መዘውር የያዙ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች ነቅነቅ ማለት ካልቻሉ ነገ ምን ሊከተል እንደሚችል ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ‹‹ጨው ሆይ ለራስህ ስትል…›› እንዲሉ፡፡
(ይትባረክ ወልደ አምላክ፣ ከሸጎሌ)