Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹አትሌቲክሱ ከሚያበረክተው አንፃር የማዘውተሪያ ሥፍራ ያስፈልጋል ብለን ድምፃችንን ብናሰማም የሚሰማን አካል አልተገኘም››...

‹‹አትሌቲክሱ ከሚያበረክተው አንፃር የማዘውተሪያ ሥፍራ ያስፈልጋል ብለን ድምፃችንን ብናሰማም የሚሰማን አካል አልተገኘም›› ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

ቀን:

የቡዳፔስት የ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ ክስተቶች አስተናግዷል፡፡ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ1500 ሜትር በድርቤ ወልተጂ የብር ሜዳሊያ በማሳካት በዓለም ሻምፒዮና ታሪኳ100ኛ ሜዳሊያ መሰብሰብ ችላለች፡፡ በሴቶች 10 ሺሕ ሜተር ከሄልሲንኪው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን 18 ዓመታት በኋላ ጉዳፍ ፀጋይ፣ ለተሰንበት ግደይና እጅጋየሁ ታዬ ተከታትለው በመግባት ሦስቱን ሜዳሊያዎች የወሰዱበት ነው፡፡ ለሜቻ ግርማ በሦስት ሺሕ ሜትር መሰናክል ለሦስት ተከታይ ዓመታት የብር ሜዳሊያን ያገኘበት ሻምፒዮና ሆኖ አልፏል፡፡ ለሜቻ በተደጋጋሚ የብር ሜሊያ ማምጣቱን ተከትሎ፣ ‹‹ዘ ሲልቨር ማን›› የሚል ቅፅል የተቸረበት የዓለም ሻምፒዮና ነው፡፡

በሌላ በኩል የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮን በወንዶች 5000 ሜትር ከፍተኛ ውዝግብና ጭቅጭቅ የተነሳበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በዓለም ሻምፒዮናው ስለነበረው አጠቃላይ ተሳትፎና እንቅስቃሴ በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮናና የአትሌቲክስ ቡድን ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ፡- በሻምፒዮናው በርካታ ክስተቶች የተስተናገዱበት ነው፡፡ በተለይ እኔ በአትሌትነት ጊዜዬ እ.ኤ.አ. በ2005 የዓለም ሻምፒዮና በ10 ሺሕ ሜትር ከብርሃኔ አደሬና ከጌጤ ዋሚ ጋር በመሆን ተከታትለን የገባንበትን ወቅት ያስታወሰኝ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ፌዴሬሽኑ በፕሬዚዳንትነት እየመራሁ፣ ይህንን ድል መመልከት መቻሌ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ሌላው በሴቶች 1500 ሜትር በደርቤ ወልተጂ የብር ሜዳሊያ ማሳካት መቻላችን በጣም ደስተኛ አድርጎኛል፡፡ ምክንያቱም ያልጠበቅነው ነበር፡፡ ድርቤ ልምድ ካላቸውና በርቀቱ ክብረ ወሰን ካላት ኬንያዊት አትሌት፣ እንዲሁም ሲፋን ሐሰን ጋር ተሠልፋ ነሐስ ማግኘቷ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በአጠቃላይ በሃንጋሪ ከነበረው ከፍተኛ ሙቀት አንፃር የአትሌቶቻችን ተሳትፎና ብቃት የሚደነቅ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የ10 ሺሕ ሴቶች ውድድርን በኤድመንተን ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ስሜቱ እንዴት ይገለጻል?

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ፡- እኔ በምሮጥበት ዘመን የነበረው ስሜት ብዙም አልነበረም፡፡ ይህኛው ግን አንደኛው አመራርነት አለ፡፡ ሕዝብ ውጤት ይጠብቃል፡፡ ስለዚህ ስሜቱ በጣም የተለየ ነው፡፡ አትሌቶቻችን ጀግና ናቸው፡፡ በአንድ የሩጫ ውድድር ሦስት ሜዳሊያ ማሳካት ቀላል አይደለም፡፡ ቀድመን ለአትሌቶቹ አገርን ቀዳሚ አድርገው እንዲወዳደሩ ነግረናቸው ነበር፡፡ እሱን በሜዳው ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል፡፡ ለዚህም ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ሻምፒዮን የሚሳተፍበት ወቅት ከኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተቃራኒ በሚሆንበት ወር ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ ቡድኑ በኢትዮጵያ ባሉ ሞቃታማ አካባቢ እንዲዘጋጁ ለምን አልተደረገም?

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ፡- እኔ ከ30 ዓመት በፊት በባርሴሎና ኦሊምፒክ ስሳተፍ ወበቁ 80 ነበር፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በአትሌቶች ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ እኔ በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና፣ በመላ አፍሪካ ጨዋታና በቡልጋሪያ የወጣቶች ሻምፒዮና የተሳተፍነው በሐምሌና ነሐሴ ወር ላይ ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ሁሌም አዲስ አበባ ከተማ ነው ዝግጅት የምናደርገው፡፡ በተወሰነ ደረጃ እንቋቋመው ነበር፡፡ በእርግጥ በተወሰነ ደረጃ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብለን ሞቃታማ ሥፍራዎች ላይ ልምምድ እናደርግ ነበር፡፡ አሁንም በተወሰነ ደረጃ ወጣ ብለው ይሠራሉ፡፡ በአንፃሩ በአገሪቱ ያለው የማዘውተሪያ ሥፍራ ለዚህ አመቺ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አትሌቶቹ ወደ ክፍለ አገር ወጣ ብለው ልምምድ ያደርጉ ቢባል ጅምናዚየም፣ ትራክና ለልምምድ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የሉም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የማዘውተሪያ ሥፍራ ችግር መፍታት ይገባዋል፡፡ አትሌቲክሱ ለአገሪቱ እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ አንፃር ማዘውተሪያ ሥፍራ ያስፈልጋል ብለን ድምፃችንን ብናሰማም የሚሰማን አካል አልተገኘም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መንግሥት ለዓምናው የኦሪገንና የዘንድሮ የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማመሥገን ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት አሁንም ቢሆን የልህቀት ማዕከል መገንባት ይጠበቅበታል፡፡ ያለዚያ ይህ ኢትዮጵያ የምትወደስበት አትሌቲክስ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ እስከ መቼ በረዥም ርቀቱ እየተሳተፈች ትዘልቃለች?

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የአትሌቲክስ ክለቦች በተለያዩ ርቀቶች አትሌቶችን ለማፍራት እየጣሩ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ አትሌቶችና አሠልጣኞች፣ እንዲሁም ተቋማት ለሚያደርጉት ጥረትና ድካም ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ለአትሌቲክሱ የተሰጠው ትኩረት፣ እንዲሁም የተለያዩ መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ ችግሩን ተቋቁመው እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከረዥም ርቀት ባሻገር በአጭር ርቀት በርካታ አቅም ያላቸው አትሌቶች አሏት፡፡ ግን የሜዳ ተግባር እንዲሁም ከ400 ሜትር ጀምሮ ያሉ ርቀቶች የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዲሁም ባለሙያዎች ያስፈልጓታል፡፡ ግን አሁንም የማዘውተሪያ ሥፍራና ቁሳቁስ ማግኘት ፈተና ነው፡፡ የተሟላ ቁሳቁስ በሌለበት መወቃቀስ ተገቢ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ የአንድ ዓመት ዕድሜ ነው የቀረው፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ  ወቅት ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል በነበረው አለመግባበት ከፍተኛ ንትርክ መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን እየተሠራ ነው?

ረዳት ኮሚሽነር  ደራርቱ፡- በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበረው አለመግባባት ለመፍታት የቀድሞ ስፖርት ኮሚሽን ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳና መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) የመጀመርያ ሥራቸው በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈጠረውን ችግር መፍታት ነበር፡፡ በአንፃሩ ሁለቱ ተቋማት ወደ አምስተርዳም በማምራትና የፓሪስ ኦሊምፒክ በመቅረቡ በጣም የቀረበ ግንኙነት ባይፈጠርም ተቀራርበው መሥራት የሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፌዴሬሽኑ ጡረታ ከወጣ በኋላ በኦሊምፒክ ኮሚቴ መመደቡን ተከትሎ ችግሮች ከሥር ከሥር እንዲፈቱ በቅርበት እየሠራ ይገኛል፡፡ ሁለቱም ተቋማት የሚገባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ከዚህ ቀደም የተፈጠረው ክስተት እንዳይደገም በጋራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሁሉም አሠልጣኞች ለኦሊምፒክ ጨዋታው ያላቸው ዕቅድና መርሐ ግብር ከወዲሁ እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቀድሞ እንደነበረው ብሔራዊ ቡድኑ ከአሁኑ አትሌቶች ሳይበተኑ ከስድስት ወራት በፊት አስቀድመው ዝግጅት እንዲጀምሩ ከውሳኔ ደርሰናል፡፡ ከስድስት ሳምንታት በኋላ በላቲቪያ ከሚከናወነው የዓለም ግማሽ ማራቶን፣ 5 ኪሎ ሜትር እንዲሁም አንድ ማይል ውድድር ከተሳተፍን በኋላ የኦሊምፒክ ዝግጅቱ ይጀምራል፡፡  

ሪፖርተር፡- ከጥላሁን ኃይሌ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ጉዳይ ምንድነው?

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ፡- ጥላሁን በሻምፒዮናው ቢወዳደር ደስተኛ ነኝ፡፡ ግን ሀቁ የበሪሁ አረጋዊ ነው፡፡ በዓምናው የኦሪገን የዓለም ሻምፒዮን ጥላሁን ኃይሌ በበሪሁ አረጋዊ ቦታ እንዲሮጥ ተደርጓል፡፡ ከምድቡ ግን አላለፈም፡፡ ዘንድሮም በሪሁ በርቀቱ የተሻለ ሰዓት ያለው በመሆኑና ዓምና የተነፈገውን ዕድል ባለው ሰዓትና ወቅታዊ አቋም እንዲሠለፍ ተደርጓል፡፡ ይህ በግል የተወሰነ ውሳኔ አይደለም፡፡፡ በሥራ አስፈጻሚው የተወሰነ ነው፡፡  አሁን ባለው የወንዶች 5000 ሜትር ቡድን ላይ በሪሁ ቢሳተፍ የበለጠ የቡድን ሥራውን ይረዳል የሚል እምነት ስለነበረን፣ እንዲሁም ወቅታዊ አቋሙ ተመራጭ አድርጎታል፡፡ ስሜታዊ ሆኖ ለተናገረው ነገር አልቀጣነውም፡፡ ምክንያቱም ለዓለም ሻምፒዮና ዝግጅት ለፍቶ ስለነበር፡፡ ግን ሀቁ የበሪሁን ስለሆነ ብቻ በሪሁ እንዲሠለፍ ተደርጓል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...