- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ለ2016 በጀት ዓመት በቂ መጻሕፍት ማሳተም አልቻለም
የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ከአሁን በኋላ በካድሬነት ሳይሆን፣ በብቃታቸው ብቻ እንደሚመረጡ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያለው ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 30ኛው ዓለም አቀፍ የትምህርት ጉባዔ፣ ‹‹ሁለንተናዊ ርብርብ ለትምህርት ተቋማት ደረጃ መሻሻል›› በሚል መሪ ቃል ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች ከአሁን በኋላ የሚመረጡት በካድሬነት ሳይሆን፣ ባላቸው ብቃትና ችሎታቸው ላይ መሠረት ተደርጎ ይሆናል ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ በብቃታቸውና በችሎታቸው የተመዘኑ 1,600 የትምህርት አስተዳዳሪዎች ሥልጠና እንደተሰጣቸውና ይህ ዓይነቱ አሠራር ቀጣይነት እንደሚኖረው ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሳደግ ሥራ በተጨማሪ የመምህራንና ርዕሳነ መምህራን ብቃትና ችሎታ ማጎልበትም ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡
ትኩረት ካገኙ መሠረታዊ ጉዳዮች ትምህርት ቤቶችን በግብዓትና በጥራት ከማሻሻል ባሻገር ክህሎት፣ ብቃትና ችሎታ ባላቸው ርዕሳነ መምህራን እንዲተዳደሩ ማድረግ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል በተጨማሪ በዕውቀት ተማሪዎቻቸውን ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችሉ መምህራንን ማብቃት ከተያዙ ግቦች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጥራት መውረዱን ገልጸው፣ በኑሮ ለተሻሉ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩበት ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
ይህ ዓይነት አካሄድ በዜጎች መካከል በኑሮ ደረጃ ከተፈጠሩ ልዩነቶች አልፎ በትምህርት ዘርፍ ላይ መታየቱ ትልቅ ክስረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህ አካሄድ በአገር አቀፍ ደረጃ አደገኛ ሁኔታዎች የሚፈጥር መሆኑን፣ በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች በገንዘብ ዕጦት ሳቢያ የትምህርት ጥራት ሊጓደልባቸው አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ትምህርት የአገር የሉዓላዊነት እሴት መለኪያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ጉዳይ ለዓመታት የተቀለደበት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው አሁን እርስ በርስ መነጋገር የማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱ የችግሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ዘርፍ መሠረታዊ መርሆዎች ሁለት መሆናቸውን ገልጸው፣ ዜጎች በብሔራቸውና በሃይማኖታቸው ሳይታዩ እኩል ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት መብታቸውን ማረጋገጥ አንደኛው መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ከሁሉም እኩል ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የሚሆኑበትን የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት፣ አሁን ያለውን የኢፍትሐዊነት ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉ ከአሥር ዓመታት በኋላ ትምህርት ቤቶች እንደ አሁኑ የፀብ (የረብሻ) መፍለቂያ ሳይሆኑ የመወዳደሪያና የብቃት ማጎልበቻ ይሆናሉ፡፡
ከዚህ በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዲግሪ እንደ ከረሜላ የሚታደልበትን አሠራር አስቀርቶ፣ በብቃትና በችሎታ ብቻ ዜጎች ማዕረግ የሚያገኙበት ሥርዓት በዘላቂነት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት 6,019,348 መጻሕፍት ለማሳተም የታቀደ መሆኑን፣ 4,125,811 ያህል መሠራጨታቸውን፣ 1,893,537 መጻሕፍት በኅትመት ሒደት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሪፖርት ያሳያል፡፡
የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መጻሕፍት ለማዳረስ ጥረት ቢደረግም በዶላርና በኅትመት ቤቶች አቅም ማነስ ምክንያት በተፈለገው ልክ መጻሕፍት አልታተሙም፡፡
በ2015 በጀት ዓመት የ12 ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ለኅትመት የተላኩ መጻሕፍት በሚፈለገው ፍጥነት አለመድረሳቸው፣ ትምህርት ቤቶች የፖለቲካ ማራመጃ አካባቢ የማድረግ አዝማሚያ መታየቱ፣ የተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ መዘግየትና ተዓማኒና ወቅታዊ መረጃ ልውውጥ አናሳ መሆኑን ከታዩ ችግሮች ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡
በሙከራ ትግበራ ላይ የነበረው የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ወደ ሙሉ ትግበራ መገባቱ፣ ኅትመታቸው የተጠናቀቁ መጻሕፍት ሥርጭት ላይ የተደረገው የጋራ ሥራ በበጀት ዓመቱ ከታዩ ጥንካሬዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በ2016 ትምህርት ዘመን የአጠቃላይ ትምህርት ፍትሐዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ ጥራትና ተገቢነት ያለው የመማር ማስተማርና የትምህርት ውስጣዊ ብቃትን ማጎልበት ከዕቅዱ የትኩረት መስኮች መካከል ይገኝበታል፡፡
የስምንተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች አማካይ 50 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች መጠን አሁን ካለበት 64.07 በመቶ፣ ወደ 65 በመቶ ማድረስ መታቀዱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በ2015 ትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ፈተና ውጤት፣ ከመላው የአገሪቱ ክፍል የተሻለ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የተመዘገበውን ውጤት ለትርፍ ያልተቋቋሙ ትምህርት ቤቶች ያመጡት መሆኑን ጠቁመው፣ የከተማው ትምህርት ቢሮ መኩራራት ያለበት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የመጣ ውጤት ቢሆን ነው ብለዋል፡፡