Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝብ ማስለቀስና አገር ማተራመስ ይብቃ!

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚስተዋሉ አጓጉል ድርጊቶች በጊዜ እንዲቀጩ ካልተደረገ፣ በናፍቆት የሚጠበቀው ሰላም ዕውን ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ይገባል፡፡ ፖለቲካው በአማተሮች የሚመራ ይመስል በብሽሽቅ የታጀበ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› የሚል ዲስኩርም ሆነ፣ ጊዜያዊና አላፊ ፍላጎቶች ላይ የተመረኮዘ መገለባበጥ የሚያስከትለው ፍጅት እንጂ ሰላም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ከዓመታት በፊት ሩዋንዳ ያለፈችበትን አሰቃቂ የዕልቂት ታሪክ ዓውድማ ሊያደርጉ የሚችሉ ትርክቶች እየበዙ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የነበረች ታሪካዊት አገርን፣ አርቆ ማየት በተሳነው አስተሳሰብ የግጭት አዙሪት ውስጥ በመክተት ተምሳሌታዊነቷን ጥላሸት መቀባት ማቆም ካልተቻለ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን መልከ ብዙ ኅብረ ብሔራዊያን መሆናቸው እየታወቀ፣ አንዱን ከሌላው ጋር በማጋጨት የሚሸመት የጥፋት ሴራ በየዕለቱ መጎንጎን አገር አጥፊነት ነው፡፡ የብሔርም ሆነ የእምነት፣ የቋንቋም ሆነ የባህል፣ የፖለቲካ አቋምም ሆነ ማኅበራዊ መስተጋብር በእኩልነት ተከብሮ የታላቅ አገር የጋራ ባለቤት መሆን ሲቻል እያደር ቁልቁል መውረድ ያሳቅቃል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ማንም የማንም ጠላት ሊሆን አይገባም፡፡ እንኳንስ ዘመናትን በትውልዶች ቅብብል እየተሸጋገሩ እዚህ ደረጃ የደረሱ ኢትዮጵያውያን ቀርተው፣ ባዕዳን ሳይቀሩ ተከብረውና ተፈቅረው የሚስተናገዱባት አገር እንደሆነችም መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንባትን ኢትዮጵያን ሳይሆን ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግደዋን በጋራ መገንባት እየተቻለ፣ በአጓጉል አስተሳሰቦች እየተመሩ ክፍፍል መፍጠርና አገራዊ ጥንካሬን ማሽመድመድ ለማንም እንደማይጠቅም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ወጣት ኢትዮጵያውያን ይህችን የመሰለች ለምና በተፈጥሮ የበለፀገች አገራቸውን ትተው እየተሰደዱ የባዕዳን አገሮች ድንበር ጠባቂዎች የጥይት ዕሩምታ እራት ሲሆኑ፣ የበረሃና የባህር ሲሳይ ሆነው የትም ሲቀሩና በአገራቸው ተስፋ ቆርጠው እግሬ አውጪኝ ሲሉ ሊቆጭ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከትናንት የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት አቅቶ፣ ጥንት ተፈጸሙ በሚባሉ የታሪክ ትርክቶች ላይ በመቸከል እርስ በርስ መበላላት ነው የተያዘው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያ የዕልቂትና የውድመት ታሪክ ባለመማር፣ ያንኑ አስከፊ ድርጊት በከፋ ሁኔታ ለማስቀጠል እንቅልፍ ማጣት ያስተዛዝባል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል ማለት ቅንጦት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት አንገሽግሾታል፡፡ ከዚህ አደገኛ ቀውስ ውስጥ በፍጥነት መውጣት ካልተቻለ እልሁ፣ ቂሙ፣ በቀሉ፣ ክፋቱ፣ ጭካኔውና አውሬነቱ እየተስፋፋ መጠፋፋቱ የከፋ ይሆናል፡፡ አጋጣሚውን እንደ መልካም ዕድል ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ደግሞ፣ የእሳት ማቀጣጠያውን ይዘው በተለያዩ ዘዴዎች በመቅረብ ኢትዮጵያ የሩዋንዳን ታሪክ እንድትደግም ያደርጓታል፡፡ ኢትዮጵያን የነፃነታችን ፋና ወጊ እናት ናት የሚሉ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች፣ እባካችሁ የአገራችሁን ሰላም ተባብራችሁ መልሱ እያሉ ጥሪ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ከገባችሁበት ቀውስ ውስጥ በፍጥነት ካልወጣችሁ የሩዋንዳውን አስከፊ ታሪክ በሚዘገንን ሁኔታ ትደግማላችሁ እያሉ ነው፡፡ ይህንን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በማለት ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል የተጀመረው አደገኛ ትንቅንቅ መገታት አለበት፡፡ የአንድ አገር ልጆች ለአንዲት አገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት የጋራ አቋም ሊኖራቸው ሲገባ፣ በብሔርና በተለያዩ ፍላጎቶች ላይ በመመርኮዝ አገርን ጤና መንሳት በታሪክም በትውልድም ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በጠላትነት ከመተያየት ወዳጅነትን ማጠናከር ያስከብራል፡፡

በመንግሥትና በፓርቲ መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ከንግግራቸው ጀምሮ እስከ ድርጊታቸው ድረስ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ሊያጋጩ ከሚችሉ ነገሮች መቆጠብ አለባቸው፡፡ ይህ ጉዳይ የገዥውን ፓርቲ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉትን ጭምር ይመለከታል፡፡ በተለይ ግን የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊነትን የጨበጡ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች፣ አገርን የማስተዳደር ኃላፊነት ስላለባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻሉ ለግጭት መቀስቀስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ፖለቲካውን በጥበብ መምራት የሚገባቸው ሰዎች በማኅበራዊ የትስስር ገጾችም ሆነ በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች፣ የአንድ አገር ሕዝብነትን በመካድ ክፍፍል መፍጠር ላይ የሚያተኩሩ ከሆኑ ቁርሾ በመፍጠር ቀውስ ከማባባስ ውጪ ጥቅም አይኖራቸውም፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን በማጦዝ ብሽሽቅን መሠረት ያደረጉ አተካራዎች ላይ ከመጣድ በፊት፣ ግራና ቀኙን መዝኖ ለዘላቂ ሰላምና ለኢትዮጵያ አንድነት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ብሔርን ወይም እምነትን ብቻ በመመርኮዝ አገርን ሕዝብን ማዕከል የማያደርጉ የፖለቲካ ዲስኩሮች፣ ቅራኔ ከመዝራትና ቂም ከማበራከት የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው ጨዋውና አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነውረኛ ፖለቲከኞች በሚረጩት መርዝ መሰቃየት ሰልችቶታል፡፡ ልዩነቶቻቸውን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ያቃታቸው ፖለቲከኞች ሰብዓዊ ጋሻ እያደረጉት የግድያ፣ የማፈናቀል፣ የዘረፋ፣ የአካላዊና የሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሰለባ መሆን አንገሽግሾታል፡፡ ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላው እየተሽከረከሩ የራሱንም ሆነ የልጆቹን መፃኢ ዕድል የሚያጨልሙ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፖለቲከኞች፣ በተቻለ ፍጥነት ገለል ቢሉለት ወይም ተስማምተው አስተማማኝ ሰላም እንዲያሰፍኑለት በተለያዩ መንገዶች ቢጠይቅም ሰሚ አላገኝም፡፡ እነሱ ለኑሮው ዕድገትና ለአገሩ ሰላም ከማምጣት ይልቅ ዘወትር ግጭት ጠማቂ መሆናቸው፣ በአንድም ሆነ በሌላ ለህልውናውም ሆነ ለመጪው ትውልድ መቀጠል ጠንቅ ከመሆን ውጪ የረባው ነገር የለም፡፡ ይህ ታሪካዊና ኩሩ ሕዝብ ለዘመናት በውስጡ ያዳበራቸው የግጭት አፈታትና የሽምግልና አኩሪ እሴቶቹ ተንቀው፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፖለቲከኞች የማያቋርጥ አደጋ ሲደቅኑበት በሕግ አምላክ መባል አለበት፡፡ እነሱ እንደ አየሩ ፀባይ አቋማቸውን እየቀያየሩ መርህ አልባ ጉድኝቶችን በፈጠሩ ቁጥር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው ከመመሰቃቀል አልፎ ሕይወቱን በከንቱ መገበር የለበትም፡፡

አገር የምታስተዳድሩም ሆነ ወደፊት አገር ለማስተዳደር አልማችሁ የፖለቲካ ፉክክሩ ውስጥ ያላችሁ በሙሉ፣ እባካችሁ ለዚህ ደግና ርህሩህ ሕዝብ አስቡለት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወቀው ሕግ በማክበር፣ መንግሥትን በማመን፣ አገሩን በማፍቀር፣ እንግዶችን በመልካም መስተንግዶ ተቀብሎ በመሸኘት፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ በባህል ዘዴዎች መላ በመፈለግ፣ አብሮ በመሥራት፣ ያለችውን በመካፈልና በበርካታ መልካም እሴቶቹ ነው፡፡ ይህንን የሚያኮራ ትጉህ ሕዝብ መምሰል ሲገባ ነጋ ጠባ ነገር በደላላ እያፈላለጉ ሕይወቱን ሲኦል ማድረግ ያሳዝናል፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ደሙን ማፍሰስና አገሩን መቅኖ ቢስ ማድረግ መገታት አለበት፡፡ በአሳፋሪ የፖለቲካ ቁማር ኢትዮጵያን ከደረጃዋ አውርዶ የዓለም መዘባበቻ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያኮሩ የታሪክ ባለቤት የሆነች አገርን ከግጭት አዙሪት ውስጥ እንዳትወጣ ማድረግ፣ ለጊዜው ባያስጠይቅ እንኳ የዘሩትን ማሳጨዱ አይቀሬ እንደሆነ ይታወቅ፡፡ ከትናንት የጥፋት ታሪኮች አለመማርና ጥፋትን ማበራከት፣ በሕግም ሆነ በታሪክ የሚያስጠይቅበት ጊዜ እንደሚኖር መገንዘብ ይገባል፡፡ እስከዚያው ግን ሕዝብ ማስለቀስና አገር ማተራመስ ይብቃ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...