Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ እንዳይገባ ተከልክሎ የነበረው ጫት መጠኑ ተቀንሶ እንዲላክ ተፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ እንዳይገባ ተከልክሎ የነበረው የጫት ምርት በፊት ይላክ የነበረውን መጠን በመቀነስ በድጋሚ እንዲላክ ተፈቀደ፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን መሐመድ ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ይገባ የነበረው ጫት ላይ ጥለውት የነበረውን ዕገዳ ከነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አንስተዋል፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረት ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ትልክ የነበረውን የጫት መጠን (ኮታ) በመቀነስ፣ ከኬንያ ጋር በቀናት በየተራ እንዲልኩ መደረጉን የጫት ላኪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሶማሊያና በኬንያ መካከል የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ቆይቶ የሰላም ስምምነት መደረጉ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎች ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ጫት ላይ ይጥሉት በነበረው ቀረጥ ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ መላክ ማቋረጧ አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ የጫት ላኪዎች ወደ ሶማሊያ ጫት መላክ ያቋረጡበት አንደኛው ምክንያት፣ ክልሎች የሚጥሉት ታክስ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት እንደነበር ላኪዎች ይናገራሉ፡፡

ክልሎችን ገቢ ለማሳደግ በሚል ምክንያት ኤክስፖርት የሚደረግ ጫት ላይ ታክስ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ የጫት ላኪዎችን ተወዳዳሪነት እንዲቀንስ አድርጎታል ሲሉ ላኪዎች ገልጸዋል፡፡

ክልሎች ታክስ መጣል በጀመሩበት ወቅት ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የኬንያና የሶማሊያ ግንኙነት በሰላም ስምምነት በመቋጨቱ፣ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የሚገባውን ጫት ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም አድርጋ ነበር፡፡

የኬንያ ላኪዎች ታክስ ስለማይደረጉና ከኢትዮጵያ ዋጋ በታች ስለሚያቀርቡ ተመራጭ እንዳደረጋቸው ላኪዎች ተናግረዋል፡፡

በየክልሉ የሚጣለው ተደራራቢ ታክስ እንዲነሳ ጉምሩክ ኮሚሽንን ጨምሮ ከፍተኛ የጫት ገበያ ካላቸው ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪና ድሬዳዋ ከተማ ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ በላይነሽ ረጋሳ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጫት የምትልከው ወደ ሶማሊያ ብቻ ሳይሆን፣ በአንደኛ ደረጃ ሐርጌሳ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጂቡቲ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት 31,363 ቶን የጫት ምርት ወደ ተለያዩ መዳረሻ አገሮች በመላክ 248.36 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ታውቋል፡፡

ከጫት ምርት የተገኘው ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ44.24 በመቶ ቅናሽ፣ እንዲሁም በገቢ 36 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ሲሉ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ኮንትሮባንድ፣ ተደራራቢ የታክስ ክፍያ፣ የንግድ ሥነ ምግባር ጉድለትና ከጉምሩክ ዕውቅና ውጪ አላስፈላጊ ኬላዎች መስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲቀንስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን በላይነሽ ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ መዳረሻ ያደረገቻቸው ጫት ተቀባይ አገሮች ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ እስራኤል፣ ኬንያ፣ ሴራሊዮን፣ ኮንጎ፣ ማዳጋስካርና ብሩንዲ ናቸው፡፡ በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ለአምራች ክልሎች ከጉምሩከ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት፣ የጫት ምርት ሕገወጥ ዝውውርና ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሠራ እንደሚገኝ በላይነሽ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጫት ንግድ መዳረሻ ገበያ ለማስፋት፣ እንዲሁም የጫት ምርት የወጪ ንግድ ችግሮችንና መፍትሔዎችን በጥናት በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫና ምክረ ሐሳብ እንዲቀርብ መደረጉን አክለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የጫት ኤክስፖርት በመቋረጡ ምክንያት፣ በዓመት ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊቀንስ እንደሚችል ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተገኘ መረጃ መረደት ተችሏል፡፡

ያደታ ጁነዲ የጫት ኤክስፖርት ድርጅት በቀን ከ20 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ኪሎ ግራም ድረስ ወደ ሶማሊያ ይልክ እንደነበር፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፋህሚ አብዱልመጂድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ላለፉት አምስት ወራት ምንም ዓይነት ጫት ኤክስፖርት ባለማድረጉ፣ በቀን ከ400 እስከ 500 ዶላር ድረስ የሚያገኘው ገቢ መቅረቱን ፋህሚ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 4,991 ፈቃድ ያላቸው ጫት ላኪዎች ውስጥ 499 ያህሉ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና እስራኤል እንደሚልኩ ታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጫት ዘርፍና በጫት አርሶ አደሮች ዘንድ ችግር መኖሩን አረጋግጠው፣ ችግሩን ለመፍታት ምክክር እየተደረገ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች