የወባ በሽታ በሞቃታማ አካባቢዎች በስፋት በሚራቡ ትንኞች የሚከሰት ከዓለማችን ገዳይ በሽታዎች በቀዳሚነት የሚሠለፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም የበርካታ ወገኖችን ሕይወት በየዓመቱ እየቀጠፈ ያለው ይህ በሽታ በተለያዩ ክፍሎች በመዛመት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሽታው በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል መከሰቱን ተከትሎ መንግሥት የተለያዩ አሠራሮችን ዘርግቶ እየሠራ ቢሆንም ችግሩ አሁንም አልተፈታም፡፡
በደቡብና ሲዳማ ክልሎች የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሔኖክ በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2015 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ447 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡
በተለይም በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የወባ በሽታ ያለባቸው ቦታዎች ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ወላይታ፣ ስልጤና ኮንሶ መሆናቸውን የተናገሩት አስተባባሪው በእነዚህ አምስት ዞኖች 75 በመቶ ያህል በሽታው መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኦሞ የሚገኙ ሰላምጎና ዳሰነሻ ወረዳዎች ላይ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች መያዛቸውን ጠቅሰው በጋሞ፣ በአርባ ምንጭ፣ ምዕራብ ዓባያ በሚገኙ ወረዳዎች ችግሩ የታየ መሆኑን አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት በወላይታ አካባቢ የሚገኙ ወረዳዎች ላይ ችግሩ ያለው በከፊል ደረጃ የሚባል መሆኑን ገልጸው በ2015 ዓ.ም. ኅዳርና ታኅሣሥ ወር ላይ በስልጤ አካባቢዎችም በሚገኙ 11 ወረዳዎች ላይ ወረርሽኙ እንደነበር ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በስልጤ አካባቢ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ላይ ወረርሽኙ አሁን ድረስ መኖሩንና በአጠቃላይም የወረርሽኙ ስፋት በክልል ደረጃ ሲታይ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡
ዓምና በክልሉ በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበርና ይኼም ከዘንድሮ ጋር ሲነፃፀር ተመሳሳይ ሆኖ በመገኘቱ የችግሩ አስከፊነት በስፋት ያሳያል ብለዋል፡፡
በክልል ደረጃ አብዛኛውን ጊዜ የወባ መከላከያ ግብዓቶች የሚቀርቡት ከፌዴራል መንግሥት በኩል ስለሆነ እንደ አገርም የኬሚካል ግዥ በመዘግየቱ የተነሳ የኬሚካል ግብዓት ለክልሉ አለመቅረቡን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከተያዙት ከ447 ሺሕ በላይ ሰዎች ውስጥ 24 ሰዎች ብቻ መሞታቸውን የተናገሩት አቶ ሔኖክ፣ ይኼም በአንፃራዊነት ሲታይ ለሕሙማኑ የክልሉ ጤና ቢሮ ተገቢ የሕክምና አገልግሎት በማዳረሱና ከግል መድኃኒት አቅራቢዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠሩ ብዙኃኑን ከሞት መታደግ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ማኅበረሰቡ ጋር ያለው የግንዛቤ እጥረት ዝቅተኛ በመሆኑ ወረርሽኙ በክልሉ በስፋት ሊሠራጭ መቻሉንና የተቆራረጠ ዝናብ በመፈጠሩም ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉም እየታየ ያለውን የወባ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር 4.4 ሚሊዮን አጎበር መሠራጨቱን ይኼም በአማካይ ሲታይ 86 በመቶ ያህል ሽፋን ማዳረሱን አቶ ሔኖክ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ማኅበረሰቡ አጎበር ሲጠቀም በትክክለኛ መንገድ ባለመሆኑ የተነሳ የወረርሽኙን ስፋት መቆጣጠር እንዳልተቻለና ከዚህ በፊትም ይተገበር የነበረው የወባ ኬሚካል ርጭት መቅረቱ ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
በተለይ የወባ በሽታ መከላከያ ኬሚካል ግዥ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅና በአጋር ድርጅቶች በኩል በሚደረግ ድጋፍ የሚገዛ በመሆኑ የአቅርቦት ችግር ሊከሰት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በፊት ኬሚካል በአገር ውስጥ ተመርቶ ይቀርብ እንደነበር ያስታወሱት አስተባባሪው፣ በአሁኑ ወቅት ግን የዓለም አቀፍ ደረጃን ስለማያሟላ ከሌላ አገር እየመጣ ሥርጭቱ የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖር ጥናቶቹ ያመላክታሉ፡፡
ማሌሪያ ኮንሶርቲየም የተባለ ተቋም በድረ ገጹ እንዳመለከተው፣ በኢትዮጵያ በወባ በሽታ ከሚጠቁት ኢትዮጵያውያን መካከል በደቡብ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ነው፡፡
በዓለም የሚታወቁ አራት ዓይነት የወባ በሽታ አምጪ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን፣ እንደ ልዩነታቸው የገዳይነታቸው መጠናቸውም ይለያያል፡፡ አፍሪካ ከምታውቃቸው ዝርያዎች የተለየና ገዳይ የሆነ አዲስ ዝርያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መገኘቱ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ይህ በከፍተኛ መጠን ተስፋፊ ነው የተባለው ዝርያ ከህንድ የመጣና በቀላሉ የሚዛመት መሆኑንም ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡