Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከቴአትር ባለሙያዎች ይቆረጥ የነበረው ሁለት በመቶ ቀረጥ ወደ ሰላሳ በመቶ ከፍ እንዲል...

ከቴአትር ባለሙያዎች ይቆረጥ የነበረው ሁለት በመቶ ቀረጥ ወደ ሰላሳ በመቶ ከፍ እንዲል ተደረገ

ቀን:

ለረዥም ዓመታት ከቴአትር ባለሙያዎች ማለትም ከአዘጋጆች፣ ደራሲያንና ተዋንያን ላይ ይቆረጥ የነበረው የፈጠራ የሥራ አበል ድርሻ ሁለት በመቶ ቀረጥ ወደ ሰላሳ በመቶ ከፍ መደረጉ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሥሩ ለሚገኙ ቴአትር ቤቶች በላከው ደብዳቤ፣ ‹‹ከሦስት ሺሕ ብር ደመወዝ በላይ የሚከፈለው የቴአትር ባለሙያ ክፍያ ሲፈጸም 30 በመቶ ቀረጥ ተቀናሽ ተደርጎ ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ፤›› ብሏል፡፡

ቢሮው ይህን ደብዳቤ ለቴአትር ቤቶች የላከው ከአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በተላለፈ ትዕዛዝ መሆኑን በደብዳቤው ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሥር በሚገኙ አራት ቴአትር ቤቶች ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነው ተጨማሪ የቀረጥ ክፍያ ባለሙያውን የማያበረታታ ነው ያሉ የቴአትር ደራሲያን፣ ሥራዎቻቸውን ከቴአትር ቤቶች እንደሚያወርዱ ማስታወቃቸው ተሰምቷል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ሥር ከሚገኙት ቴአትር ቤቶች የአዋቂ ቴአትሮች በማሳየት ላይ የሚገኘው የሀገር ፍቅር ቴአትር ብቻ ሲሆን፣ ራስ ቴአትርና ማዘጋጃ ቤት በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱት ጸሐፌ ተውኔት አቶ ውድነህ ክፍሌ ለሪፖርተር እንደተናሩት፣ ከ40 ዓመታት በላይ ሲተገበር የቆየውን ሕግ በአንድ ጀንበር ተነስቶ በመሻር እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ማስተላለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕጉን ያወጡ አካላት የሙያውን ባህሪ ካለመረዳት የደረሱበት ውሳኔ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

የቴአትር ድርሰት መጻፍ ምንም ትርፍ የሌለው ሥራ መሆኑን የገለጹት አቶ ውድነህ፣ ‹‹ደራሲው ክፍያ የሚያገኘው ተመልካች ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለቴአትር የተሻለ ጊዜ እየመጣ ነው በምንልበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት የደራሲያንን የሥራ ፍላጎት የሚቀንስ ውሳኔ ላይ መደረሱ አሳዛኝና ያልተገባ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከቴአትር ቤቱ ጋር ቀደም ሲል በተገባው ውል መሠረት የማይፈጸምና በአዲሱ ውል ይፈጸም ከተባለ፣ ለቴአትር ቤቱ ያበረከቷቸውን ሦስት ሥራዎች እንደሚያወርዱ አቶ ውድነህ አስታውቀዋል፡፡

የቴአትር ቤቱ አስተዳደርና የቢሮው ኃላፊዎች ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቀረጥ ጭማሪውን  እንዲተገብሩት ከተነገራቸው ቴአትር ቤቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም ጀማል፣ ከሦስት ሺሕ ብር በላይ የሆኑ ማናቸውንም ክፍያዎች የፈጠራ ተብለው ሁለት በመቶ የነበረውን ወደ ሰላሳ በመቶ ከፍ በማድረግ ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ ተገልጾልናል ሲሉ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ቢሮው ያስተላለፈው ውሳኔ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. የደረሰን ቢሆንም፣ ለባለሙያዎች ክፍያ የሚፈጸመው ከተሰበሰበው ገቢ በወሩ መጨረሻ ላይ ታክስ ተቆርጦ በመሆኑ በደራሲዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፤›› ሲሉ አቶ አብዱልከሪም አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ቴአትር ቤቱ መፍትሔ በማፈላለግ ላይ መሆኑን፣ ከሳምንታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ተወካዮች በቴአትር ቤቱ ተገኝተው የባለሙያዎቹን ሥራዎች መመልከታቸውን አቶ አብዱልከሪም ተናግረዋል፡፡

ለቴአትር ቤቶቹ ደብዳቤ ከላከው የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ለሆኑት ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ለቢሮው ምክትል ኃላፊ ሰርፀ ፍሬስብሐት የስልክና የጽሑፍ መልዕክት በመላክ ምላሽ ለማግኘት ሪፖርተር በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመታየት ላይ ከሚገኙት የደራሲ ውድነህ ክፍሌ ሥራዎች መካከል ‹‹በዓሉ ግርማ – ቤርሙዳ›› እና ‹‹የደፈረሱ ዓይኖች›› ተጠቃሽ ናቸው፡፡

‹‹በዓሉ ግርማ – ቤርሙዳ ቴአትርን ለመሥራት ከ11 ወራት በላይ የፈጀ ሲሆን፣ በርካታ ተመልካች እያገኘ የመጣ ቴአትር ነው፡፡ ለቀረጥ ክፍያው ሳነሳ በመቶ የሚፈጸም ከሆነ ከሀገር ፍቅር ጋር ያለኝን ውል በማቋረጥ ምንም ዓይነት የቀረጥ ክፍያ  ከሌላቸው የግል ኢንተርፕይዞች ጋር መሥራት እጀምራለሁ፤›› ሲሉ አቶ ውድነህ አስታውቀዋል፡፡

 ‹‹እኔ በግሌ ቴአትር ድርሰት የምጽፈው ሙያውን ስለምወደው እንጂ፣ የረባ ገንዘብ የሚያመጣ ሥራ ስለሆነ አይደለም፤›› ያሉት ደራሲው፣ ‹‹ነጭ ጥቀርሻ›› ከሚለው ቴአትር 0.15 ሳንቲም ብቻ እንደተከፈላቸው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሀገር ፍቅር ቴአትር ለአንድ ሰው መግቢያ 90 ብር እንደሚያስከፍል፣ ከሚገኘው የቴአትር ገቢ ውስጥ ጸሐፌ ተውኔቱ ጋ ከመድረሱ በፊት ለትኬት ቀረጥ 20 በመቶ፣ እንዲሁም ለትኬት ማሳተሚያ 5.42 በመቶ እንደሚቆረጥ ተገልጿል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ወጪዎች በኋላ የተገኘው ገቢ ድጋሚ ወደ መቶ ፐርሰንት ይቀየርና ለቴአትር ቤቱ ድርሻ 50 በመቶ፣ ለደራሲው ደግሞ 30 በመቶ እንደሚከፈል ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...