- ከታሰበው አራት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ የተገኘው 27 በመቶው ብቻ ነው ተብሏል
የሰብዓዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ድጋፍ የሚያደርጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኤጀንሲዎች፣ በኢትዮጵያ ቁጥርራቸው እየጨመረ ላሉት ቀውሶች ሁሉ ድጋፍ ማድረግ እንደማይችሉ አስታወቁ፡፡
በተያዘው ዓመት ኤጀንሲዎቹ በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ሰብዓዊ ድጋፍ ተመድ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ቢያስታውቅም፣ እስካሁን የዕቅዱን 27 በመቶ ብቻ ከአጋዥ ተቋማት ማሰባሰቡ ተገልጿል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2022 ከ21 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በትንሹ አንድም ጊዜ ቢሆን ድጋፍ አድርገው የነበሩት የተመድ ተቋማት፣ እ.ኤ.አ. በ2023 በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 17.3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ምግብ ነክ የሆኑና 5.2 ሚሊዮን ዜጎች ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎችን ማቅረባቸውን፣ የተመድ የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ኃላፊ አስተባባሪ በጽሑፍ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ቀንን በማስመልከት ማክሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ተቋም የኢትዮጵያ ዋና መሥሪያ ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ በመግለጫውም የዩኤን ኦቻ የኢትዮጵያ ዋና ኃላፊ ሚሼል ሳአድ እና የፍልሰተኞች ተቋም የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዋና ኃላፊዋ አቢባቶ ዌን ተገኝተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ በከፊል የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው፣ በዓለም ላይ የሚታየው የኢኮኖሚ አለመረጋጋትም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ኃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡
የተለያዩ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎች ሲያስፈልጉ የማስተባበር ኃላፊነት ያለበት የተመድ የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) ኃላፊ እንደገለጹት፣ እየተከሰቱ ያሉት ችግሮች ብዙ ዓይነት ድጋፎች እንደሚያስፈልጋቸው ነው፡፡
የተመድ ኤጀንሲዎች በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ‹‹ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ እየሰጠን እንደሆነ አድርገን አናስመስልም፤›› ያሉት የዩኤን ኦቻ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ሚሼል ሳአድ፣ ችግሮችን ለመቅረፍ በመዋቅር ደረጃ ሰፊ ድጋፎች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በሰላም ግንባታ፣ በዕርቀ ሰላምና በመልሶ ማዋሀድ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ ላይ ያተኮረ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ፣ በእነዚህ ድጋፎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ሰብዓዊ ቀውሶችን በሚገባ መቅረፍ እንደሚቻልም ነው ያስረዱት፡፡
የተመድ ኤጀንሲዎች ‹‹በጣም ጠቃሚ›› ድጋፍ እያቀረቡ እንደሆነ፣ ድጋፉንም የማይቀጥሉበት ከሆነ ሞት መከሰቱ የማይቀር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲዎቹ ከአጋሮች የሚመጡ የድጋፍ እጥረቶች እያጋጠሟቸው እንደሆነ፣ የሚሰጡዋቸው ድጋፎችም በምን ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የመወሰን አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡም ተገልጿል፡፡
‹‹አስቸኳይ የሕይወት ድጋፍ ፍለጋ የሚመጡ ሰዎችን ስናይ ጉልበታችንን በየትኛው ላይ እናድርግ በማለት አጣብቂኝ ውስጥ እንገኛለን፤›› ያሉት ዋና ኃላፊው፣ የተለያዩ ዓይነት ሰብዓዊ ዕርዳታዎች በአፋጣኝ የማይቀርቡ ከሆነ አስቸኳይ ዕርዳታዎች የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡
የተመድ የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ኃላፊ በመሆን በቅርቡ የተሾሙት ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) በጽሑፍ በላኩት መልዕክታቸው፣ ወደፊት የሚጠበቅባቸው ሥራዎች በጣም ከፍተኛ መሆናቸውንና ቁርጠኝነታቸውን ለማሳየት ለተረጂዎች ድጋፍ ማድረግ መቀጠል አስፈላጊነትን አሳስበዋል፡፡