Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ተጨናንቀናል!

ሰላም! ሰላም! ‹‹ሰላምታ የፈጣሪ ምሳና እራቱ ነው…›› የሚሉኝ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ ምንም የማይሳነው አምላክ የእኛ ሰላምታ ምሳና እራቱ ከሆነ፣ እኛም በፍቅር ሰላም ብንባባል እኮ ደስ ይለዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሰላማችሁ ይብዛ እላለሁ፡፡ እናንተን ሳገኝ የወሬ አባዜዬ ያንቀለቅለኛል አይገልጸውም። ‹‹ሲያንቀለቅልህ አዋዜ ወይ ሚጥሚጣ ላስ…›› ትል ነበር እናቴ። እኔ ግን በወሬ ተክቼዋለሁ። መቼም አንድ ቀን ብሎልን ነዳጅ ካወጣን መጀመሪያ ወሬን አጥፍተን መሆን አለበት። አሊያማ በሁለት ነዳጅ ስናልቅ ታሪክ ነጋሪ አናስተርፍም። እና መቼ ዕለት ለወሬ ነጋሪ እንዳንተርፍ አድርጎ የወሬኛ መንጋ ሊጨርሰን ነበር። ያውም ዋናው ከተማ አዲስ አበባ። ቦሌ አካባቢ አንድ የማሻሽጠው ቪላ ቤት ነበረኝ። ከየት መጣ ሳይባል ታዲያ የወሬ መንጋ ቦሌን በቁጥጥሩ ሥር ያዋለው ይመስል ወሬ በየዓይነቱ ይሰለቃል። አንዱ ይነሳና አይፎን ፕሮማክስ ስልኩን እያወዛወዘ፣ ከውስጡ የቃረመውን ወሬ ይተነትንልን ጀመር፡፡ ‹‹አዳሜ ያለሽ መስሎሽ ከሆነ ተሳስተሸል…›› እያለ ትኩረታችንን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ይውረገረግብናል፡፡ ይበለን!

በዚያ ሰዓትና ሥፍራ እግዜር ለምን እንደከሰተኝ ቆይቶ ነበር የገባኝ። ምክንያቱማ ባለአይፎኑ ዋናው ጉዳዩ እንደ ሽንጥና ዳቢት የሚመትረው ወሬ ሳይሆን፣ በቅርቡ ከአሜሪካ የተላከለትን ፕሮማክስ 14 ለቢጤዎቹ ለማሳየት የሸረበው ሴራ ነበር። ፈጣሪ በሰጠን ፀጋ ሠርተን መለወጥ ያለብን ሰዎች በሠራነው ሳይሆን፣ በገዛነው ወይም በተመፀወትነው ቅራቅንቦ ስንሸልል ቃር ቃር ይለኛል። ይኼ ያልኳችሁ ሰውዬ አንዴ ደላላ ሌላ ጊዜ የሀብታሞች አጫዋች በመሆን እንደ ካርታ ቁማርተኛ ወንበሩን ለዋዋጭ ስለሆነ፣ ሁሌም የሚያሳየው ባህሪ በጣም ተገለባባጭ ከመሆኑ የተነሳ ጓደኞቹ ሳይቀሩ ‹‹ሸርተቴ›› ነው የሚሉት፡፡ አዲስ ጃኬት፣ ሱሪ፣ ሸሚዝ፣ ኮፍያ ወይም ሰዓት የቀየረ እንደሆነ እሱን ለማሳየት የማይሆነው ነገር የለም፡፡ አንዱ ዳላላ ወዳጃችን፣ ‹‹ሸርተቴ እኮ በአምስት ሺሕ ብር የገዛውን ጃኬት ለማስመረቅ ሃምሳ ሺሕ ብር ያጠፋል…›› ካለ በኋላ የእሱ ነገር በቅቶኛል፡፡ ዛሬም ወዳጁ የላከለትን ዘመናዊ አይፎን ለማሳየት በሐሰተኛ ወሬ ሲጋጋጥ፣ ‹‹እንዴ አቶ ሸርተቴ አንተ ብቻ ነህ እንዴ እሱን ነገር የያዝከው…›› ብዬ ወደ ኪሴ ዘው ብዬ ለመግባት እጄን ስሰድ፣ በብርሃን ፍጥነት በድንጋጤ ከአካባቢው ለመሰወር ሲጣደፍ ከኋላው እንደ መድፍ የተከተለው የደላሎች ሳቅ ሁለተኛ እዚያ አካባቢ የሚያደርሰው አይመስልም ነበር፡፡ ሸርተቴ እኔ ይኑረኝ ወይም አይኑረኝ ሳያውቅ ‹‹በጨበጣ›› ደንግጦ መሮጡ ከወቅቱ የፖለቲካ ጉዳያችን ጋር ተያይዞ ብዙ ተወራበት እላችኋለሁ፡፡ ተገኝቶ ነው አትሉም!

ምን እያወራሁ ነበር? የእኛ ሰው እርስ በርሱ በከንቱ ነገር ሲጨፈላለቅ መኖሩን፣ አሁንም እንዳለቀቀው ለራሴም ማስታወስ ነበረብኝ። ታዲያ ትውስታ እንኳን የእኔ ቢጤ የደነገጡትን፣ አደብ የገዙ የተባሉትንም እያቀዣበረ መሆኑን ከእናንተ በላይ ታዘብኩ አልልም። ይገርማችኋል ከልጅነቴ ጀምሮ በሁለት ነገር እንዳልሞት አጥብቄ እፀልያለሁ። አንዱ በዕባብ መርዝ ነው። ይኼኛው ፀሎቴ ልክ እንዳልነበር ያወቅኩት ከዕባብ ይልቅ የሰው መርዛማ ድርጊት እንደሚከፋ ሳይ ነው። ሁለተኛው ግን ስህተት የተገኘበት አልመሰለኝም። እንዲያውም የወሬ አምሮት እንዳይገለኝ የፀለይኩት ምን ያህል በፈጣሪ እንደተደመጠ እንዳይ ይመስላል፣ የዘመናችን የወሬ ሠራዊት ኑሮ በቁሙ እንዲያጎላጅ የፈረደበትን ወገኔን ሀቲቱን ሲበላው ሁሌም መሀል እገኛለሁ። ‹‹ቆይ ግን እኛ ምንም ሳንበላ በሂያጅና በመጪ አጉል ተስፋ ገንዘባችንና ጉልበታችን እየተበላ እስከ መቼ ነው የምንዘልቀው?›› ትናንት ከእነ እንቶኔ ጋር ‹‹…አሼሼ ገዳሜ መቼ ነው ቅዳሜ…›› ይሉ የነበሩ ቱልቱላዎች ድንገት ተገልብጠው አሠላለፍ ሲቀይሩብን በቃ አንነቃም ማለት ነው። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አንድ ቀን በእግራችን ወደ እንጦጦ ረጅም ጉዞ ለማድረግ ስንራመድ፣ ‹‹ችግሩ ከእኔ ይሁን ወይም ከሌላ እንደሆነ ባይገባኝም የዚህ ዘመን ሰው ባህሪ ፈፅሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ትናንት የቆመበትን ቦታ የፅድቅ አድርጎ ሲደሰኩር የነበረ ዛሬ ድንገት መጥቶ ያንን የፅድቅ ቦታውን የኩነኔ መቀፍቀፊያ ነው ሲል በቂ ማብራሪያ ሲሰጥ አላይም፡፡ ይህ ባህሪ የብዙ ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው መሆኑ ደግሞ ድንቅ እያለኝ ነው…›› ብሎኝ ነበር፡፡ እኔ አዳመጥኩት እንጂ ምላሽ አልነበረኝም፡፡ ከየት አምጥቼው!

ካልታሰበው የወሬኛ መንጋ ተነድፎም ሳይነደፍም ሮጦ ያመለጠ፣ ትንፋሽ ለመሸብሸብ የሆነ ጥግ ይሰባሰብና ያንን ያረጀና ያፈጀ ጭቅጭቅ ይጣድበታል። ‹‹መቶ ሜትር የማትሆን ሮጠን ማራቶን እንደ ሮጥን ሁሉ በንዴት ስናለከልክ ለታዘበን ትምህርት ላይ በእጅጉ መተኮር እንዳለበት ይረዳል። ኑሮ ራሱ አሲድ በሆነበት ዘመን በማይረቡ ጉዳዮች ሲቃጠሉ ውሎ ማደር ያስቆጫል…›› ይላል አንዱ በቦሌ መንገድ ላይ ሲራመድ ቆይቶ ትንፋሽ ለመውሰድ የቆመ እግረኛ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ። አንዷ ደገፍ ብላ የቆመች ደግሞ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ወይኔ አገሬ የጀግኖች አገር ትመስለኝ ነበር። በዚህ አያያዛችን ለጥቂት ጀግና አትሌቶቻችን ስንዘምር ብንኖር ምን ይገርመናል?›› አለች። ‹‹እሱን እንኳ ተይው፣ እኔ የምለው ግን እኛ ያለ ምንም ችግር እንደምናቦካው አሉባልታ ፖለቲከኞቹ ቁጭ ብለው ለማውራት ምነው አቃታቸው?›› ብሎ ሌላው ወሬውን ጀመረ። ድካሙ እስኪለቀው ጊዜ ወስዶ እየተረጋጋ የነበረው ወገን ድንገት ተገናኝቶ ሌላ ሽኩቻ ውስጥ ገባ። ‹‹እንዲያማ ሊሆን አይችልም። እነሱ እኮ ዋናው ጉዳያቸው ሥልጣንና የሚያስገኘው ጥቅም እንጂ፣ ለእኛ አስበው ለመነጋገር ይቀመጣሉ ብለሽ አታስቢ…›› ብሎ ነገሩን አጦዘው። ምፀቱ የምር የመሰለው ነፍሱ ስትጨነቅ ይታያል። ቀሪው ያላግጣል። በመሀል አንዱ ሲጋራ አውጥቶ ይለኩሳል። ‹‹ወንድም ሕዝብ በተሰበሰበበት መሀል ማጨስ በሕግ የተከለከለ ነው…›› ይለዋል አጠገቡ የቆመ አፍለኛ ወጣት፣ ‹‹መበተን ነዋ፣ ወትሮም መንጋ የሚበተነው በጢስ ነው…›› ሲል ሁሉም መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ይገርማል!

እኔም በአፍለኛው ማሳሰቢያ ሳይሆን ጉዳዬ ሰዓቱ ደርሶ ከስብስቡ ተለየሁ። ያልኳችሁን ቪላ አዋክቤ አከራየሁና ኮሚሽኔን ስቀበል ሆዴ ሲጮህ ሰማሁ። ነገር ስበላ ምግብ አለመብላቴን ረስቻለሁ። ወደ ቤቴ ልሄድ ስል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወለ። ‹‹እህ?›› ስለው፣ ‹‹ምሳ እየበላን የማዋይህ ነገር አለ ቶሎ ድረስ…›› አለኝ። ወደ ፒያሳ ገሰገስኩ። እንዳየኝ ጠኔ እንደጠናብኝ ከፊቴ አንብቦ፣ ‹‹በል ቶሎ ወደ ሸራተን…›› ሲለኝ ልቤ ተንሸራተተ፡፡ ‹‹ምን ልንሠራ?›› ስለው፣ ‹‹ምሳ ልንበላ…›› አለኝ ከአፌ ነጥቆ። ‘ይኼ ሰውዬ ዛሬ ምሳዬን ሸራተን አብልቶ ቀሪውን ዘመኔን እንድራብ ይፈልጋል እንዴ? ምነው ፈጣሪ አንድ ያለኝን ወዳጅ ሳዝንበት ዝም ባትል?’ እያልኩ ተከተልኩት። ጥቂት ሄደን አንድ ምግብ ቤት ይዞኝ ገባ። አስተናጋጁ፣ ‹‹እንኳን ወደ ሸራተን በሰላም መጡ…›› ሲለኝ ነፍሴ ገባች። ለስሙ ብቻ ክፈሉ ካልተባልን የእኔም የእሱም ምሳ እንደ ወረደ ከምንጠጣው የእግዜር ውኃ ጋር ከ150 ብር እንደማይበልጥ አወቅኩ። የደሃ አምላክ የት ሄዶ ያለ ግጦሽ መሬታችን እንሰማራና? አስተናጋጁ በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም አንድ ነን በሚል መንፈስ በቀልጣፋ መስተንግዶው ሲያረካኝ ሳየው ወደ ባሻዬ ልጅ ዘወር ብዬ፣ ‹‹ምናለበት የዴሞክራሲ ጠበቆች ነን የሚሉንም እንዲህ ቆመንለታል ለሚሉት ጉዳይ ዕውን መሆን በቅንነት ሲተጉ ብናይ?›› ማለት መቼም አፌ አያርፍ፡፡ ‹‹እነሱም የመፈተኛቸው ጊዜ ሲደርስ እንደ ይሁዳ ባይከዱን ለማለት ፈልገህ ነው?›› አለኝ። እሱም አፉ አያርፍ!  

ሆዳችንን ሞልተን ስናበቃ ለምን እንደፈለገኝ ስጠይቀው ለሽምግልና እንደሆነ አጫወተኝ። ‹‹ሽምግልና?›‹‹ ስለው አንድ የማውቀውን ስም ጠርቶ፣ “ይኼው ሁለት ዓመቱ 50 ሺሕ ብር ተበድሮኝ አልመለሰም። ጭራሽ መስከረም ላይ ቀለበት ያስራል። ደግሞ ከስንት ሰው መሰለህ ተበድሮ ሰው እያስለቀሰ ያለው?›› አለኝ። ‹‹እና?›› ስለው፣ ‹‹ብሩን ባይመልስ ቢያንስ በሕዝብ ገንዘብ ቀለበት መንገድ እንጂ ቀለበት እንደማይታሰር ሊገባው ያስፈልጋል። ምነው ሰው ይኼን ያህል ኃፍረት ራቀው?›› አለኝ። አንዴ ሳልወድ ታጭቻለሁና ሌላ አንድ ወዳጄን አስከትዬ ከመሄዴ በፊት ስልክ ደወልኩ፣ ተበዳሪው አነሳው። ለምን እንደፈለግኩት ጫፍ ጫፉን ስነግረው፣ ‹‹… ቆይ መልሼ ልደውል። አንዴ… አንዴ…›› ብሎ ስልኩን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነኝ በል አለው። ዕድሜ ለስማርት ስልኮች ደሃም ብንሆን ሰው መሆናችን እንዴት እንደ በጀን ዘንድሮ አየን። ከኔትወርክ ክልል ውጪ ነኝ በማስባል ደዋዩን እንደ ዕብድ ውሻ ቆጥሮ እሱ ባለበት አልገኝ ማለት ሌብነት ነው። ይኼ ደግሞ ጉድጓድ ቆፍሮ በቁም ከመቅበር አይተናነስም። አቤት ስንቱ ይሆን ኔትወርክ ሥር የተቀባበረው ዘንድሮ!

ሽማግሌ የተባልኩት ሰውዬ መናደድ ጀመርኩ። እንደ ፀበኛ ሰተት ብዬ ቤቱ ስሄድ አገኘሁት። ሲያየኝ ቆፍጠን ብሎ፣ ‹‹እኔ ከአንተ ይኼን አልጠብቅም፡፡ ቀጥረኸኝ መልሼ ስደውል ስልክህን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ታስብላለህ?›› ብሎ ወቀሰኝ። አቤት? ስንት ፈጣጣ አለ እባካችሁ፡፡ እንዲያው ልክ ልኩን ነግሬው ዛሬ ወጥቶልኝ ስል ደግሞ ቀድሞኝ፣ ‹‹ይልቅ በጣም ስፈልግህ ደረስክ። በመስከረም ቀለበት አስራለሁ። ቀለል ያለ ምሳ ነገር ይኖራልልና እንዳትቀር አደራ፡፡ የፈለግኩህ ከአንድ ሁለት ሳምንት በኋላ የምመልስልህ 50 ሺሕ ብር እንድታበድረኝ ነው…›› ብሎኝ አረፈው። እኔ ምለው ኑሮ በክሬዲት ሲደራ ምነው ሳትነግሩኝ? ‹‹ምን ዓይነት ዘመን ነው ዘመነ ፈጣጣ፣ ባል ተቀምጦ ውሽማ ሲመጣ…›› አለ ያገሬ ዘፋኝ፡፡ ለሽምግልና የሄድኩት ሰውዬ በሽማግሌ ተገላግዬ የሌለብኝን ሙልጭ አርጌ ተሳድቤ የኮሚሽን ገንዘብ ልሰጥ ወደ ውዲቷ ማንጠግቦሽ ገሰገስኩ። ለወትሮው ስንትም ብሰጣት የምታምነኝ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ዓይኔ እያየ ምራቋን ‘ቱ…ቱ…’ እያለች ደጋግማ ገንዘቡን ስትቆጥር አየሁ። የማልም መሰለኝ። ለአንድም ቀን ተጠራጥራኝና ፈትሻኝ የማታውቀዋ ባለቤቴ የሰጠኋትን ገንዘብ ስታበጥር ሳያት ከየት እንደመጣ አላውቅም ይሁዳን የማይ መሰለኝ። ቆጥራ ስትጨርስ ከመቀመጫዋ ተነስታ ጉንጬን ስትስመኝ በፍርኃት ተርበደበድኩ። ‹‹ምነው?›› ስትለኝ ሁኔታዬን ታዝባ እኔ ‹‹የፈጣሪ ያለህ…›› እላለሁ። የቁም ቅዠት ጨረሰን እኮ እናንተ!

በሉ እንሰነባበት፡፡ ማንጠግቦሽ ወደ ገበያ ስትሮጥ እኔ ወደ አዛውንቱ ባሻዬ ቤት ተጣደፍኩ። በእርጋታ ከልጃቸው ጋር እየተጫወቱ የነበሩት ባሻዬ ትኩር ብለው ሲያዩኝ ቆይተው፣ ‹‹ምን ሆነሃል?›› አሉኝ። ‹‹ባሻዬ ይሁዳን አየሁት መሰለኝ?›› አልኳቸው። እንደ መሳቅም እንደ መገረምም ብለው የት እንዳየሁት ሲጠይቁኝ ሁሉንም ተረኩላቸው። ‹‹ዘመኑን ነዋ ያየኸው፣ ዘመኑን ነው፡፡ በይሁዳ ተመስሎ ያየኸው ዘመኑን ነው፡፡ ያቺ ሰላሳ ዲናር ምንዛሪዋ እያደር ጨምሮ ይኼው ሕዝበ አዳም ለገንዘብና ለሥልጣን የማይሆነውን እየሆነ እሱነቱን ክዷል፡፡ በሕዝብ፣ በወገን ሀብት አላግጦ ሲኖር አንዳች ፀፀት የሚሰማው አይመስልም። ይሁዳን ሳይሆን ያየኸው የይሁዳን መንፈስ፣ ስግብግብነት የፀነሰውን የፈረሰ እምነት፣ የቀዘቀዘ ፍቅር፣ የክፋት አባዜ ነው። እሱን ዓይተህ ነው…›› አሉኝ። ‹‹እኮ የዘመን ትንሳዔ የለውም ነው የሚሉኝ ባሻዬ?›› ብዬ ብጠይቃቸው፣ ‹‹እሱን ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው…›› ብለው ዝም አሉ። በዝምታችን ውስጥ የፊቱ ወደ ኋላ የኋላው ወደ ፊት ያልተገለበጠበት፣ የግራው ወደ ቀኝ የቀኙ ወደ ግራ ያልተቀያየረበት ዘመን መጠማታችን ታውቆናል። የዘመን ትንሳዔ ናፍቆት አቁነጠነጠኝ። እንዲያው ወገኖቼ ስንቱ ነገር ነው የሚያቁነጠንጠን? እኔማ ብዙ ነገራችን ግር እያሰኘኝ ነው፡፡ ትልቅ የተባለው ትንሽ ሲሆን እያየሁ ማፈር ጀምሬያለሁ፡፡ የተከበረ የሚባለው ከእነ ውርደቱ ሲንጎማለል ጥፍሬ ውስጥ መደበቅ አምሮኛል፡፡ አንዳንዴ ይህንን ጉድ በጊዜ እንዳላሳብብ ሰውን የሚያህል ትልቅ ፍጡር ነው ዋናው ባለጉዳይ፡፡ አጥፊውም አልሚውም ማለቴ ነው፡፡ ብቻ ይጨንቃል! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት