Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየደቡብ ኮርያ መንግሥት ለኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ የ300 ሺሕ ዶላር ፕሮጀክት አስጀመረ

የደቡብ ኮርያ መንግሥት ለኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ የ300 ሺሕ ዶላር ፕሮጀክት አስጀመረ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የሚገኙና የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ንብረት የሆኑ መገልገያዎችን ለማደስና ለመጠገን የደቡብ ኮርያ መንግሥት የ300 ሺሕ ዶላር ፕሮጀክት አስጀመረ፡፡

ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመተግበር ላይ ለሚገኘው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የደቡብ ኮርያ መንግሥትና ሕዝብ ሲሸፍኑ፣ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት እየተከታተለ ዳር የሚያደርሰው ዋና መሥሪያ ቤቱን በኮርያ ያደረገው ‹‹ወርልድ ቱጌዘር ኢትዮጵያ›› የተባለ የዕርዳታ ድርጅት መሆኑን የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር አስታውቋል፡፡

በፕሮጀክቱ ከታቀፉት ሥራዎች መካከል፣ አፍንጮ በር አካባቢ የሚገኘው የመታሰቢያ ፓርክ የሚያስገባውን ዋናውን በር ዘመናዊ ማድረግ፣ ከዋናው በር አንስቶ በኮርያ ጦርነት ለተሰዉ ኢትዮጵያውያን ዘማቾች መታሰቢያ የቆመው ሐውልት ድረስ የተዘረጋውን የአስፋልት መንገድ ማሻሻልና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎችን ማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ጽሕፈት ቤት የሆነውን ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ዕድሳትና ጥገና ማድረግም የፕሮጀክቱ አካል ነው፡፡

በኮርያ ጦርነት የተሰዉ ኢትዮጵያውያን ዘማቾች ፎቶግራፋቸው የተለጠፈበትና ስሞቻቸውም የተጻፈበትን ሐውልት ማደስ፣ አካባቢውን በፋውንቴንና በኤሌክትሪክ ብርሃን ማስዋብና ከማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ጋር ተያይዞ የሚገኘውን ሙዚየም ማስፋፋት፣ ማደስና ማስዋብ በፕሮጀክቱ ተይዟል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ሌተና ኮሎኔል ሸን ጂ፣ ፕሮጀክቱ ታሪካዊ የሆነውን ቅርስ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው፣ ይህም የኢትዮጵያንና የደቡብ ኮርያን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡

የወርልድ ቱጌዘር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሲዎንሞክ ሊ፣ ለደቡብ ኮርያ ሕዝብ ሰላምና ነፃነት መስዋዕት የሆኑ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾችን የኮርያ መንግሥትና ሕዝብ ምንጊዜም እንደማይረሷቸው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ኮርያ የላከችበትን 72ኛ ዓመትና ደቡብ ኮርያና ኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበት 60ኛ ዓመት በሚከበርበት ወራት የፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር ድባቡን ልዩ እንደሚያደርገው የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን በተወረረችበት ጊዜ (1928-1933) ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀድሞው ሊግ ኦፍ ኔሽን ቀርበው ‹‹አንድ አገር አንዲትን አገር መውረሩ አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ጦርነቱን አስቁሙልን፤›› የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ግን ለጥያቄው ጆሮ ዳባ በማለት ምንም ዓይነት መልስ ሳይሰጣቸው መቅረቱን ገልጸዋል፡፡

ጊዜው አልፎ ሌላ ጊዜ ሲመጣ ደግሞ ደቡብ ኮርያ በአንድ ኃያል አገር እንደተወረረች፣ ኢትዮጵያ በጭንቀቷ ጊዜ ችግሯን ሰሚ ብታጣም፣ ትናንሽ አገሮች በትላልቅ አገሮች መወረር የለባቸውም ከሚለው ጽኑ እምነቷ ተነስታ ወታደሮቿን ወደ ኮርያ ማሰማራቷን ኮሎኔል እስጢፋኖስ አስታውሰዋል፡፡

ጦርነቱ አብቅቶ በሁለቱ አገሮች መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ፣ ለደቡብ ኮርያ ሰላምና ነፃነት ሲታገሉ የተሰዉት ወታደሮች አጽምና በሕይወት የተረፉት ወታደሮች ወደ እናት አገራቸው እንደተመለሱ፣ የተሰዉ ወታደሮችም አጽም በክብር እንዳረፈ፣ በሕይወት ላሉት ግን የኮርያ መንግሥትና ሕዝብ ልዩ ልዩ የሰብዓዊ ጽሑፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ከድጋፎችም መካከል በአዲስ አበባ ኤምሲኤም በሚል መጠርያ የሚታወቀው የኮርያ ሆስፒታል ለኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች በነፃ፣ ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ ግማሽ ዋጋ እያስከፈለ የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ይገኝበታል፡፡

ወርልድ ቱጌዘር ኢትዮጵያ፣ ኮኒካ እና ኤልጂ የተባሉት ኩባንያዎች የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፎችን ከማበርከታቸውም በላይ፣ ወርልድ ቪዥን ደግሞ ለገቢ ምንጭነት እያገለገለ ያለውን ባለ ሦስት ወለል ሕንፃ በነፃ ሠርቶ ለማኅበሩ ማስረከቡን ኮሎኔል እስጢፋኖስ አክለዋል፡፡

በደቡብ ኮርያኖች ትዕግሥትና ጥንካሬ አሸናፊነት ደቡብና ሰሜን ኮርያዎች አንድ የሚሆኑበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...