በሽተኞች – የታመምን
ልብስ የለሾች – የታረዝን
መከራ – የጋራ ሀብታችን
ጦርነት – ታሪካችን
ረሃብ – ዓርማ ቅርሳችን
ልማት – ምኞት ተስፋችን
እኛ ነን፡፡
ዘራችን ግንዱ አንድ ነው፡፡
በባዶ ሆድ – በጠኔ ቀጠና
በእርዛት
በሕመምና
ጦርነት
ተሰልቆ የተገነባ፡፡
በእግዜር ትዕዛዝ የማይፈርስ
በሕዝቦች ፀሎት ምኅላ፡፡
እኛ ነን፡፡
ባህላችን ግንዱ አንድ ነው
ተርቦ – የመጋደል
ለመብላት – የመሟሟት
ታሞ – የመታኮስ
ለመዳን – የመተራረድ
ታርዞ – የመጫረስ
ለመልበስ – የመጨፋጨፍ
እኛ ነን፡፡
- ፈቃደ አዘዘ ‹‹አሻራ››