Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብሔራዊ ባንክ የወሰነውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባርና ውጤቱን ከሥር ከሥር ሊገመግም ይገባል!

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአገሪቱ የተንሠራፋውን የዋጋ ንረት ለማርገብ ያስቸለኛል ያለውን ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ሰሞኑን በይፋ አሳውቋል፡፡ እወስደዋለሁ ያለውን ዕርምጃ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ዋነኛ መፍትሔ አድርጎ ያስቀመጠው ባንኮች የሚሰጡትን ብድር መገደብ ነው፡፡ መንግሥት ከብድር ላይ እጁን እንዲሰበስብ ያደርጋልም ተብሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞናዊ ውሳኔ መሠረት በተያዘው የበጀት ዓመት ሁሉም ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ከቀዳሚው ዓመት ከሰጡት ከ14 በመቶ መብለጥ የለበትም፡፡ ባንኮች በዚሁ ድንጋጌ መሠረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ 

‹‹ለዋጋ ንረቱ መባባስ ባንኮች የሚያበድሩት ገንዘብ ከፍ በማለቱ ነው›› የሚል አንድምታ ያለው ይህ የብሔራዊ ባንክ ዕርምጃ፣ ብድሩን በመገደብ የዋጋ ንረቱን መቀነስ እንደሚችል በማመን ውሳኔው ወዲያው ወደ ተግባር የሚገባበት በመሆኑ የማስፈጻሚያ መመርያውንም አውጥቷል፡፡ 

ይህንን በማድረግ በቀጣይ ሁለት ዓመታት የዋጋ ንረቱን ወደ አሥር በመቶ የማውረድ ዕቅድ ይዟል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማውረድ የያዘውን ውጥን ለማሳካት ተያያዥ ከሆኑ ዕርምጃዎች ጎን ለጎን እንደሚወሰድም ሰምተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት እጅግ አንገብጋቢ ለሆነው የዋጋ ንረት መፍትሔ ለማበጀት በዚህን ያህል ደረጃ ዝግጁ መሆኑ መልካም ነው፡፡ እስከዛሬ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተወሰዱ የተለያዩ ዕርምጃዎች የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ሊያመጡ ካለመቻላቸው አንፃር፣ ለየት ባለ መንገድ መፍትሔ ይሆናል ያለው ዕርምጃ ይሳካለት ዘንድም ምኞታችን ነው፡፡  

ዜጎች እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት ነገንም መቀጠል ያለባቸውና ብሔራዊ ባንክ በእርግጥም ይዞት የመጣው አዲስ የመፍትሔ ሐሳብ ሊታገዝ የሚገባው ነው፡፡ በብዙዎች እምነት ግን የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የባንኮችን ብድር በመገደብ ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ከባድ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት እየተነሳ ነው፡፡

በተለይ የብድር ገደቡ ሌላ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይፈጥር የሚለው ሥጋት አንዱ ነው፡፡ ‹‹ገደቡ ኢኮኖሚው ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖም ምን ያህል ታስቦበታል›› የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ባንኩ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ሲወሰን በተያያዥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ያልታሰቡ ችግሮች በአግባቡ የሚመለስበት መላ ከሌለው፣ ለመልካም የታሰበው ዕርምጃ ችግሩን ሊያባብስ እንደሚችል መሥጋት ስህተት አይሆንም፡፡ 

ከሁሉም በላይ ግን የፋይናንስ ዘርፉን ተበዳሪዎች፣ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ሊኖረው ከመቻሉም በላይ የመንግሥትንም ገቢ የሚቀንስ ይሆናል፡፡ በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ መሠረት ባንኮች ሊያበድሩት ከሚችሉት ገንዘብ እስከ ግማሽ ያህል የሚሆነውን እንዳያበድሩ ሊያደርግ የሚችለው ይህ ውሳኔ፣ ትርፋቸውን በእጅጉ ይጎዳል፡፡ ባንኮች አብዛኛው የትርፍ ምጣኔያቸው በብድር ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም አንፃር፣ ወለድ ከፍለው ያሰባሰቡትን ተቀማጭ ገንዘብ መልሰው የማያበድሩ ከሆነ፣ ለተቀማጭ ገንዘብ መክፈል የሚጠበቅባቸው ወለድ ከፍ ማለቱ አይቀርም፡፡ 

ባንኮች የብድር መጠናቸውን በመገደብ ትርፋቸው ሲቀንስ ደግሞ ለባለአክሲዮኖቻቸው የሚከፍሉት የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ይቀንሳል፡፡ የትርፍ ግብርና የትርፍ ክፍፍል ግብርን ይቀንሳል፡፡ 

በኢትዮጵያ የግብር ሥርዓት ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ የሆነውን ግብር በመክፈል የሚጠቀሱ ናቸውና በሰሞኑ ዕርምጃ ብቻ ሊቀንስ በሚችለው ትርፋቸው መንግሥት ቀላል ያልሆነ ገቢ ሊያጣ እንደሚችልም ይታመናል፡፡ የባንኮች ሥራ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር የተያያዘ ነውና ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ገቢ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ 

ይህም ባንኮች የሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር በተለያዩ ቢዝነስና ኢንቨስትመንቶች በመሆኑ፣ እነዚህን ኢንቨስትመንቶች ደግሞ የኢንሹራንስ ሽፋን ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ የብድር ምጣኔው መቀነስ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኢንሹራንስ ሽፋን ሰጥተው ሊያገኙ የሚችሉትን ገቢ ይቀንሳል፡፡ ሌሎች እንዲህ ያሉ የተለያዩ ተፅዕኖዎች ሊከሰቱ የሚችሉ መሆኑ ይታመናል፡፡    

ስለዚህ ይህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ የቱንም ያህል ጠቃሚ ቢሆን፣ እንዲህ ያሉ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክፍተቶችን ለመድፈንና ሥጋቱንም ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ሒደቱን ሊወስናቸው የሚችሉ ተጨማሪ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከርና የመፍትሔ ሐሳቦችን ማሰባሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ 

በተለይ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በተከታታይ መምከር፣ የእነሱን ሐሳብ መቀበልና አሳማኝ ለሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦች አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ የሚፈለገውን ግብ ለማሳካት ይቻላል፡፡  

ሌላው መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የዕርምጃው አተገባበርና የተቀመጡ የ14 በመቶ የብድር ገደብ እንዴት ተሠልቶ እንዲተገበር እንደተፈለገ ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት ወደ 32 የሚሆኑ ባንኮች ያሉ ሲሆን፣ የእነዚህ ባንኮች ቁመና እኩል አይደለም፡፡ ባለፈው የሒሳብ ዓመት 30 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጠና ሁለትና ሦስት ቢሊዮን ብር ብድር የሰጡ ባንኮች በእኩል የብድር ምጣኔያቸው ማደግ ያለበት በ14 በመቶ ብቻ ነው ብሎ መደንገግ፣ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም የሚል መከራከሪያ እያስነሳ ነው፡፡ ተወዳዳሪነትንም ይነካል፡፡ ስለዚህ አዳዲስና የብድር ምጣኔያቸው አነስተኛ የሆኑ ባንኮች የብድር መጠናቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ይገታል፡፡ 

የብድር መጠናቸውን 30 እና 40 ቢሊዮን ብር ያደረሱ ባንኮች በድንጋጌው መሠረት በ14 በመቶ ብድራቸውን ሲያሳድጉ፣ አሁንም 40 እና 50 ቢሊዮን ብር የማበደር ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ዝቅተኛ ብድር ሲሰጡ የቆዩ ባንኮች የብድር ምጣኔያቸው ዕድገት በ14 በመቶ ብቻ የሚገደብ ከሆነ፣ በዚህ የዕድገት መጠን የብድር መጠናቸው ሲሠላ ከአንድና ከሁለት ተበዳሪ በላይ ለመስጠት የማያስችል በመሆኑ፣ መመርያው እንዲህ ያሉ ተፅዕኖዎች እንዳይኖሩና ያልተጠበቁ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ 

አነስተኛ ካፒታል ባላቸውና የብድር ምጣኔያቸው በዓመት ከአምስት ቢሊዮን ወይም ከአሥር ቢሊዮን ብር ሊበልጥ ያልቻሉ ባንኮች፣ የተሻለ ዕድል እንዳላቸውና ትልቅ የሚባሉ ባንኮች መታየት ስለሌለበት፣ መመርያው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መፈተሽ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ይህንን ዕርምጃ ለመውሰድ ብዙ ጥናቶችን አድርጎ እንደሚሆን ቢታመንም፣ አተገባበሩን አይቶ ከሥር ከሥር ማስተካከያዎችን ሊወስድ ይገባል፡፡ በተለይ መመርያውን በዋናነት ከሚያስፈጽሙት ባንኮች ጋር በቅርርብ መሥራት በርካታ ነገሮችን ለማስተካከል ይረዳል፡፡ 

ከዚህ ባሻገር ግን መመርያው ተፈላጊውን ግብ እንዲመታ እንደ ሸማች እንመኛለን፡፡ ዋናው ነገር በፋይናንስ ተቋማቱ፣ በመንግሥትም ሆነ በተበዳሪዎች መስዋዕት የሚተገበረው ይህ መመርያ በተጨባጭ የዋጋ ንረቱን የሚያቀል ይሁን፡፡ እኛም የዛሬ ሁለት ዓመት ‹‹የዋጋ ንረቱ ቀነሰ፣ ወደ አሥር በመቶ ወረደ›› ብለን ለመጻፍ ያብቃን፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት