የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከ500 ሺሕ በላይ ለሚገመቱ ለውጭ አገር ሕጋዊ ተጓዥ ሠራተኞች የመድን ሽፋን አገልግሎት ለመግዛት፣ ለአገር ውስጥ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያወጣውን ጨረታ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ማሸነፉ ታወቀ፡፡
መሥፈርቱን በተመለከተ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት የነበረውን ይህንን ጨረታ፣ ቀድሞ በተዘጋጀው መሥፈርት መሠረት ተካሂዶ ውጤቱ ይፋ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህ ጨረታ ለተወዳደሩ ከአሥር በላይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በደብዳቤ እንዳስታወቃቸው፣ የጨረታ አሸናፊው ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ነው፡፡ አሸናፊ የሆነበትን ዋጋም አሳውቋል፡፡
ለውጭ ተጓዥ ሠራተኞች አምስት የሕይወት የመድን ሽፋን ዓይነቶችን ለመስጠት በወጣው ጨረታ መሠረት፣ ለሁሉም የመድን ሽፋን ዓይነቶች ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ እከፍላለሁ ብሎ ያቀረበው የካሳ ክፍያ ዋጋ ተወዳዳሪዎች ካቀረቡት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ ያለው በመሆኑ አሸናፊ ሊሆን መቻሉ ታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ የዓረቦን መጠኑን በ500 ብር በመገደብ ነበር ጨረታውን ያወጣው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ዋነኛ መወዳደሪያ በ500 ብር ለአንድ ሰው ለሚሰጡት የመድን ሽፋን የጉዳት ካሳ ይህንን ያህል ክፍያ እንከፍላለን ብለው የሚያቀርቡት ዋጋ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በዚህ መሠረት ውጤቱ ይፋ መደረጉን የተገኘው መረጃ ያመለከታል፡፡
ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የጨረታ ውጤት መሠረት ኒያላ ኢንሹራንስ የተፈጥሮ፣ የድንገተኛ ወይም ራስን የማጥፋት አደጋ ሲያጋጥም ለአንድ ሰው 1.35 ሚሊዮን ብር የሚከፍል መሆኑን በማሳወቁ አሸናፊ ሊሆን መቻሉ ተሰምቷል፡፡
ለዘላቂ ወይም ለከፊል የአካል ጉዳት፣ ለአዕምሮ መታወክ፣ እንዲሁም ለአስገድዶ መደፈር ጉዳት የመድን ሽፋኖች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 1.25 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ለመክፈል ያስገባው የመወዳደሪያ አሸናፊ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ከእነዚህ አራት የመድን ሽፋን አገልግሎቶች በተጨማሪ ዜጎች በሄዱበት አገር የሞት አደጋ ካጋጠማቸው ለአስከሬን ማጓጓዣ፣ ለቀብር ማስፈጸሚያና ለንብረት ማጓጓዣ ተብሎ ለተጠቀሰው የኢንሹራንስ ዓይነት ደግሞ 250 ሺሕ ብር ካሳ እንደሚከፈል ታውቋል፡፡ ለእነዚህ ኢንሹራንሶች አገልግሎቶች ኢንሹራንስ የሚገቡት ሠራተኞች የሚከፍሉት ዓረቦን 500 ብር ብቻ ነወ፡፡ ይህንን በየዓመቱ በመክፈል አገልግሎቱን እንዲያገኙ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ጨረታ ከማውጣቱ ቀደም ብሎ ለውጭ ተጓዦች ለአምስቱ የመድን ሽፋን ዓይነቶች ይከፍል የነበረው ካሳ ከ40 ሺሕ እስከ 400,000 ብር እንደነበር ታውቋል፡፡ አሁን ግን የመድን ሽፋን አገልግሎት መሰጠቱ የመድን ሽፋን የሚገባለት ግለሰብ የተሻለ የካሳ ክፍያ እንዲያገኝ የሚያስችለው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህም በላይ በዚህ ጨረታ መሠረት የሚሰጠው የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰበሰበው የዓረቦን መጠን ከፍተኛ በመሆኑ፣ በቀጣይ ዓመታት የአገሪቱን የሕይወት የኢንሹራንስ ሽፋን እንደሚያሳድግ ይጠበቃል፡፡ በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ብዛት ያላቸው ሰዎች የሕይወት የመድን ሽፋን የሚያገኙበት ስለሚሆንም፣ ነጠላ አኃዝ ይዞ የቆየውን የሕይወት ሽፋን የዕድገት ምጣኔ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጨረታ ጉዳይ ከኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በቀጣይ ሳምንታት ከሚኒስቴሩ ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ ይገባል፡፡ በእነዚህ የኢንሹራንስ ሽፋን ዓይነቶች ተጠቃሚ የሚሆኑት ተጓዥ ሠራተኞች በሙሉ በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ ስለሚሄድና እስከ 500 ሺሕ ይደርሳሉ ተብሎ ስለሚገመት፣ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ለማስተናገድ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ አዳዲስ ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
ለዚህም ተጓዦች የኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ቅርንጫፎች ቀርበው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ ባሉበት ቦታ የኢንሹራንስ ሽፋኑን ለማግኘት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጨረታውን ሲያወጣ ተቃውሞ አስነስቶ የነበረው፣ በጨረታ መሥፈርትነት የቀረቡት መመዘኛዎች ብዙዎችን ያገላል የሚል እንደሆነ ይታወሳል፡፡ የጨረታ ውጤቱ ከተገለጸ በኋላ ቅሬታ ያላቸው ኩባንያዎች በአምስት ቀናቸው ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ሚኒስቴሩ ቢያስታውቅም፣ እስከ ዓርብ ምሽት ድረስ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳልቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡