Sunday, September 24, 2023

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በፓርላማ የተደመጡ የተለያዩ ሐሳቦች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ የሥነ ሥርዓትና የአካሄድ ጥያቄዎች በተነሱበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለተኛ ዓመት አንደኛ ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ሥራ በገባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች፣ ፓርላማውን በሐሳብ ክርክር ለሁለት ከፍለውት ነበር፡፡ በስተመጨረሻ በነበረው የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ግን አዋጁ በከፍተኛ ድምፅ ፀድቋል፡፡

ከክረምት የዕረፍት ጊዜው ላይ ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ፓርላማው ማክሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የጠዋት ስብሰባውን በዝግ ያካሄደ ሲሆን፣ ከቀትር በኋላ ያደረገው ስብሰባ ለሚዲያ ክፍት ሆኖ በአዋጁ ላይ ግልጽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ በፓርላማ የተደመጡ የተለያዩ ሐሳቦች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተቃውሞ ሐሳባቸውን ሲያቀርቡ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ‹‹የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ›› በሚል ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለማፅደቅና ይቀጥል አይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ ለመወሰን በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ 360 የምክር ቤቱ አባላት መገኘታቸው ተገልጿል፡፡ ስብሰባውን የመሩት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ለሚ በዶ ለአባላቱ የብሔር ስብጥርን መሠረት ያደረገና ለአንድ ወገን ያደላ የሚመስል ዕድል ለተናጋሪዎች ሰጥተዋል በሚል ከአንድ የምክር ቤት አባል ቅሬታ ቀርቦባቸው ነበር፡፡

በውይይቱ ወቅት ዕድል ካገኙት 16 አባላት መካከል ሁለት የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እና 14 የብልፅግና ፓርቲ አባላት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች አራቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ባለመሆኑ መንግሥት ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀምርና ምክር ቤቱም አዋጁን እንዳያፀድቀው የጠየቁ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 14 አባላት ደግሞ የአዋጁ መውጣት ጊዜውን የጠበቀና በአማራ ክልል የሚታየውን የሰላም ዕጦት ለመፍታት ወሳኝ ዕርምጃ ስለመሆኑ ተናግረው ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡ አዋጁ ከአጠቃላይ አባላት በ16 ተቃውሞ በ12 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

የመጀመሪያ ዕድል የተሰጣቸው የኦሮሚያ ብልፅግና ተወካይ አቶ ጆን አህመድ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜውን ጠብቆ የመጣ መሆኑንና ፓርላማው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 እንደተቀመጠው የመላው ኢትዮጵያ ወኪል በመሆኑ አዋጁን ሊቀበለው ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹በ1966 ዓ.ም. የከሰረ ትውልድ፣ ፈሪኃ እግዚአብሔር የሌለው ትውልድ›› በማለት ለአብነት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የተሰኙ የአሜሪካ ነዋሪ ግለሰብን በመጥቀስ፣ ‹‹በ1977 ዓ.ም. የተራበውን የጎንደር ሕዝብ ዘርፎ የሄደ ሰው ዛሬ እዚህ ሌላ ወጣት እንዲያልቅ የሚያነሳሳ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ አባል ከፈና ኢፋ (ዶ/ር) ባነሱት ጥያቄ፣ ‹‹ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በፅንፈኞች እንደሚወራበት የኦነግ ሠራዊት አይደለም፡፡ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተወጣጣ የአገር ኩራትና የአገር መከታ የሆነ በኢትዮጵያ አይደለም በአፍሪካ እጅግ ተፈሪ የሆነ፣ በዓለም በጥብቅ የሚታወቅ በአደረጃጀቱ እጅግ የዘመነ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንጂ የአንድ ብሔር ወይም የአንድ ግለሰብ ሠራዊት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአማራ ክልልንም ሆነ ኢትዮጵያን ሥጋት ውስጥ የጣሉ ጉዳዮች፣ ‹‹የተስፈኞች፣ የሕልመኞችና የቆሞ ቀሮች የቆየ፣ ያረጀና ያፈጀ አመለካከት ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡  

የፓርላማ አባሉ፣ ‹‹በአገር ላይ የጦርነት ከበሮ እየደለቁ ያሉት በሠለጠነ ዓለም የሚኖሩ፣ ነገር ግን ራሳቸው ያልሠለጠኑ ሰዎች ናቸው፤›› ብለው፣ ‹‹አገር የቀየሩ ነገር ግን ጭንቅላታቸው ያልተቀየረ ቆሞ ቀሮች፣ ዘመን ጥሏቸው የሄደ ሰዎች ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ መረጃ የሌለው የአማራ ወጣትና ሕዝብ እነዚህን ሰዎች ተከትሎ የእሳት ራት መሆኑና ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መጋጨት፣ መጣላትና ፀብ ውስጥ መግባቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ የአማራ ሕዝብ የሚጠቅሙትና የማይጠቅሙትን በሚገባ ለይቶ ማወቅ አለበት ብለዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ሰዎች በሚዲያ እየቀረቡ ትዕዛዝ በመስጠት የክልሉ መሪዎች እንዲገደሉና ክልሉ ያለ መሪ እንዲቀር በማድረግ መሪ አልባ ክልል እየፈጠሩ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

የፓርላማ አባሉ ‹‹ፅንፈኞች›› ባሏቸው አካላት በአንድ ብሔርና በአገር መሪ ላይ ትኩረት ያደረገ ዘመቻ መከፈቱንም ተናግረዋል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት እንዲፈተሹ የጠየቁት ከፈና (ዶ/ር)፣ ‹‹ፅንፈኞች›› በሚዲያ እየወጡ በአማራ ሕዝብ ላይ የታወጀውን ጦርነት የምትደግፍ ከሆነ በሚል በቤት ቁጥራቸውና ስልካቸው ለእያንዳንዳቸው ማስፈራሪያ እየተላከላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹እስካሁን በተደረገው ሁኔታ እነዚህ ፅንፈኛ ቡድኖች በአሸባሪነት ሊያስፈርጃቸው የሚችል መረጃ ይኑር አይኑር ዕውቀቱ የለኝም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ተጣርቶ እንዲቀርብና ውይይት እንድናደርግበት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አባል ሞላ ፈለቀ (ዶ/ር) በአመዛኙ በአዋጁ ዙሪያ ያጠነጠኑ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የክልሉ ፕሬዚዳንት የጻፉትን ደብዳቤ እንደ መነሻ ያደረጉት መሆኑን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ይህ ደብዳቤ በክልሉ አስተዳደር ምክር ቤት የወጣ መስሎ ስላላገኘሁት ከሕግ አንፃር እንዴት ሊሆን ይችላል?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ ምክር ቤት ስም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የመጠየቅ የሕግ መሠረት አላቸው ወይ? የሚል ተጨማሪ ጥያቄ አክለዋል፡፡

 ‹‹እኔ የክልሉ ሕገ መንግሥት ተጥሷል የሚል እምነት ስላለኝ የተሟላ፣ ግንዛቤ ይዘን እንድንሄድ የሚያስችል መረጃ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

 አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይቀርብና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሳይቋቋም፣ ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑ ምን ያህል የሕግ መሠረት አለው? የሚል ጥያቄም አቅርበዋል፡፡

አክለውም እስካሁን እየተፈጸሙ ያሉ ሒደቶችና ሁነቶች ያለመርማሪ ቦርዱ ክትትልና ቁጥጥር እንዴት ኃላፊነት መውሰድ ይቻላል? የሕግና የሕጋዊነት ጥያቄ አያስነሳም ወይ? በማለትም ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

በአዋጁ የተቋቋመው የጠቅላይ መምርያ ዕዝ አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የፈጸማቸውን ተግባራት ኃላፊነት ወስዶ ለሕዝብ ለምክር ቤት ሒደቱን መግለጽ አልነበረበትም ወይ? ሲሉም ሌላ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

በሌላ በኩል የተፈጻሚነት ወሰኑ ከአማራ ክልል አልፎ እንዲሄድ በመለጠጥ እንደ አስፈላጊነቱ ለየትኛው የአገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚ እንዲሆን መቅረቡ፣ በአንድ ክልል ውስጥ ሰላም ለማስፈን የታሰበን አዋጅ የተፈጻሚነቱን ወሰን ከዚያ የአስተዳደር ወሰን እንዲያልፍ መደረጉ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች የጅምላ እስራት አየተፈጸመ መሆኑ በአፈጻጸሙ የሚኖሩ ከፍተቶች እንዴት እንደሚፈቱ ጠይቀዋል፡፡

በአዋጁ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምርያ ዕዝ የተለያዩ የአስተዳደር ዕርከኖችና መዋቅሮችን መልሶ ማቋቋም፣ ማደራጀት ወይም የአስተዳደርና የፀጥታ መዋቅሮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍና የመወሰን ሥልጣንን በተመለከተም ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

‹‹ይህ በእኔ መረዳት ለአንድ ፌዴራላዊ አገር ወይም የፌዴራል ሥርዓት በሚከተል አገር፣ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለውን የሲቪል አስተዳደር በወታደራዊ አገዛዝ እንደሚዋቀር አድርጌ ወስጃለሁ፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሲቪል አስተዳደርን መልሶ ማደራጀትና ማዋቀር ከተቻለ ሙሉ በሙሉ በክልሉ አስተዳደራዊ ሁኔታ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመወሰን ሥልጣን ያለው በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 93 (2) ሀ መሠረት በማናቸውም ረገድ የማይገደቡ መብቶች ተደርገው ከሚቆጣጠሩት አንቀጽ 39 (1) ጋር የሚጋጭ ስለመሆኑ ሕጋዊ ክፍተት እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 8 (1) የቬዬና ኮንቬንሽን፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ደንቦች፣ ዕውቅና የተሰጣቸው የዲፕሎማቲክ መብቶች እንደተጠበቁ ሆነው ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጎች አዋጁ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተፈጻሚነት የላቸውም በሚል የቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ የሚያቋቁመውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መብት የሚጋፋ  ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ እንደሚሉት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሲቪል አስተዳደርን በወታደራዊ ዕዝ የሚቀይር፣ በአማራ ሕዝብ ወይም በአማራ ክልል የአስተዳደር ወሰን ውስጥ ጦርነት የማወጅ ዓይነት ይዘት ያለውና ከአስተዳደር ወሰን ያለፈ ነው፡፡

በዚህም ክልላዊ አስተዳደርን አልፎ እየተፈጸመ ባለው አዋጅ አሁን መሬት ላይ ካለው ሁኔታ አኳያ የሕግ መከበርና ሥነ ሥርዓት መኖር የታመነበት ቢሆንም፣ ትልሞቹ ተጨማሪ ሕዝብን የመግፊያና የመነጠል ባህሪ የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም መከላከያ ከትግራይ ክልል ዘመቻ እንደወጣ ሁሉ፣ አሁንም ሰላም እንዲገኝና ለአማራ ክልል አርሶ አደር የአዝመራ ወቅት በመሆኑ ንግግር እንዲጀመር፣ በድርድሩ ሒደትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ አቋቁሞ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ያ ካልሆነ ደግሞ ፓርላማው በክልሉ የማደራጀት ተግባር ውስጥ ተሳትፎ ኖሮት ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ማንኛውም አገራዊ ችግር ሲከሰት ከጦርነት ይልቅ ድርድርና ውይይት ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ሞላ (ዶ/ር) አክለው ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ አበበው ደሳለው በበኩላቸው በአማራ ክልል የተሰከተውን ችግር፣ ‹‹በተለያዩ የምክር ቤቱ አባላት እንደተባለው የጥቂት ቡድኖችና የታጠቁ ኃይሎች አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፣ ለረዥም ዓመታት እየተንከባለለ የመጣ የሕዝብ ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ከዚህ በፊት በነበረው መንግሥትም የጥቂት ቡድኖችና የዘራፊዎች ሐሳብ ነው እየተባለ፣ የሕዝብን ጥያቄ ገለል የማድረግ ጉዳይ አዋጭ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ እውነታው ላይ ተመሥርቶ መፍትሔ መፈለግ ላይ ትኩረት ቢደረግ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ችግር የተፈጠረው የአማራ ሕዝብ በሚኖርባቸው ክልሎች በተለይም በወለጋ የተለያዩ ዞኖች በተደጋጋሚ እየተገደለ በመሆኑ፣ የሚኖርበት ቤት ሕገወጥ እየተባለ እየፈረሰበት በመሆኑ፣ ዜጎች መንገድ ላይ እየታደኑና እየታፈሱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተጠየቀባቸው በመሆኑና በመጨረሻም ሕዝቡ ለሚተማመንበት የግብርና ሥራ የሚጠቀመው ማዳበሪያ ሊቀርብለት ባለመቻሉ ችግሮች ተደራርበው በሕዝቡ ላይ ብሶት በመፍጠራቸው ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በጎረቤት ትግራይ ክልል ያለው ሕወሓት ትጥቅ ሙሉ በሙሉ የፈታ ባለመሆኑና በኦሮሚያ ከኦነግ ሸኔ ሊደርስበት የሚችለውን ጥቃትና የህልውና ሥጋት በማሰብ ልዩ ኃይል ትጥቅ መፍታት የለበትም ብሎ ቢከራከርም፣ መንግሥት ማንንም ሳያማክር ልዩ ኃይሉን ለመበተንና ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ አክለውም አሁን የሚታየው ችግር የጥቂቶች ሳይሆን የመላው የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ለመምታት ጥረት ስለመደረጉም ገልጸዋል፡፡ እስከ ዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የምክር ቤት አባላት ቤታቸው ውስጥ  ተገብቶ ተደብድበው እስከ መታሰር መድረሳቸውን አውስተው፣ ፓርላማውም ማንኛውም የምክር ቤት አባል ተደብድቦ እስር ቤት ሲገባ ዝም ያለበት ምክንያት ምንድነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ሥራ እየተሠራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፅደቁልን ማለት፣ አሁንም ተጨማሪ የሕግ ጥሰቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን ማለት በመሆኑ ሊፀድቅ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ ነው ተብሎ ከታሰበው ዓላማ አንዱ የንፁኃን ግድያ በክልሉ መበራከቱ ነው ቢባልም፣ የንፁኃን ግድያን እያካሄደ ያለው ግን በመንግሥት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ለአብነት እንኳ በእኔ የምርጫ ክልል ጎጃም ፍኖተ ሰላም አካባቢ ትናንት በአንድ ቀን ከ60 በላይ ንፁኃን ተገድለዋል፤›› የሚሉት አቶ አበባው በባህር ዳር፣ በላሊበላ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጎንደር፣ በቡሬ፣ በጭልጋና በተለያዩ ከተሞች ግድያ እየተፈጸመ ያለው ከባድ መሣሪያ በያዘው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስለዚህ ሰላም የሚመጣውና ችግር የሚፈታው መከላከያና የመንግሥት ኃይል ከክልሉ ሲወጣ በመሆኑ፣ የበለጠ ኃይል በመጠቀም ችግር ሊፈታ አይቻልም ብለዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ያለውን ችግር የከፋ የሚያደርግና አገሪቱን የሚበታትናት በመሆኑ የሚሻለው ድርድር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሰሜኑን ችግር የፈታው በድርድር ሆኖ ሳለና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ድርድር  ጀምሮ እያለ፣ በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር ድርድር የማይደረገው ለምንድነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊፀድቅ አይገባም ያሉት አቶ አበባው፣ ‹‹አዋጁ ፀደቀ ማለት ተጨማሪ ንፁኃን እንዲሞቱና የፖለቲካ አመለካከት እየተለየ ዜጎች በጅምላ እንዲታሰሩ መፍቀድ ማለት በመሆኑ፣ አዋጁን ውድቅ እንድናደርገው እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ አብርሃም በርታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ከማርገብ ባለፈ መዋቅራዊ የሆነ አገር አቀፍ ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት መፍትሔ መስጠት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተከፈተበት የጠቀሱት አብርሃም (ዶ/ር)፣ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተቃጣው አደጋ በአገር ሉዓላዊነት እንደተቃጣ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግርና የክልሉ ችግር አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ የተደረገው የመንግሥት ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው በመሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቀዋል፡፡

አክለውም የኢትዮጵያ ሕዝብም ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ ሊያገኝ ይገባል ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ የመንግሥት ሚዲያዎች ለመንግሥት ፕሮፓጋንዳ በመዋላቸው በፅንፈኛ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ሕዝቡ እውነትን ሳያውቅ እየቀየረ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ገለልተኛ የሆኑ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓይነት ተቋማት የሚያቀርቡትን ምክረ ሐሳብ በትክክል መፈጸም ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ተወካይ የፓርላማ አባልና የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሰከን ብሎ ካልታሰበ በቀር ሰው ገድሎ፣ አስገድሎ፣ ሴራ ፈጥሮ፣ አሰቃይቶ፣ አቃጥሎ፣ የለህም ብሎ ክዶ ተጎዳሁ የሚለው ጩኸት ደግሞ ከየት እንደሚመጣ በጣም የሚገርም ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም እንዲህ እንዲህ ዓይነት የጠጠሩ ሁነቶችን በግልጽ ተነጋግሮ ካልተዳኙ በስተቀር፣ መሰል ሴራዎችንና ጥፋቶችን እየፈጸሙ መቀጠሉ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም፣ ‹‹በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ፋኖ ገድሎ አልታጠቀም፣ መከላከያን አድኗል፣ መከላከያ የዳነው በፋኖ ብቃት ነው፣ በውጊያው ወቅት ፋኖ የመሀል ተጫዋች ነበር የሚሉ ዓይነት ንግግሮች ልባችን የሚያውቀው እውነትና መሬት ያለው እውነት ግን ብዙ ሰዎች የረገፉበት በመሆኑ፣ እዚህ ምክር ቤት ላይ ቀርቦ ለማሳመኛነት ማቅረብ ብዙ የሚወስደን መንገድ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም መታጠቅ ካለበት አዋጅ አውጥተን እናስታጥቀው፡፡ ካልሆነ ግን ሌላው እንደፈለገ ገድሎ፣ አዘርፎና ዘርፎና፣ ታጥቆ መሣሪያን እንደ ጭራሮ እያወዛወዘ ሊያንበረከክ ከሚፈልግ ኃይል ጋር ምን ዓይነት አንድነት ነው የሚታሰበው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም ሕግ እንዲከበር ከተፈለገ ለአገሪቱ ትልቅ መረጋጋትና የሰላም ዕድል አዋጁን ፓርላማው እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡

የቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ፣ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሰጡት አስተያየት ‹‹አሁንም ካለፉት ጥፋቶቻችን መማር አለመቻላችን ያለፉት አምስት ዓመታት ያሳዩን፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ራሱ ፖለቲካዊ ችግር ፈጥሯል፡፡ ይህን ችግር ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት መንቀሳቀሱ ነው ችግሩ፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ያለው መንግሥት ባህሪ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

ፖለቲካዊ ችግሮችን በወታደራዊ ኃይል መፍታት ቢቻል ኖሮ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ምናልባት በምድር ላይ ሰላም የሰፈነባት አገር ትሆን እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለመፍታት በርካታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ታውጀው ተተግብረዋል፡፡ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜ ተቋቁመው ነበር፡፡ ነገር ግን አንድም ያቀለሉት ችግር የለም፡፡ የተወሰነ የሰላም ፍንጭ የታየው በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት በተሞከረባቸው አካባቢዎች ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ የትግራይን ጦርነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ያም የሆነው ከብዙ ዕልቂትና የጋራ ጥፋት በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ አስከፊ ጦርነት የቆመው በፖለቲካዊ መንገድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አሁን በአማራ ክልል የተፈጠረው የፖለቲካ ተቃውሞ በሚገባ መታወቅ እንዳለበት ተናግረው፣ የአማራ ሕዝብ ምናልባት ለማዕከላዊ መንግሥት ያደላ እንደሆነ እንጂ የመከላከያ ሠራዊትን ለመቃወም ፈልጎ ያደረገው ነገር አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለተፈጠረው ችግር መሠረታዊ ምክንያቱ የብልፅግና መንግሥት የፖለቲካ አመራሩ ውድቀት መሆኑን ጠቅሰው ምንም ሊሸፋፈን አይገባም ብለዋል፡፡

ካለፉ ስህተቶች ትምህርት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ገዱ፣ የሰፊው ሕዝብ ጥያቄ የሆኑና ወደ ጥፋት የሚያመሩ ጉዳዮችን ሰከን ብሎ ዓይቶ ከመፍታት ይልቅ የጥቂት ቡድኖች አድርጎ የመመልከትና ክብረ ነክ የሆኑ ፍረጃዎችን በማኅበረሰብ ላይ በማሳረፍ፣ ኅብረተሰቡ እንዲቆጣ በማድረግ የበለጠ ጥፋቱን ያባብሰዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ መጀመርያ ለብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ ደጋፊ የነበረው፣ ቆይቶም ተስፋ የተጣለበት የለውጥ እንስቅስቃሴ አቅጣጫውን መሳቱን ሲገነዘብ የመንግሥት ስህተቶች እንዲታረሙ አጥብቆ ሲቃወም እንደነበር አውስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ስህተቶች ከሚታረሙ ይልቅ በኢትዮጵያ ተከስተው በማያውቁ ደረጃ ተባብሰው በማንነት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተቃውሞ ለለውጥ የታገለው የአማራው ሕዝብ፣ ማንነቱን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ በተከታታይ እንደተካሄደበት ተናግረዋል፡፡ አማራው ከሚኖርበት ቀዬ በመቶ ሺዎች ተፈናቅሎ፣ ዕድሜ ልኩን ያፈራውን ሀብትና ንብረት በየቦታው ትቶ ለጉስቁልናና ለውርደት እንደተዳረገም አብራርተዋል፡፡

‹‹ይህንን በሰላም የመኖርና የፍትሕ ጥያቄ ሰሚ ሊያገኝ ቀርቶ መንግሥት በሚሰጣቸው የተለያዩ ፍረጃዎችና የተዛባ ትርጉም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ አማራን እረፍት መንሳት፣ ማፈናቀል፣ ሰበብ ፈልጎ መግደል፣ ማንገላታትና ማሰር የመንግሥት ተቋማት ተልዕኮ ያለ በሚስመል መልኩ በአስከፊ ሁኔታ ተገፍቶበታል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም አሁን እየተካሄደ ያለው የአማራ ሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተጠራቀመ ግፍና በደል የወለደው ቁጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹የአማራ ሕዝብ ከምር ተቆጥቷል፡፡ የተቆጣን ሕዝብ በኃይልና በወታደራዊ መንገድ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ችግሩን በቅንነት ለመፍታት ከተፈለገ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች ሲሞከር ከርሞ አገርን ወደ ከፋ ጥፋት የመራውን ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ሳይሆን፣ ፖለቲካ ውይይት ነው የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ያለው ችግር እንዲፈታና ሰላምና መረጋጋት ከተፈለገ፣ መከላከያ ሠራዊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ካምፑ እንዲመለስም ጠይቀዋል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብና የብልፅግና ፓርቲ ግንኙነት በማይጠገንበት ደረጃ ስለተበጠሰ፣ በአስቸኳይ ሁሉንም የአማራ ኃይሎች ያቀፈ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ችግሩን ማቃለል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል በሚታየው ተቃውሞ ዋነኛ ተዋናዮች አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችና የከተማ ነዋሪዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ዋነኛ ጥያቄያቸውም ሠርተው ለመኖር ሰላም፣ ለሚደርስባቸው በደል ፍትሕ፣ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽና መሰል ጥያቄዎች እንዲመለስላቸው ነው ብለዋል፡፡

በመንግሥት ደረጃ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት የሚደረግ ኃላፊነት የጎደለው ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁኔታው እንዲታረም አሳስበዋል፡፡ አቶ ገዱ የፓርላማ አባላት ይህንን አዋጅ ማፅደቅ እንደሌለባቸው፣ የሚያፀድቁት ከሆነ ግን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ሁሉም በየተራ ይደርሰዋል ብለዋል፡፡

አቶ ገዱ ጥያቄያቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት የምክር ቤት አባላት የአካሄድና የሥነ ሥርዓት ጥያቄ እየቀረበ በየመሀሉ ሲያቋርጧቸው ታይቷል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ የአካሄድና የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ሲያቀርብ፣ የሥነ ሥርዓትና የአካሄድ ይስተካከል ጥያቄ የአቋም ማንፀባረቂያ ሳይሆን ስብሰባው የሚመራበት ሥርዓት ከተጣሰ አንቀጽ ተጠቅሶ መቅረብ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አክለውም በመላምት የአካሄድና የሥነ ሥርዓት ጥያቄ መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የትርክት መዛባት እጅግ በጣም ውድ ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ፣ ይህን ነገር ለመቀየር ወንድማማችነትና እህትማማችነት አብሮነትና አንድነትን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መስበክ አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ሕዝቡን በሕዝብ ላይ ያነሳሳል በሚል የቀረበው የተሳሳተ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል ያለው የሕዝብ ጥያቄ የሚመለስበት መንገድ አሁን የተያዘው መንገድ ባለመሆኑ፣ ተመራጩ መንገድ ሰላምን ለማምጣት በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካይነት በአጭር ጊዜ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ይደረጋል ብለዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ በአማራ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት የፌዴራሉ መንግሥት የክልሉን ምክር ቤትም ሆነ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥያቄ ሳይቀርብ በራሱ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ሥልጣን አለው ብለዋል፡፡

አዋጁ በፓርላማ ሳይፀድቅ ዕርምጃ መወሰዱን በተመለከተ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ሁኔታው ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በራሱ ጊዜ አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ያለው ስለሆነ ለፓርላማው የቀረበው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሕግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የቀረበውን አዋጅ ምክር ቤቱ ተቀብሎ እንዲቀጥል ይፍቀድ አይፍቀድ የሚለውን ለመወሰን እንጂ ለማፅደቅ ብቻ አልነበረም ብለዋል፡፡ የተፈጻሚነት ወሰኑ ከክልሉ ወጣ ብሎ እንዲፈጸም መደረጉ የተፈጠረው ችግር ከክልል ተሻግሮ የመሄድ አቅምና አዝማሚያ ያለው በመሆኑ እንደሆነም አክለዋል፡፡

ይህም በመላምት ሳይሆን ቡድኑ በሚዲያ በሚሰማው ትንታኔና በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር መረጃ መሠረት፣ እዚህ እንጀምረዋለን እዚያ እንጨርሰዋለን በሚል የተቀመጡ ዓላማዎች ተይዘው በመንቀሳቀሳቸውና ግቡ አገራዊ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህንን የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈጻሚነት እንዲኖረው ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹መንግሥት ይደራደር፣ ይነጋገር፣ ፖለቲካዊ ውይይት ይኑር ለሚባለው ጉዳይ መጀመርያ መንግሥት መኖር አለበት፡፡ በክልሉ መንግሥት ከፈረሰ ውይይት ሊኖርና ፖለቲካዊ ድርድር ሊያመቻች የሚችል አካል የለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዳይፈርስ ለመጠበቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ዘላቂ የሆነ መፍትሔዎችን መፈለግ ያሻል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -