Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ላኪዎች የኮንትራት እርሻ ምዝገባ የሚያደርጉበት ቀነ ገደብ ተነገራቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራጥሬና የቅባት እህል ላኪዎች የውል እርሻ ልማት (የኮንትራት እርሻ) ስምምነት ማስመዘገብ የሚችሉት፣ እስከ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኮንትራት እርሻ ስምምነት በአርሶ አደሮችና በባለሀብቶች መካከል የሚደረግ ስምምነት ሲሆን፣ ዓላማውም አርሶ አደሮች ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ለምርት ማሳደጊያ ግብዓት የሚሆኑ አቅርቦቶችን ለማሟላት ነው፡፡ እንዲሁም ለአርሶ አደሮች አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል፡፡

በኮንትራት እርሻ አማካይነት የተገኘ ምርት ግብይት መመርያ ቁጥር 929/2015 መሠረት፣ አምራቾችና አስመራቾች የገቡትን የ2015 እና 2016 ዓ.ም. ምርት ዘመን ውል እስከ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስመዝገብ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የተሰጠው ቀነ ገደብ ካለፈ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጊዜው ሲደርስ በሚኒስቴሩ አመራሮች የሚገለጽ መሆኑን፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የቅጣት ዓይነቱን ማወቅ አለመቻሉን የሚኒስቴሩ ኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንት ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በኮንትራትና በኢንቨስትመንት እርሻ የተገኘ ምርት ግብይት መመርያ የግብይት ሥርዓታቸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያልፉ ምርቶችን በሚያመርቱና በሚገበያዩ አካላት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡ በመመርያው መሠረትም በአምራቾችና በአስመራቾች መካከል የተገባ ውል፣ በወቅቱ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ቀርቦ መመዝገብ እንደሚገባ መመርያው ይደነግጋል፡፡

በዚህ የውል ሥርዓት የተመረተን ምርት አምራቾችና አስመራቾች፣ በወቅቱ በአቅራቢያቸው የሚገኝ የምርት ገበያ ቅርንጫፍ ወስደው ማስመዘንና መገበያየት እንደሚገባቸው መመርያው ይገልጻል፡፡ 

የኮንትራት እርሻ ስምምነት ከማሳ ዝግጅትና ከምርጥ ዘር መረጣ አንስቶ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ የአግሮ ኢንዲስትሪዎች እየተስፋፉ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ላኪዎች የቅባት እህሎችና የእንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የኮንትራት እርሻ መመርያ አልሚዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር የምርት ማሳደጊያ ግብዓትና ቴክኖሎጂ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የኤክስፖርት ግኝትን ለማሳደግና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

የግብርና ምርት አመራረት ሒደቱ ለተለያዩ አደጋዎች የተጋለጠ በመሆኑ፣ ለምሳሌም በአየር ንብረት መለዋወጥና በበሽታ ወዘተ ምክንያት በውሉ መሠረት መፈጸም የማይቻልባቸው ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ መመሪያው ያብራራል፡፡ በዚህም የተነሳ በተዋዋይ ወገኖች መካከል አለመግባባቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ፣ የግብርና ምርት ውልን የተመለከተ በተለየ ሕግ የግብርና ምርት ልዩ ባህሪያትን ግምት ውስጥ ያስገቡ አለመግባባቶችን የመፍቻ መንገዶች በማመቻቸት፣ በተዋዋይ ወገኖች መካከል ፍትሐዊ ግንኙነት እንዲኖር እንደሚያስችል በመመሪያው ተካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች