Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፌስቡክና ቴሌግራም የተሰረቁ ዕቃዎች መገበያያ መሆናቸው ተነገረ

ፌስቡክና ቴሌግራም የተሰረቁ ዕቃዎች መገበያያ መሆናቸው ተነገረ

ቀን:

እንደ ፌስቡክና ቴሌግራም በመሳሰሉ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ለገበያ የሚውሉ የተሰረቁ ዕቃዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተነገረ፡፡ ከሞባልይ ስልክ ቀፎዎች ጀምሮ እንደ ላፕቶፕ፣ ቴሌቪዥንና ሌሎች ኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች፣ ጌጣጌጥና አልባሳት ጭምር የተሰረቁ ዕቃዎች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አማካይነት በሰፊው ለገበያው መቅረባቸው እየተለመደ መምጣቱን የፖሊስ መረጃም አመልክቷል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች የተሰረቁባቸውን ዕቃዎች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሲሻሻጡ አግኝተው መልሰው እስከ መግዛት መድረሳቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

በፌስቡክ መተግበሪያ በቀረበው ማርኬት ፕሌስ በተባለው መገልገያ በመጠቀም የተሰረቁ ዕቃዎች ልክ ከፋብሪካ እንደወጣ ሸቀጥ እንደሚቸበቸቡ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ መምርያ ባልደረቦች አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ በኩልም በቴሌግራም ጭምር የተዘረፉ ዕቃዎች እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ በተሰረቁ ዕቃዎች ወንጀል ክትትል ወቅት ይኸው የስርቆት ዕቃዎችን በቴክኖሎጂ የመገበያየት ሁኔታ በተደጋጋሚ እንዳጋጠማቸው ነው የመምርያው ፖሊሶች ያረጋገጡት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ላነሳላቸው ጥያቄ የተለየ ሪፖርት እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰረቁ ዕቃዎች ሽያጭ በዝቶ ከሆነ ክትትልና ግምገማ በማድረግ እንገልጻለን፤›› ሲሉ አጠር ያለ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

አንዳንድ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አጠቃቀም ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በኢትዮጵያ 20.86 ሚሊዮን ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ሲኖሩ፣ ከአጠቃላይ 124.9 ሚሊዮን የአገሪቱ ሕዝብ መካከል 83.3 በመቶው ኢንተርኔት ተጠቃሚ አለመሆኑ ይነገራል፡፡ በአገሪቱ በአጠቃላይ 66.80 ሚሊዮን ሕዝብ የእጅ ስልክ (ሞባይል) ተጠቃሚ መሆኑም እንዲሁ፡፡

አንዳንድ መረጃዎች በአገሪቱ ያለው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች አጠቃላይ ቁጥር ከ6.5 ሚሊዮን እንደማያልፉ ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚ ቁጥርን በየዘርፉ የሚያስቀምጡ የመረጃ ምንጮች፣ በኢትዮጵያ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቁጥር ብቻ 6.6 ሚሊዮን መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ፌስቡክን ተከትሎ የመልዕክት መለዋወጫው ሜሴንጀር 6.1 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን በኢትዮጵያ ማፍራቱን ያመለክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፌስቡክ መተግበሪያዎችን ተከትሎ ቴሌግራም በሦስተኝነት ከፍተኛ ተጠቃሚ እንዳለው ነው የሚነገረው፡፡

ውድ ንብረቶችን የተዘረፉ ግለሰቦች ቴክኖሎጂ የሰው ልጆች ችግር መፍቻ ሳይሆን ለክፋት እየዋለ ነው ይላሉ፡፡ የኢንተርኔት (ኦንላይን) ግብይት ሕግና ሥርዓት ተበጅቶለት ሊካሄድ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ የኦንላይን ግብይቱ ቁጥጥር ልል በመሆኑ ሕገወጥ ግብይትን ከማስፋፋቱ በተጨማሪ፣ ቀረጥና ግብር ሳይኖረው የመንግሥትን ገቢ በማሳጣት እንደሚካሄድም ይገልጻሉ፡፡

በኦንላይን ግብይት ከተሰረቁ ዕቃዎች በተጨማሪም ለሰዎች ጤና ጎጂነት ያላቸው የምግብ ሸቀጦችና መድኃኒቶች ጭምር እንደሚቀርቡ በመጥቀስ፣ መንግሥት በዘርፉ የተለየ የቁጥጥር ዘዴ እንዲዘረጋም አሳስበዋል፡፡

በአንድ አጋጣሚ ግምቱ ወደ 150 ሺሕ ብር የሆነ አይፎን ፕሮማክስ የተባለ ውድ የእጅ ስልክ የተዘረፉ አንዲት ግለሰብ፣ የተዘረፈባቸውን ንብረት በቴሌግራም ለገበያ ሲቀርብ መልሰው መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡት የግል ተበዳይ ንብረቱን የዘረፏቸውና መልሰው የሸጡላቸው ሰዎች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በሚገባ የሚያውቁና የሽያጭ ሒደቱን በጥንቃቄ የሚያካሂዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የግል ተበዳይዋ ለሕግ አካላት የሥርቆቱን ሪፖርት ቢያደርጉም ዕቃው በቀላሉ መገኘት ባለመቻሉ፣ እንዲሁም ከጠፋው ዕቃ ጋር በተያያዘ የሚጠፋባቸው የግል መረጃ በገንዘብ የማይተካ መሆኑን በማገናዘብ የጠፋባቸውን ውድ የእጅ ስልክ በ40 ሺሕ ብር ከሌቦቹ መልሰው መግዛታቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳይ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አያልነህ ለማ በበኩላቸው፣ ችግሩ ቴክኖሎጂ በጎም ሆነ መጥፎ ጎን ይዞ ከመምጣቱ ጋር የተገናኘ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ገበያና ግብይት የነበረና የግብይት ወንጀልም ያለ ጉዳይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አያልነህ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አዋጅ ቁጥር 1205/2012 የፀደቀለት መሆኑንና ችግሩ የሕግ አለመኖር እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የአዋጁ ዋና ዓላማ ኤሌክትሮኒክ ግብይትን መፍቀድና ቴክኖሎጂ ለግብይት እንዴት መዋል እንዳለበት ማስቀመጥ ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ገበያ ሻጭና ገዥ ብቻ ሳይሆን ሌባም እንዳለ ሁሉ፣ አሁን በተፈቀደው የኦንላይን ግብይትም ሌባው ሊስፋፋ ይችላል፤›› ሲሉ የአዋጁን መነሻ አስረድተዋል፡፡

ይህም ቢሆን ፖሊሶች (ሕግ አስከባሪዎች) በኤሌክትሮኒክ ገበያ የሚያጋጥሙ ወንጀሎችን እንዳይመረምሩ የሚከለክላቸው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ካሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የወንጀል ክትትላቸውን ዘመኑ (ቴክኖሎጂው) ከሚጠይቀው አሠራር ጋር አብሮ ማስኬድ እንደሚገባቸው ነው አቶ አያልነህ የጠቆሙት፡፡

‹‹የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ›› በ2012 ቢወጣም ይህን ጥቅል አዋጅ በማስፈጸሚያ መመርያዎችና ደንቦች በሥራ ላይ የማዋሉ ጉዳይ ግን ገና ብዙ እንደሚቀረው ይነገራል፡፡ የተሰረቀ ዕቃ በቴሌግራምና በፌስቡክ እያወጣ እንደ አዲስ ዕቃ የሚሸቅጥ ተጠርጣሪ በምን አግባብ እንደሚጠየቅ ግልጽ አሠራር አለመዘርጋቱ፣ ሕገወጦችን እያደፋፈረ መምጣቱን የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...