Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበትግራይና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል በአውሮፕላን ሊረጭ ነው

በትግራይና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል በአውሮፕላን ሊረጭ ነው

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

የግብርና ሚኒስቴር ከምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን፣ የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው የትግራይና የአፋር ክልሎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ በአውሮፕላን ኬሚካል ለመርጨት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ንጉሤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኬሚካል ርጭት የሚያደርጉት የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት አብራሪዎች ናቸው፡፡ አብራሪዎቹ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. መግባታቸውን፣ ወደ አፋር ክልል በማግሥቱ በመሄድ ለሥራው የሚሆን የቅድመ ዝግጅት እንደሚያደርጉ፣ ለዚህም ሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ማግኘታቸውን አቶ በላይነህ አስረድተዋል።

‹‹አሁን ያለው የአየር ፀባይ ለአንበጣ መንጋ መራባት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፤›› ያሉት አቶ በላይነህ፣ ‹‹የአንበጣ መንጋው ለሰው ኃይልም ሆነ ለተሽከርካሪ ምቹ ባልሆኑ ተራራማ አካባቢዎች ሲያርፍ ተስተውሏል፡፡ ኬሚካሉ በአውሮፕላን የሚረጭባቸው ቦታዎች በባለሙያ አሰሳ ተደርጎ የመለየት ሥራ ተሠርቷል፤›› ብለው፣ በዚህ መሠረት በተራራማና በሰው ኃይል መርጨት በማይቻልባቸው አካባቢዎች በአውሮፕላን እንደሚረጭ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ከትግራይና ከአፋር ክልሎች ባለሥልጣናት ጋር በመቀናጀት የአንበጣ መንጋ ፍልሰትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  እየሠራ ነው፤›› ያሉት ኃላፊው፣  የግብርና ሚኒስቴር ለክልሎቹ የፀረ አንበጣ ኬሚካል፣ የርጭት ተሽከርካሪዎችና የባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጫ ሰጥቷል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የአንበጣ መንጋ ወረራን ለመከላከል በክልሉ ግብረ ኃይል መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡ የአንበጣ መንጋ በሰብልና በደን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መከላከል እንደሚገባና ኅብረተሰቡ ለቅድመ መከላከል ሥራ በንቃት እንዲሳተፍ አሳስበዋል።

አቶ ጌታቸው በመግለጫቸው ሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች በሚባል ደረጃ በአንበጣ መንጋ መወረራቸውን፣ በአሁኑ ወቅት በሰብልና በደን ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን፣ መንጋውን ከመነሻው ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት የኬሚካልና የአውሮፕላን ድጋፍ እንዲያደርግ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

‹‹የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ትልቅ ዕርምጃ ነው፤›› ያሉት አቶ በላይነህ፣ መንግሥት ችግሩን በፍጥነትና በብቃት ለማስወገድ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በአንበጣ መንጋው ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብረ ኃይሎችና የአካባቢ ማኅበረሰቦች የጋራ ጥረት ወሳኝ እንደሆነና የመከላከያ ዕርምጃዎችን በመተግበር ረገድ የማኅበረሰብ ተሳትፎ  አስፈላጊ እንደሆነም አሳስበዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የአንበጣ መንጋውን አስከፊነት በመገንዘብ የግብርናውን ዘርፍና የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመታደግ ተገቢ ዕርምጃዎችን  በመውሰድ፣ የአንበጣ መንጋ ወረራን በፍጥነት ለማስወገድ፣ በምግብ ዋስትናና በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እየተሠራ እንደሆነ አቶ በላይነህ ጠቁመዋል፡፡ የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ቀውስ እንዳይፈጥር በግብርና ሚኒስቴር፣ በክልል ግብረ ኃይሎችና በአካባቢው ማኅበረሰቦች መካከል ትብብር  መፍጠር ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...