የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ክፍልፋይ ክልሎች አንዱ የሆነው አዲሱ ‹‹የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል›› ምክር ቤት፣ መሥራች ጉባዔ በመጪው ዓርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐዋሳ እንደሚካሄድ ተነገረ፡፡
ክልሉ ካቀፋቸው ከአምስቱ ዞኖች ማለትም ከከምባታ ጠምባሮ፣ ከሀዲያ፣ ከጉራጌ፣ ከስልጤና ከሀላባ፣ ዞኖች እንዲሁም ከየም ልዩ ወረዳ የተወከሉ የክልል ምክር ቤት አባላት ለስብሰባው ሐሙስ ሐዋሳ ገብተው እንዲያድሩ ጥሪ መተላለፉ ታውቋል፡፡
ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም፣ ደቡብ ኢትዮጵያ የተባሉ ሦስት ክልሎች በሕዝበ ውሳኔ መመሥረታቸውን ተከትሎ ነበር ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተባለው አራተኛው ክልል ያለ ሕዝበ ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲመሠረት የተደረገው፡፡
አዲሱ ክልል በመጪው ዓርብ መሥራች የምክር ቤት ስብሰባውን የሚያደርግ ሲሆን፣ በስብሰባውም በረቂቅ ሕገ መንሥት ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከረቂቅ ሕገ መንግሥት በተጨማሪ የክልሉን ማዕከላዊ ክላስተር ከተሞችና የተለያዩ መዋቅሮች ድልድልን በሚመለከት ውሳኔ እንደሚያስተላለፍ ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጂ ከመሥራች ምክር ቤቱ በፊት የተለያዩ ጥያቄዎቻችን ይመለሱ ያሉ አካላት ከወዲሁ ስብሰባውን እየተቃወሙት ይገኛሉ፡፡
በተለይ ከመዋቅር ድልድል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቅሬት ሲያቀርቡ የቆዩት የከምባታና ጠምባሮ ዞን የምክር ቤት አባላት፣ የዞኑ ጥያቄ ሳይመለስ ወደ ከልል ማደራጀት መገባቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ዱራሜ ባሉ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ከተሞች ተጠርቶ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ሰኞ ዕለት እንዳይካሄድ መደረጉን የገለጹት የዞኑ ምክር ቤት ተወካዮች፣ ባለፉት ሁለት ቀናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የልዩ ኃይል ፖሊስ በዞኑ መሰማራቱንም አመልክተዋል፡፡
ሥራና እንቅስቃሴ ማቆም እንዲሁም በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማው በዞኑ ረገብ ያለ መልክ ቢይዝም፣ ቅሬታውና ውጥረቱ ግን እንዳለ መሆኑን ተወካዮቹ ገልጸዋል፡፡ የዱራሜ ከተማ ምክር ቤትና የዞንም ምክር ቤት ተወካይዋ ወ/ሪት ሰናይት ለገሠ፣ ባለፈው እሑድ ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የዞን ምክር ቤት ስብሰባ ለግማሽ ቀን መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ የዞኑ ተወካዮች ካነሷቸው ቅሬታዎች መካከል የክልሉ መዋቅር ድልድልን የሠራው የጋራ ኮሚቴ በፍትሐዊነት የቢሮዎች ምደባን አላደረገም የሚል እንደሚገኝበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ጉራጌ ዞንን የወከሉትና የክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ርስቱ ይርዳው ለከምባታ ጠምባሮ፣ ለሀዲያ፣ ለስልጤ፣ ለጉራጌ፣ ለሀላባ ዞኖችና ለየም ልዩ ወረዳ የቢሮ ድልድል የሚያደርገውና የክልል አደረጃጀትን የሚወስነው ኮሚቴ አባል መደረጋቸው የኮሚቴውን ፍትሐዊነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፤›› የሚል አቤቱታ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
የከምባታ ጠምባሮ ዞን አንድ የግብርና ቢሮ ብቻ እንዲሰጠው ተደርጎ ክልሉ ይዋቀር መባሉ ሕዝቡን እንዳስቆጣው የተናገሩት ወ/ሪት ሰናይት፣ ይህ ጥያቄ ሳይመለስ ወደ ክልል ማቋቋምና ሕገ መንግሥት ወደ ማፅደቅ መሄዱ ትክክለኛ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ክልል ብዙ መዋቅሮችና ቢሮዎችን በማግኘት በሚታማው በጉራጌ ዞን ግን በክላስተር አደረጃጀቱ እንቀጥል የሚል ሳይሆን፣ የራሳችን ክልል እንመሥርት የሚል ተቃውሞ አሁንም ድረስ መኖሩን ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ አስታውቋል፡፡ ፓርቲው የጉራጌ ዞንን በክላስተር ክልል ለመጨፍለቅ የሚደረግ ጥረት ያለውን የክልል መደራጀት ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጀሚል ሳኒ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጉራጌ ራሱን በራሱ በክልልነት የማስተዳዳር ጥያቄውን አልተወም፡፡ ‹‹ጥያቄያችን ቡታጅራ ወይም ወልቂጤ ከተሞች ምን ያህል የክልል መዋቅሮችን አገኙ የሚል ሳይሆን፣ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበር የሚል ነው፤›› በማለት አቶ ጀሚል አክለዋል፡፡
የክላስተር ክልል አደረጃጀትን የደገፉ ዞኖች ወደ መዋቅር ድልድል ሲመጣ አነሰኝ ወይ በዛ የሚል ቅሬታ ሊያሰሙ እንደሚችሉ አቶ ጀሚል ያወሳሉ፡፡ ‹‹የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄ ግን ክላስተርን ሲጀመርም ውድቅ አድርጎ በራሴ ክልል ልደራጅ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የመዋቅር ክፍፍልን በተመለከተ ጥያቄም የለንም፣ ቅሬታም አናነሳም፤›› በማለት ነው የጉራጌ ዞን ጉዳይ የተለየ ገጽታ ያለው መሆኑን ያብራሩት፡፡
ቀደም ብሎ በተደራጀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የክልሉ መዋቅር በተለያዩ ከተሞች ተሠራጭቶ እንዲደራጅ መደረጉ ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ የተለያዩ ቢሮዎችን በተለያዩ ከተሞች መበተኑ ሕዝቡን ለእንግልት ከመዳረጉ በተጨማሪ፣ የመንግሥትን አስተዳደራዊ ወጪ እንዳሻቀበው ቅሬት ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ እንዲደራጁ በተወሰኑት የደቡብ ኢትዮጵያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ በተባሉ ሁለት ክልሎች መዋቅር ድልደላ በተለያዩ ከተሞች መደረጉ ሌላ ዙር ተቃውሞና ቅሬታ እያስነሳ ነው፡፡