Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሥጋት የደቀነው የኮሌራ ወረርሽኝ

ሥጋት የደቀነው የኮሌራ ወረርሽኝ

ቀን:

በኢትዮጵያ የኮሌራ ወረርሽኝ በስፋት በመዛመት የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ ወረርሽኙም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ጭምር እየጎዳ መሆኑም በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ ቢያደርግም ችግሩ ግን ሊፈታ አልቻለም፡፡

በአብዛኛው ገጠራማ አካባቢ ነዋሪዎች የወንዝና የዝናብ ውኃን ለመጠጥና ለምግብ አገልግሎት ስለሚጠቀሙ በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

የደቡብ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ድንገተኛ የጤና ነክ ክስተቶች ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታሪኩ መለሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደቡብ ክልል ከሚገኙ 152 ወረዳዎች በ43ቱ ውስጥ የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡

በክልሉ የኮሌራ ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው ሚያዝያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ሲሆን፣ ወረርሽኙም በስፋት በመሠራጨት 43 ወረዳዎች ውስጥ ሊከሰት መቻሉን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውን፣ 60 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሕይወታቸው ማለፉን አክለዋል፡፡

ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተበት ወቅት ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ባለመደረጉ የተነሳ፣ በፍጥነት በመዛመት የብዙ ሰዎችን ጤና ማወኩን አብራርተዋል፡፡

ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ቦታዎች ውስጥ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ባልተከሰቱ ወረዳዎች ግንዛቤ በመፍጠር ክልሉ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተለይ በ13 ወረዳዎች በተደረገው ርብርብ ወረርሽኙን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቆጣጠር እንደተቻለ የገለጹት ባለሙያው፣ በቀጣይም በሌሎች ወረዳዎች ያለውን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ እስካሁን ባለው ሁኔታ በ15 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 1.2 ሚሊዮን ዜጎች ክትባት እንዲያገኙ ተደርጓል የሚሉት አቶ ታሪኩ፣ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ሌሎች ተቋሞች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ግብዓቶችን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወረርሽኙ እያጠቃ ያለው በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እንደሆነ ጠቅሰው፣ እስካሁን ከሞቱት 60 ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ አረጋውያን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ውስን ቦታዎች ቀደም ተብሎ ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ፣ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ሊሆን እንደቻለና በዚህም የተነሳ ወዲያው ለመቆጣጠር መቻሉን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ወረርሽኙ ሊስፋፋ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የነበረው የድርቅ ሁኔታና የጎርፍ አደጋ መሆኑን ገለጸዋል፡፡

በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የነበረው የንፅህና አጠባበቅ ሥርዓት በመቀነሱ በክልሉ ወረርሽኙ በስፋት እንዲስፋፋ ማድረጉን የተናገሩት አቶ ታሪኩ፣ በቀጣይ ወረርሽኙን ለማቆም ክትባት በተሰጠባቸውም ሆነ ባልተሰጠባቸው ቦታዎች በመሄድ ዘላቂነት ያለው ሥራ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከዓምና ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ በርካታ ዜጎች ጤናቸው ታውኳል ያሉት፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ድንገተኛ ጤና ቁጥጥርና የጤና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ሹሚ ናቸው፡፡   

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በኮሌራ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ከ7,400 በላይ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ70 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከ12 በላይ የሚሆኑ የክልሉ ዞንና ከተሞች እንዲሁም ከ50 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ውስጥ ወረርሽኙ መከሰቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ክልሉ ጠንካራ የሆነ አሠራር በመዘርጋት በበርካታ ቦታዎች ሙሉ ለሙሉ ወረርሽኙን መቆጣጠር እንደተቻለ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ በአንዳንድ የሸገር ከተማ አካባቢዎች በከፊልም ቢሆን ወረርሽኙ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም ሆነ ከተከሰተ በኋላ ቢሮው ሰፊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በተከሰተባቸው ቦታዎች ጊዜያዊ የሕክምና ማዕከል እንዲኖር መደረጉን አክለዋል፡፡

በጊዜያዊ የሕክምና ማዕከላት ውስጥ በቂ ባለሙያዎችንና ግብዓቶችን በማሠራጨትና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ወረርሽኙን በከፊልም ቢሆን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ወረርሽኙ በዋናነት የተስፋፋበት ምክንያት ከግልና ከአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ መጓደል ጋር በተያያዘ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ገመቹ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ቢሮው ታች ድረስ በመውረድ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

የወረርሽኙ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ጤናማ ከሆነው ማኅበረሰብ ለመለየት ወጥ የሆነ ሥራ መሥራቱን ገልጸው፣ በአብዛኛው ቦታዎች ችግሩን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት በሁለት ዙር መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ከሁለት ወራት በፊት 16 በሚሆኑ ወረዳዎች የሚገኙ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች መከተባቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ምዕራብ ጉጂና ምሥራቅ ሸዋ በተመረጡ አራት ወረዳዎች ከ530 ሺሕ በላይ ሰዎች ክትባት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑን፣ ክትባቱንም በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል እያገኙ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ክትባቱ ተደራሽ እየሆነ ያለው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች በሙሉ መሆኑን፣ ወረርሽኙ በአብዛኛው ከ34 ዓመት ዕድሜ በላይ የሚገኙ ሰዎችን ማጥቃቱን ገልጸዋል፡፡

በሽታው ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች በተጨማሪ በትግራይና በአማራ ክልል መከሰቱም ይታወቃል፡፡                          

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኮሌራ ‹‹ቫይብሮ ኮሌራ›› በተባለ ተህዋስያን አማካይነት የሚከሰትና አንጀት የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ በተበከለ ምግብና ውኃ አማካይነት የሚመጣው ተህዋሱ፣ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ምልክቶቹ ናቸው፡፡ ኮሌራ በሰውነት ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ስለሚያሟጥጥና አቅም ስለሚያሳጣ ፈጥነው ካልታከሙ በሰዓታት ውስት ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...