- የአማራ ክልል ሕክምና ማኅበር የደምና የኦክስጅን እጥረት አለ ብሏል
ከሰሞኑ በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የደረሰውን ጉዳት መጠን በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም ያለው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ለደረሰው ጉዳት ተገቢውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ መቸገሩን አስታወቀ፡፡
የቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ አባል ጌታሁን ሁሴን (ኢንጂነር)፣ የተከሰተው ግጭት ድንገተኛ ከመሆኑም በላይ፣ መንገዶች በመዘጋታቸው፣ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ተንቀሳቅሰው ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም ብለዋል፡፡ ቅርንጫፎቹ ‹‹ምን ያህል ጉዳት ደረሰ?›› የሚለውን መረጃ ለመያዝ የሚያስችል አቅም እንዳልነበራቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹ሁሉንም ወገኖች የምንለምነው ተንቀሳቅሰን ድጋፍ ለማድረግና ሰብዓዊ ድጋፋችንን ለመስጠት እንድንችል ተባብሩን ነው፤›› ሲሉ ጌታሁን (ኢንጂነር) ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ለመርዳትና በክልሉ የከፋ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት፣ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎችንና ምላሾችን ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስመልክቶ ሐምሌ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋና ጽሕፈት ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ታዓ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፣ ሰሞኑን በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት ምክንያት በርካታ ዜጎች፣ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ እንዲሁም አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ለተለያዩ ሰብዓዊ ችግር ተጋልጠዋል፡፡
በግጭቱ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በቅርቡ ዕርዳታ ለማሰባሰብና የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ወደ ሥራ መገባቱን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ በግጭቱ ምክንያት ዜጎች ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ማኅበሩ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ሁሉም አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞች፣ አምቡላንሶችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የቀይ መስቀልን ዓርማ ይዘው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ማኅበሩ አበክሮ ጠይቋል፡፡
አሁን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ የቀይ መስቀል ማኅበር ለቁስለኞች የሚያስፈልጉ መድኃኒቶችና ቤተሰብ ማገናኘትን ጨምሮ፣ ባሉት ቅርንጫፎች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በመግለጫው ወቅት ተነግሯል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንስቶ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የውስጥ ጦርነትና የኑሮ ውድነት በመከሰቱ ሰብዓዊ አገልግሎት ከፍ ማለቱን የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አስታውሰዋል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም በአምቡላንሶቻችን ለረዥም ጊዜ አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ በአምቡላንሶቻችን፣ በበጎ ፈቃደኞቻችንና በሠራተኞቻችን ላይ አደጋ ደርሷል፤›› በማለት ያስረዱት የቦርድ አባሉ፣ ማኅበሩ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት እየከፈለ ሕይወት እንደሚያድንና የተቸገሩትን እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በግጭቱ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሁሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ዓርማዎችን፣ አምቡላንሶችንና የመጠለያ አካባቢዎችን እንዲጠብቁ ጥሪ በማድረግ፣ ለአገልግሎት ለሚንቀሳቀሱ አምቡላንሶቹ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጥሩለት ጠይቋል፡፡
‹‹በቀይ መስቀል መኪና ዓርማ መሣሪያም፣ ታጣቂም ማንቀሳቀስ አይቻልም፤›› ያሉት ጌታሁን (ኢንጂነር)፣ ማኅበሩ ለሁሉም እኩል እንደሆነና በእኩልነት እንደሚሠራ፣ ሕግና ሥርዓት በጠበቀ መንገድ ያለውን ውስን ሀብት አንቀሳቅሶ ድጋፍ ለመስጠት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተያያዘም የአማራ ክልል ሕክምና ማኅበር ነሐሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ እንዳደረገው፣ በአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመንገድ መዘጋት፣ የሕክምና ግብዓት ችግር፣ የኦክስጂንና የደም እጥረት እየተከሰተ ነው።
‹‹በዚህም ምክንያት በጦርነት ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ወገኖች፣ እናቶችና ሕፃናት ጭምር መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም፤›› ያለው ማኅበሩ፣ የሚመለከታቸው አካላትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ሕክምና በማንኛውም ሁኔታ ሊከለከል የማይገባው መሠረታዊ የሰው ልጆች መብት መሆኑ ታውቆ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያርጉ ጥሪ አቅርቧል።
‹‹ለሁሉም የሕክምናና የጤና ባለሙያዎች በሙሉ እስካሁን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ለምትሰጡት አገልግሎት እያመሠገንን፣ አሁንም በየአካባቢያችሁ ከተቋቋሙት የድንገተኛ የሕክምና ቡድኖች ጋር በመሆን ሙያዊ ግዴታችሁን መወጣታችሁን እንድትቀጥሉ፤›› ሲል የአማራ ክልል ማኅበር አሳስቧል፡፡