Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፋይናንስ ተቋማት ደንበኞች ላይ የሚፈጸም ዲጂታል ዝርፊያና ማጭርበር ተባብሷል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት እየተስፋፋ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ ላይ ያነጣጠሩ የማጭበርበር ተግባራት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ መምጣታቸው የፋይናንስ ተቋማትን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከቷል።

ሪፖርተር ከተለያዩ ባንኮች ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ማጭበርበሮች በዋናነት የሚመነጩት የባንክ ደንበኞች የግል መረጃዎቻቸውን በተለያዩ ሁኔታዎች ለሌሎች አሳልፈው ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣ የግል መረጃን በአግባቡ ካለመያዝ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች እየተጭበረበሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚደርሱ መረጃዎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ከዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ያመላቱት አቶ አቤ፣ ደንበኞች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ደጋግሞ እያሳሰበ ቢሆንም ድርጊቱ ጎልቶ እየታየ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ ከደንበኞች መረጃ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች እየጎሉ መምጣታቸው አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ ስለመድረሱም ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የእጅ ስልኮቻቸውንና የዲጂታል ባንክ አገልግሎት መጠቀሚያ የይለፍ ቃሎችን በሚስጥር መያዝ ሲገባቸው፣ የይለፍ ቃሎችን (ኮዶችን) በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ መዝግበው እየያዙ መሆኑ፣ ቴክኖሎጂዎችን በሚጠቀሙ አጭበርባሪዎች ኮዶቻቸውን በቀላሉ እየመነተፏቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ ድርጊትም እየተባበሰ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

ለችግሩ መባባስ ተጨማሪ ምክንያት ናቸው ብለው የጠቀሷቸው ሌሎች ጉዳዮች ውስጥ የሞባይል ስልኮች አሰጣጥና ቁጥጥር ክፍተት ያለው መሆኑ ነው፡፡ የብሔራዊ መታወቂያ ባለመኖሩም አጭበርባሪዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሒደት የከፋ ጉዳት ባይደርስም፣ የማጭበርበር ድርጊቱ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ነው ያሉት አቶ አቤ፣ ደንበኞች የግል መረጃዎቻቸውን አያያዝ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

ሁኔታው በወጉ ካልተያዘ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል መሆኑን ያስረዱት አቶ አቤ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን ይህንን ማጭበርበር ድርጊት ፈጻሚዎችን በሕግ ለመጠየቅ እየሠራ መሆኑንና ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችንም ለሕግ አካል ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡ 

የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው፣ የካርድም ሆነ የሞባይል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞች በየባንኮቻቸው የሚሰጧቸውን የጥንቃቄ መመርያዎች በአግባቡ ያለመተግበር ለማጭበርበር ሊያጋልጣቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህ አንፃር ብዙ ጊዜ የጥንቃቄ ጉድለት የሚታይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አስፋው፣ ‹‹የይለፍ ቃሎችን (ፓስ ዎርድ) በጭንቅላት መያዝ እንጂ፣ ጽፎ ማስቀመጥ ለአደጋ ያጋልጣል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የይለፍ ቃልን በስልክ ላይ መዝግቦ ማስቀመጥና መሰል የጥንቃቄ ጉድለቶች የማጭበርበር ተግባራትን ሊያበራከቱ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ደንበኞች ኤቲኤም ሲጠቀሙና በፓስ ማሽን ግብይት ሲፈጽሙ የይለፍ ቃሎቻቸውን ሌሎች በማይመለከቱበት መንገድ ማስገባት እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ብዙዎች ይህንን መሠረታዊ የጥንቃቄ ተግባር ባለመፈጸም ለመጭበርበር የሚጋለጡበት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ሌላው ቀርቶ የይለፍ ቃልን በመኖሪያ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ አስተማማኝ እንዳልሆነ የሚመክሩት ያነጋገርናቸው የባንኮች የሥራ ኃላፊዎች፣ የይለፍ ቃሎችን በጥንቃቄ ባለመያዝ በገዛ ቤተሰቦቻቸው ከቴሌ ብርና ከባንክ ሒሳቦቻቸው ገንዘብ የተመዘበሩና ድርጊቱን የፈጸሙትም ተደርሶባቸው ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች መኖራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

እንደ አቶ አስፋው ገለጻ፣ ግለሰቦችን ለመጭበርበር ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ሌላው ነጥብ ወቅትን ጠብቆ የይለፍ ቃል ያለመቀየር ነው፡፡ ቢያንስ በሁለትና በሦስት ወራት የይለፍ ቃልን መቀየር ከተጋላጭነት እንደሚያድንና ደንበኞች የይለፍ ቃል እንዲያስተካክሉ የሚጠይቅ መረጃ ሲደርሳቸው ጊዜ ሳያባክኑ ወዲያውኑ ማስተካከል እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ የሚጠቀሙበት ባንክ ሲስተም ይህንን መረጃ እስኪያደርሳቸው መጠበቅ እንደማይገባቸውና የይለፍ ቃሎቻቸውን በየጊዜው የመቀር ልምድ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን መክረዋል።

እያደገ ከመጣው ዲጂታል ኢኮኖሚ ጎን ለጎን ማጭበርበሮች መከሰታቸው አይቀርም የሚሉት አቶ አስፋው፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሰዎች ለማጭበርበር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ደንበኞች የግል መረጃዎቻቸውን በአግባቡና ጥንቃቄ መያዝና መጠቀም የመጀመርያው መፍትሔ መሆኑን ያምናሉ፡፡

‹‹የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ነው፡፡ የተጠቃሚዎች ቁጥር ሲጨምር ደግሞ የሌቦችም ቁጥር እንደሚጨምር እንገምታለን፤›› ያሉት አቶ አቤ፣ ይህንን ክፍተት ለመድፈን ግን የባለድርሻ አካላትን የቅንጅት ሥራ የግድ የሚል መሆኑን አስምረውበታል።

በሳይበር ጥቃት ሲስተማቸውን በመስበር ከአንዱ አካውንት ወደ ሌላ አካውንት በማዘዋወር የመዝረፍ ነገር በሌላው ዓለም የከፋ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ከሙከራ ባሻገር የተፈጸመ ነገር አለመታየቱን አቶ አቤ ተናግረዋል።

‹‹እስካሁን ድረስ የእኛን ባንክ የዲጂታል ሲስተም ጥሶ ስርቆት የፈጸመ የለም፡፡ ይህ ቢሆን ግን አደጋው የከፋ ይሆን ነበር። አሁን በብዛት እያጋጠመ ያለው ማጭበርበር የግለሰብ ደንበኞችን የጥንቃቄ ጉድለት በመጠቀም ገንዘብ የማጭበርበር ተግባር ነው፤›› ብለዋል።

አጭበርባሪዎች ከሚጠቀሙባቸው ሥልቶች መካከልም ‹‹ሽልማት ልንሰጥዎ ነው፣ ብድር ልናቀርብ ነው›› የሚሉ መሰል አጓጊ መልዕክቶችን ወደ ደንበኞች በመላክ የደንበኞችን መረጃ በመውሰድ የባንክ ሒሳባቸውን እንደሚመነትፉ ተናግረዋል። አንዳንዴም አጭበርባሪዎች ዲጂታል ባንክ ተጠቃሚ ሰዎች ዘንድ በመደወል አታላይ መረጃዎችን በመስጠት ደንበኞች ነገሩን ሳይረዱ የተባሉትን በመፈጸም ከራሳቸው ሒሳብ ወደ አጭበርባሪው ሰው ገንዘብ የሚያስተላልፉበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል። በተለይ ሽልማት ልንሰጥ ነው በማለት የሚሰጡ መረጃዎች ከብዙዎች ገንዘብ እንዲወሰድባቸው አድርጓል፡፡ 

አጭበርባሪዎች ከደንበኞች ሒሳብ ላይ ስርቆት ለመፈጸም ይህ ሁሉ ችግር ግን ደንበኞች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መረጃዎቻቸውን መስጠታቸው ስለመሆኑ ከባንኮቹ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የተለያዩ ሥልቶችን የሚጠቀሙ ሲሆን በቅርቡ እንኳን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሞባይል ባንኪንግ አማካይነት ብድር እየሰጠ ነው በሚል በሐሰት መረጃ ሐሰተኛ ኮድ በማዘጋጀት ከደንበኞቹ ሒሳብ ላይ ስርቆት ለመፈጸም የተደረጉ የማጭበርበር ሙከራዎችም እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ 

ማጭበርበሩን ከመቀነስ አኳያ ደንበኞች ከሚያደርጉ ጥንቃቄዎች መካከል በስልኮቻቸው የተለያዩ መረጃዎች ሲደርሳቸው ወዲያው ማሳወቅ ተገቢ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከባንክ አካውንት ገንዘብ ተቀንሶ በሞባይል ስልካቸው መልዕክት ሲደርሳቸው ወዲያውኑ ከባንኮቻቸው ጋር የመገናኘት ልምድ ደንበኞች ሊያደዳብሩ እንደሚገባ አቶ አቤም ሆኑ አቶ አስፋው ይመክራሉ፡፡ አጠራጣሪ ነገር ካለም ባንኮቻቸውን ማነጋገር ከመጭበርበር ሊያድናቸው እንደሚችል፣ እንዲሁም ከተጭበረበሩም በቶሎ መፍትሔ ለመፈለግ የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሲስተም ያለ መኖር ወይም በሌላ ምክንያት አንዳንድ ግብይቶች ወይም የገንዘብ ማስተላለፍ ሒደት ከሚገባው በላይ ሲዘገይ ወይም አገልግሎቱ ተፈጽሞ ወደ ሞባይል የሚላከው የማረጋገጫ መልዕክት ከዘገየ ደንበኞች በፍጥነት ስለሁኔታው ለባንኮቻቸው ማሳወቅና መጠየቅ እንደሚገባቸውም መክረዋል።

ደንበኞች በምንም ሁኔታ ሽልማት ወይም ሎተሪ ደርሶዎታል የሚሉና ሌሎች ማማለያ መልዕክቶችን ለሚልኩላቸው የማይታወቁ ሰዎች የግል ታሪኮችና ሌሎች የባንክ መረጃዎችን ከመስጠት መቆጠብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ሁኔታው ሳይባባስ ተቀናጅቶ ከሕግ አካላት ጋር በመሆን መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡ 

ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ሲገባ አደጋዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉት አቶ አስፋው፣ የማጭበርበር ተግባራት ሲፈጸሙና ሁኔታው ለፖሊስ ሪፖርት ሲደረግ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ አስተማሪ የሆነ ቅጣት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ባንኮችም በየጊዜው ሲስተማቸውን መፈተሽ የሚያስፈልግ ስለመሆኑም የገለጹት አቶ አስፋው፣ ችግሩ ከውስጥ ሠራተኞቻቸው አካባቢም ሊሆን ስለሚችል ሠራተኞቻቸውን መከታተል የመፍትሔው አካል ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡ 

ከዚህ ውጪ ግን ሲስተሙ ደንበኞችን የሚጠብቅ የተለያየ አሠራር እንዳለው ያመለከቱት አቶ አስፋው፣ ለምሳሌ ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ተጨማሪ የይለፍ ቃል ጥያቄዎችን ደንበኞቹ ሳይሰለቹ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተገልጋዮች ‹‹ተጨማሪ የይለፍ ቃል ለምን ይጠየቃል፣ አሠራሩን ለምን ታረዝሙብናላችሁ›› ቢሉም፣ እንደዚያ የሚደረገው የደንበኞቻቸውን ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች