Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለአገራዊ ፈተና እያጋለጡን ያሉ ማኅበራዊ ህፀፆች

ለአገራዊ ፈተና እያጋለጡን ያሉ ማኅበራዊ ህፀፆች

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ሰዎች አብረው ሲኖሩ ሊከተሏቸው የሚገቡ የአብሮ መኖር ሥርዓቶች መኖራቸው ከጥንተ ጀምሮ የታወቀ ነው፡፡ የሚኖሩባቸው አገሮች ያስቀመጧቸውን የረዥም ጊዜ ዕቅድ ለማሳካትም ሆነ፣ የየራሳቸውን ዕለታዊ ሕይወት ለመምራት በሥርዓት (ዲሲፕሊን) መንቀሳቀስ የማይታለፍ ግዴታቸው ነበር፡፡ መሆንም አለበት፡፡

ሥርዓትን ማስከበር ደግሞ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚረጋገጥ ሳይሆን፣ ይልቁንም ዜጎች በራሳቸው ተሳትፎና ማኅበረ ባህላዊ ተቋማት ሚና የሚሳካ ነው፡፡ ሥርዓትን (ሕግና ሕገ መንግሥት) ማክበርም ሆነ ማስከበር የዜጎች የራሳቸው ኃላፊነትም ጭምር ነው፡፡ ዜጎችም ሆኑ መንግሥት ይህን አጥብቀው መገንዘብ ብቻ ሳይሆን የመተግበርም ግዴታ አለባቸው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን በእኛ አገር የሥነ ምግባር ጥሰቱ መባባስና የማኅበራዊ ህፀፆች መድራት የሕግ ጥሰትና ሥርዓት አልበኝነትንም እያበረታው ሆኖ ይታያል፡፡ እንዴት አዲስ ዓይነት የመገፋፋት፣ የመጨካከን፣ የነውረኝነትና የስግብግብነት ልማድ ሲበረታ ሕዝቡ ራሱ እንደ ተቋም መታገል ተሳነው? የሚለው ጥያቄ ጥልቅ ጥናትና አርምሞን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡

በእርግጥ በዜጎች ላይ የሚታዩ የሥነ ሥርዓት ችግሮች (ህፀፆች) በሁሉም አገሮች በተለያዩ ደረጃዎች ቢሆንም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ቀደም ሲል በአፍሪካ በቅድሚያ ከሚጠቀሱት አገሮች መካከል ናይጄሪያ ግንባር ቀደም ናት፡፡ በአንድ ወቅት በድረ ገጾች የተለቀቀ ‹Can Nigerians stop being unruly?› በሚል ርዕስ የቀረበውን ትንታኔ አስታውሳለሁ፡፡

የያኔው (ከ40 ዓመታት በፊት አንስቶ) የአገሪቱ መገለጫ ሆነው የነበሩት ሥርዓት አልበኝነቶች የመንጋ ፍርድ፣ የቡድን ጥቃት፣ ጭካኔ የተሞላበት የዘርና የእምነት ልዩነት መጠቃቃት፣ ሙስናና ማኅበረሰባዊ ንቅዘት፣ ግዴለሽነትና የብሔራዊ ስሜት መዳከም… ዓይነተኛ ማሳያዎች እንደሆኑ ያስረዳል ጽሑፉ፡፡ እነዚህ መገለጫዎች ደግሞ ተደማምረው ቆይተው በመንፈንቅለ መንግሥት መልክ ወደ ሥልጣን የመጡት የጀኔራል ቦሃሪ አስተዳደር ዋነኛ ራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር፡፡

እሳቸውም በሌላ መፈንቅለ መንግሥት በ1986 ዓ.ም. ከሥልጣን እስከተወገዱ ድረስ ናይጄሪያን በወታደራዊ ኃይል የመሩት ፕሬዚዳንቱ የመጀመርያ ዕርምጃቸው የነበረው፣ በአገራቸው ዜጎች ላይ የሚታየውን ሥርዓት የለሽነት ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ነበር፡፡ ‹‹በዲሲፒሊን አልባነት ላይ ጦርነት›› (War Against Indiscipline-WAI) የተሰኘ መመርያ ማውጣትና መተግበርም ጀምረው ነበር፡፡ ይህውም ሥነ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ ዓላማ ያለው ነበር፣ ቅጣቱም ወታደራዊ ነበር፡፡

እንኳንስ ለለየላቸው ደረቅ ወንጀሎች ይቅርና በዚያ መመርያ መሠረት፣ ለምሳሌ በትምህርት ቤትም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አርፍደው (ሰዓት አሳልፈው) የሚመጡ ሰዎች አካላዊ ቅጣት ያገኛቸው ነበር፡፡ ተንበርክከው፣ ቁጢጥና እንጣጥ እያሉ እንደ እንቁራሪት እየዘለሉ አካላቸው እስኪደክም ድረስ የሚንፏቀቁበት የቅጣት ዓይነት ነበር፡፡ በወታደርኛ (Frog Jumps) ይባላል፡፡ ሲዘርፍና ሕገወጥ አድማ እየመታ የደሃ አገር ሀብት የሚያወድመውንማ በጥይት እስከ መቁላት ይደርሱ ነበር፡፡

ቆሻሻን ባልተፈቀደ ቦታ የሚጥሉ እንኳን፣ በየሥፍራው (ፍሳሽ ወይም ደረቅ) የሚፀዳዱ ዜጎች የሚያገኛቸው ቅጣት በወታደራዊ ፖሊሶች አማካይነት በአደባባይ ላይ ሕዝብ እያየ የሚፈጸም ነበር፡፡ የሥራ መመርያ የማያከብሩ ሁሉ የአካላዊ ቅጣት ሰለባ ከመሆን አያመልጡም፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅጣቱን በመፍራት ብቻ ሁሉም ዜጋ ሥነ ሥርዓት እንዲኖረው ለማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ የከተሞችም ፅዳት ከሚታመነው በላይ ተሟልቶ ነበር፡፡

ጄኔራል መሐመድ ቡሃሪ በድጋሚ ከዛሬ ስምንት ዓመታት በፊት (May/2015) በምርጫ ተወዳድረው ጉድላክ ጆናታንን ተክተው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ሕዝቡ ‹‹በድምፃችን ጥሩ መሪ አገኘን፣ ሥርዓት የለሽነት ከእንግዲህ አበቃለት…›› በሚል ከፍተኛ እምነት ጥሎባቸው ነበር፡፡ ሕዝቡ ቡሃሪ የያዙት በትረ ሥልጣን የድግምት በትር (Magic Wand) እስኪመስለው ድረስ እሳቸው የነኩት ችግር ሁሉ ከመቅጽበት እንደሚፈታ ሙሉ እምነት አሳድሮ የነበረውም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አብዛኛው ነገር የታሰበውን ያህል ባይሆንም፡፡

እውነት ለመናገር አምባገነናዊና ወታደራዊ መንግሥት በዚህ ዘመን አይደለም በፊትም ቢሆን ተመራጭ ባይሆንም፣ ሥርዓተ አልበኝነትና ሕገወጥነት ከተንሰራፋበት ሥርዓተ መንግሥት የተሻለ መሆኑ አይቀርም፡፡ አገራችን አሁን የምትገኝበት ደረጃም ቢሆን ከዚሁ ተነጥሎ እንዳማይታይ ነው ብዙዎች እየተናገሩ ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ባለፉት አምስት ዓመታት በለውጥ ስም ያልተፈጸመ ወንጀልና የሕዝብ ጥቃት ምን አለ ብሎ ለጠየቀ ሰው አባባሉ ስህተት አይመስለኝም፡፡

ዜጎች በየአካባቢው በማንነታቸው እየተገደሉ በጅምላ ተቀብረዋል፡፡ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ወድሟል፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ በየአካባቢው የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች ጥቃት በርካታ የፀጥታ አካላት መስዋዕት ከመክፈላቸው ባሻገር ንፁኃንም እረፍት አጥተው ተቸግረዋል፡፡ ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ተሳደዋል፣ ታግተዋል፣ ዋስትናም እስከማጣት ደርሰዋል፡፡ የዜጎች ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብትም በተጨባጭ ተገድቧል፡፡

በየአካባቢው አለመረጋጋትና ጠንካራ የልማት እቅስቀሴ መታጣቱ የፈጠረውና ያባባሰው ሥራ አጥነት እያየለ ነው፡፡ በዚህም እንደ ሌብነትና ዘረፋ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ማኅበራዊ ህፀፆችም ስለመቀነሳቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ የመሠረተ ልማትና የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ዘረፋ አልቀነሰም፡፡ ከላይ እስከ ታች ባለው መንግሥታዊ መዋቅር ካለፈው ሥርዓት የተሻለ አገልግሎትና መልካም አስተዳዳር ተዘርግቷል ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ መስኮች ዓይን ያወጣ ሙስናና ኢፍትሐዊነት እየተስተዋለ መሆኑን ነው ሕዝቡ በምሬት የሚናገረው፡፡

አሁን በምንገኝበት ሁኔታ በብሔርና በሃይማኖት ስበብ ከፍተኛ የፖለቲካ ሽኩቻ እየተመላለሰ አገሪቱን በማናወጥ ላይ ነው፡፡ መንግሥትም ጠበቅ ያለ ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አመኔታውን ወደ ሚሸረሽር የአደራዳሪነት ተግባር መግባቱና አንዳንዴም በጠራራ ፀሐይ ሕግና ሥርዓት ሲጣስና ጋጠ ወጦች ሲፋንኑ ተው ባይ በመጥፈቱ ሥጋት የገባቸው ወገኖች ትንሽ አይደሉም፡፡ መጪው ጊዜም በሥጋት ደመና ውስጥ ወድቀዋል፡፡

እዚህ ላይ የአገራችን ብዙኃኑ ሕዝብ ቸልተኝነትና ዝግመትም እንደ ድክመት መነሳት ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሠረቱ ማንኛውም ሥልጡን ማኅበረሰብ ግዴታውን በአግባቡ እንደሚወጣው ሁሉ ጥቅሙንም አሳልፎ አይሰጥም፡፡  ሥርዓትን ማክበርና ማስከበርም ዋነኛው ተግባሩ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ለሁሉም ነገር የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት መጠበቅም አይገባም፡፡ የራሱን መብት ማስከበር የሕዝቡ የራሱ ግዴታ ነበር መሆን ያለበት፡፡ ይህ በእኛ ዘንድ እየታየ አለመሆኑ ያስቆጫል፡፡

እንደ ሕዝብ አሁን በሚታየው መንገድ የምንቀጥል ከሆነ ዋነኞቹ ተጎጂዎች እኛው ራሳችን ነን፡፡ እንኳንስ በማኅበረሰቡ ውስጥ በመንግሥት አካላትም ቢሆን የሚፈጠርን ሕገወጥነት አምረርን የማንታገለው እስከመቼ ድረስ ነው? ብሎ መነሳት ግድ ይለናል፡፡ ዜጋው በገዛ ቀየውና አገሩ ከሥነ ሥርዓት ውጭ በሆነ መንገድ መብቶቹ ሲጣሱ እያየ ዝም ማለት የለበትም፡፡ የራሱን ሚና ሳይጫወት፣ የራሱን ግዴታ ሳይወጣ በየጎዳውናውና በየጉራንጉሩ ለተፈጠሩ የሰዎች አጉራ ዘለልነት ሁሉ ጣቱን መንግሥት ላይ ቢቀስርም ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡

ለመሆኑ አሁን ባለችው አገራችን የመንግሥትን ድክመት እናቆየውና እነዚህ በማኅበረሰቡ  በየቦታው ሲፈጸሙ የሚታዩ አዋኪና ከሥነ ሥርዓት ውጭ የሆኑ የዜጎች ባህሪያት የትኞቹ ናቸው? ጥቂቱን እናንሳቸው፡፡

ለአገርንና ለሕዝብ ጥቅም ያልወገኑ ፖለቲከኞች

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የአገራችን ፖለቲካ ንግድ፣ ያውም አየር ባየር ንግድ እየመሰለ ነው፡፡ የሕገወጥ ንግዱ መጫወቻ ካርድ ደግሞ ብሔር/ሕዝብ እየሆነ ነው፡፡ የተግባሩ ሥረ መሠረት የአገርና ሕዝብ ጥቅምን ማስከበር ቢሆንም፣ ብዙዎቹ የራሳቸውን አለፍ ካለም የቡድናቸውን ፍላጎት ለማርካት የሚራኮቱበት የስግብግቦች ሜዳም ሆኗል፡፡ አሳዛኙ ነገር ሚዲያው፣ ማኅበራዊ የትስስር ገጹ፣ ዓውደ ምሕረቱ፣ መስጅዱ፣ ትምህርት ቤቱና አደባባዩ… ሁሉ የእነዚህ በሕግና ሥርዓት የማይመሩ አካላት መንቦራጨቂያ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡

የአገራችን አንዳንድ ፖለቲከኞች አካሄድ ጭልጥ ባለ ሰርጥ ላይ እንደ ማንቀላፋት ያለ ነው፡፡ ገና በለጋ የለውጥ መንፈስና እንጭጭ የዴሞክራሲ ጉዞ ውስጥ ሕግን እየጣሱና ከዚያና እዚህ እያጣቀሱ መሄድ፣ ያውም ተከታይ የሆናቸውን ወጣት ለእሳት እየማገዱ ፍላጎትን ለማሳካት መሞከር ከማንወጣበት ቀውስ ውስጥ ነው የሚከተን፡፡ አገር ለመምራት ሥልጣን ላይ ተቆናጦስ አፍ ከልብ አለመሆን፣ በጥገኛና የዘር ፖለቲካ መታወርና መሳሳብ፣ የግል ጥቅምን ማሳደድና በጥላቻ መናወዝን ምን አመጣው? ዕብደት ነው፡፡   

ለመሆኑ በእንዲህ ያለ አፍራሽና የትርምስ መጥሪያ መንገድ እስከ የት ድረስ ለመሄድ ይቻላል? የፖለቲካ ትግል ማለት እኮ ሥልጣን ይዞ ሕዝብ ለማገልገል ነበር ብሂሉ፡፡ እንጂ ሕዝብን እያባሉ ለመኖር እንዴት ሊታሰብ ይችላል? አገር አፍርሶና አመሳቅሎስ ምን ድል አለ ፀፀትና የዘለዓለም ተወቃሽነት እንጂ፡፡ እንደ ሕዝብ ይህን አገራዊ ደዌ ታግሎ መሻገር ካልተቻለ የችግራችን ሰንኮፍ ስለመነቀሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

እናም ሌላ ሥራ ሠርተውና ተወዳድረው መኖር የማይችሉ ወስላታ ግለሰቦች ሁሉ በፖለቲካ ስም እንዲጫወቱብን መፍቀድ የለብንም፡፡ በተናጠልም ሆነ በጊዜያዊ ቡድን ውስጥ ሆነው ሕጉን በእጃቸው እያደረጉ ራሳቸውን ከሕግ በላይ አስመስለው በሕዝብ ይሉኝታ እየተጠቀሙ፣ ‹‹ምን ታመጣለህ?›› እያሉ እንዲፈነጩብን መፍቀድም የሞት ያህል ሊቆጠር ይገባዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ፀሮችና ቀጠሮ አጨናናቂዎች

የለውጡ መምጣት አንዱ ተስፋ ሌብነትን የሚያስቀርና መልካም አስተዳዳርን የሚያሰፍን ይሆናል የሚል ነበር፣ ይህ አልተሳካም፡፡ እውነት ለመናገር በመሬት ዘርፍ፣ በመንገድ ትራንስፖርት፣ በገቢዎችና መሰል የአገልግሎት መስኮች ከፍተኛ ሕገወጥነትና መጉላላት ነው እየታየ ያለው፡፡ በአገልግሎት ረገድ እንዲያውም አዲስ አባባ ይሻላል እንጂ፣ እዚሁ ጎረቤት ካሉት ሰበታና ቡራዩ ጀምሮ በየክልሉ ያለው የሕዝብ እንግልትና በግላጭ የሚታይ ሙስና የሥርዓተ አልበኝነት መገለጫ መስሏል፡፡

ዛሬ ዛሬ የትም ብትሄዱ ከሕዝብ ብዛትና ተገልጋይ ጋር ባልተጣጣመው የአገልግሎት አሰጣጥና ዳተኝነት ምክንያት፣ አገልግሎት ፈላጊው አንድ አዳራሽ ውስጥ ተጠቅጥቆ ሲበሳጭ ማየት የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዱ ጋር ፈጻሚውም ባለሙያውም አይገኝም፡፡ አስተናጋጅ ተብዬዎች ብቅ እያሉ ‹‹እየመጡ ናቸው ወይም ስብሰባ ናቸው…›› እያሉ ያዘናጋሉ፡፡ በዚያወም ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ ቢመጡም ለሕዝብ አዝነው ተፍተፍ አይሉም፡፡ የሚፈሩት አካል ያለ የማይመስሉትም የበዙ ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉ ሰዎችን ሲመጡ ‹‹ቀኑን ሙሉ እርስዎን ጥበቃ የምንገላታው ለምንድነው? አሁንስ አላበዙትም እንዴ? ግብር ከፍለን በተቀጠሩበት ሥራ ወይም በድምፃችን በተሾሙበት ወንበር እንዴት እንገላታ? ይህ ሁሉ ቀጠሮ ያለ በቂ ምክንያት ለምንድን ተሰጥቶ ነው ቀኑን ሙሉ የምንገለታው? የደንበኝነታችንና የዜግነታችን  መብትስ እንዴት አይከበርም? ደንበኛ ንጉሥ መሆኑ እንኳ ቢቀር እንደ ሰው፣ እንደ ተገልጋይ መታየት ለምን አልቻለም…›› ማለት የአሠሪያቸው መንግሥት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛ የተገልጋዮችም ፈንታ መሆን አለበት፡፡

አንዳንድ ጊዜ ለተገልጋዮች መጉላላት የሠራተኞች ከሥራ መቅረት፣ መፎረፍና በውጤታማነት አለመሥራትም ተፅዕኖ ሲያደርግ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ሥራ ላይ ያልተገኘውን ሠራተኛ እንደተገኘ አድርገው ሰዓት መቆጣጠሪያ ላይ የሚሞሉለት ነውረኛ ተቆጣጣሪዎችና አሠሪዎችም አይጠፉም፡፡ ርካሽ ተወዳጅነትን ያገኙ እየመሰላቸው የሠራተኛውን ባህሪና የሥራ መንፈስ የሚያበላሹና መሥሪያ ቤቱንም ላልተሠራ ሥራ እያስከፈሉ ለወጪ የሚዳርጉ ከንቱዎች፣ ሕዝብ እየበደሉ መሆናቸውን አይዘነጉትም፡፡ እነዚህን ፊት ለፊት መናገር መልመድ አለብን፣ መታገልም ያስፈልጋል፡፡

እውነት ለመናገር እንደ ሕዝብ ሥራውን በሰዓቱ ተገኝቶ፣ በፍትሐዊነት፣ በግልጽነትና በታማኝነት የማይሠራና በሙስናና በውጣ ውረድ የሚያማርረንን መንግሥታዊ መዋቅር/ሠራተኛ ካልታገልንስ ምን ልንታገል እንችላለን?

ሠልፍ ሰባሪዎች

በሁሉም አገሮች በተለይ በአፍሪካ ለአገልግሎት፣ ለትራንስፖርት፣ ለሸመታ ወይም ለምዝገባና ሌሎች ጉዳዮች ሁሉም ሰው እንደ አመጣጡ ሠልፍ ይዞ ተራውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ በቴክኖሎጂ ታግዞ ቁጥር መያዝና የአሻራ ምዝገባ ከመምጣቱ በፊትም ሠልፍ መያዝ ዘመናዊ፣ ተገቢና ፍትሐዊ አሠራር ሆኖ ነው የቆየው፡፡

በእኛም አገር በተለይ በአዲስ አባባ እንደተለመደው (ክልሎች በዚህ ደካማ ናቸው) ከአረጋውያን፣ ከነፍሰ ጡሮች፣ ከአካል ጉዳተኞች፣ ከሕፃናትና ከተማሪዎች በስተቀር ሁሉም ሰው ሠልፍ መግባት ይጠበቅበታል፡፡ ይሁን እንጂ ሥነ ሥርዓቱ  ይህ መሆኑን እያወቁ ሠልፍ መቆም ባለመፈለግ በቀጥታ እንደመጡ ከፊት ሆነው ቀድሞ አገልግሎት ለማግኘት የሚገፈትሩ ሥርዓት የለሾች አሉ፡፡ እንዲህ ያለ ጋጠ ወጥነትና አጭበርባሪነት ቀላል ቢመስልም ሊወገዝ የሚገባው ነውር ነው፡፡ አውጋዦቹ መሆን ያለብን ደግሞ ሠልፈኞቹ ወይም ራሳችን ዜጎች ነን፡፡  

በእኛ አገር ሁኔታው የባሰ ነው፡፡ በሕዝብ ይሉኝታ የሚጠቀሙ፣ በቡድን ተደራጅተው ባላየ ባልሰማ ሰተት ብለው የሚገቡ አጉል ጠባይ ያላቸው ወጣቶች አሉ (ለነገሩ ድንኳን ሰባሪ የሚባሉ በሰው ድግስ ገብተው ዘርፈው የሚበሉ፣ አለፍ ሲልም የግል ጥቅም ለማግኘት ሆ ብለው ልማት የሚያወድሙ፣ በደቦ ተነሳስተው በዘር ወይም በሃይማኖት መዘዝ ነብስ የሚያጠፉ፣ ንብረት የሚዘርፉ ወሮ በሎች ያሉባት አገር ውስጥ አይደል ያለነው)፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹን ዘው ባይ ፈጣጦች ወይም በማኅበረሰቡ ነውር የሆነ ድርጊት ፈጻሚዎችን ሃይ ለማለት ወይም ሥርዓት ይዘው እንዲኖሩ ለማድረግ የግድ መንግሥት መምጣት አለበት ወይ? ‹‹ሠልፍ ያዙ፣ ተራ ጠብቁ፣ ሥርዓት አድርጉ፣ ነውር አትፈጽሙ…›› ማለት የአገሪቱ ዜጋ ግዴታ አይደለም ወይ? መብቱን ማስከበር የእሱ (የተሠላፊው) ኃላፊነትስ አይደለም ወይ?… ይህን ነው መፈተሽ የሚያስፈልገው?

ሰርቆ አደርነትና ሌብነት የትም አገር ያለ ቢሆንም፣ በእኛ አገር በተለይ አዲስ አባባን በመሰሉ ከተሞች እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ዛሬ ዛሬ በቡድንና በጦር መሣሪያ ቤት/ድርጅት ወርሮ ከመዝረፍ አንስቶ የፀጥታ ኃይሎችን ተመሳስሎና የአሻጥሩ አካል አድርጎ የሚፈጸም ሰፋፊ ወንጀል እየታየ ነው፡፡ ተሸከርካሪ እንዳለ መስረቅ፣ ወይም ሕፃን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ ወይም በመንግሥት ተሸከርካሪ ጭምር አፍኖ መዝረፍ መታየቱ፣ የችግሩን መባባስ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ እንዲህ ያሉት ወንጀሎች ላይ ፖሊስ ትልቅ ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡

ኪስ አውላቂዎችም እንደ ዝንብ የበዙበት ጊዜ ነው፡፡ በትራንስፖርት (በአውቶቡስና ባቡር ውስጥ ይብሳል) እና በአገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች በሚፈጠሩ መጨናነቆች መሀል እጃቸውን እየሰደዱ የሰው ገንዘብና ንብረት (ሞባይል) የሚሰርቁ ተራ ሌቦችን ለመታገል ሕዝቡ ማነስ የለበትም፡፡ ከፊታችን የቆመውን ሰው ሲሰርቁ ከኋላ ወይም ከጎን ያለን ሰዎች እናያቸዋለን፡፡ ዝም እንላቸዋለን፣ ወይም ሌቦቹ ከሄዱ በኋላ በገደምዳሜ ለተሰራቂው በምልክትም ቢሆን እናሳውቀዋለን፡፡ ይህ ነው መስተካከል ያለበት፡፡

ሌቦቹን እጅ ከፍንጅ መያዝ እየቻልን ዝም ብለን ካሳለፍናቸው በኋላ ሰርቀው ከሄዱ በኋላ ብንናገር ምን ዋጋ አለው? ከእዬዬ በቀርስ ምን ይተርፈዋል? ጉዳዩ ነግ በእኔ ነው፡፡ እኛ ብዙ ሆነን አንድና ሁለት ኪስ አውላቂ መያዝ እንዴት ያቅተናል? ተባብረን ለፖሊስ መስጠትስ ለምን ይሳነናል? ኧረ ጎበዝ ተው እንተባበር? ማለት ነው የሚቻለው፡፡ ለነገሩ አንዳንዱ እግረኛ መንገድ ላይ የሚደባደቡ ሰዎችን ወይም ፆታዊ ጥቃትንስ መቼ ላስቁም ይላል? መስተካከል ያለበት ህፀፃችን ነው፡፡

ከእነዚህ ልማዶች ተነስቶ ነው ኮንትሮባንዱ፣ ቅሸባው፣ አጭበርባሪነቱ፣ ገቢ መሸሸጉ፣ ሕገወጥ ምንዛሪው፣ ወዘተ እየተባባሰ ያለውና ትግሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ንቅናቄ ሊያጅበው ግድ ይላል፡፡

መብራት ጠላፊዎች

ይህኛውን ንፁስ ምዕራፍ በመብራት ሰየምነው እንጂ ለውኃ፣ ለፍሳሽ ማስወገጃ፣ ለስልክም ሆነ ለሌላው መሠረተ ልማት አጠቃቀምም ይመለከታል፡፡ እነዚህኞቹ ሥርዓት የለሾች መብራትን ከአንዱ ምሰሶ ወይም ከአንዱ ግቢ ወደ ሌላው ምሰሶ ወይም ቤት የሚጠልፉ ናቸው፡፡ መብራት ሥርዓትን ባልተከተለና መሥሪያ ቤቱ በማያውቀው አሠራር ከተለጠፈ፣ እየተጠላለፈ ወይ ገመዱ ይበጠስና ወይም ይቃጠልና በመንገደኛውና በአካባቢው ላይ አደጋ ያደርሳል፣ ወይም መብራት ይቋረጣል፡፡ መንግሥትንም ያገኝ የነበረውን ጥቅም ያሳጣል (ተራ ብረት በውንብድና ለመሸጥ ወደ አንድ ከተማ የሚገባ መስመርን እስከ መበጠስ የሚደርስ ስግብግብነትም የሥርዓት አልበኝነቱ መገለጫ ነው)፡፡

ይህ የመብራት ጠለፋ ወይም የመሠረተ ልማት ሌብነት የሚካሄደው እዚሁ እኛ ዓይናችን ሥር ነው፡፡ በተለይ በአንዳንድ ወፍጮ ቤቶች፣ መበየጃና ጋራዦች፣ የግንባታና ምግብ ማምረቻዎች፣ ወዘተ በሕገወጥ ሰዎች መሆኑንም እናውቃለን፡፡ ሰውየው ባለሙያ አለመሆኑንም እንረዳለን፡፡ ‹‹ተው›› ለማለት ግን እንፈራለን፣ ወይም በይሉኝታ ዓይተን እንዳላየን እናልፋለን፡፡ አደጋ ሲደርስ ወይም መብራት ሲጠፋብን ግን ምክንያቱን እያወቅን መንግሥትን ተጠያቂ እናደርጋለን? ይህ እስከ መቼ ይሆናል?

መንግሥት በእያንዳንዱ ሽቦ ወይም መስመር ላይ ጠባቂ እንዲያቆምልን መፈለጉም አይበጀንም፡፡ እንድንፈራና እንድንዳከም ስለተሠራብን እንጂ ተደራጅተንና አንድ ሆነን ሥርዓት አልበኝነትና ወንጀልን ካልታገልን ነገ መቆሚያ መቀመጫ ነው የምናጣው፡፡ እንደ ሰው የችግሩ ምክንያቶች ራሳችን በመሆናችን መፍትሔዎቹም እኛው መሆናችንን ማመንና መታገል ነው ያለብን፡፡

በአጠቃላይ እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ያሉብን አጉል ፀባያት (ህፀፆች) በጣም ብዙ ናቸው፡፡ መፍትሔው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን እኛው ዜጎች ራሳችን ብቻ የሆንባቸው የሥርዓተ አልበኝነት ድርጊቶቻችን ተቆጥረው አያልቁም፡፡ ጥገኛው፣ ፅንፈኛውና አጋጭቶ አዳሪው ያሻውን እያረገፈ የሚያባላንም እንደ ሕዝብ ካለን አለመተባባርና ዳተኝነት ተነስቶ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ለመፍትሔው ጣታችንን ወደ ራሳችን ማዞር እስካልቻልን ድረስ ሁልጊዜም ተጎጂዎቹ ራሳችን ብቻ መሆናችንንም እንረዳ፡፡ መንግሥት ሚናውን ካልተወጣ የሚቀየር ተቋም እንጂ፣ የሕዝብ ሚና ያለው አካል አይደለምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...