Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የአሁናችን ማረፊያና ማስታወሻ አንዱ የባቡሩ ሐዲድ ነበር

ትኩስ ፅሁፎች

ሕገ ተፈጥሮ ሆኖ ሁሉም ነገር በሒደት በእንቅስቃሴና በለውጥ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የሰው ልጅ ያለመርሳትና ያለመረሳት ብርቱ ምኞቱ ይሳካ ዘንድ በተለያየ መንገድና ብልኃት ‹‹አሁንን›› አንቆ ለማቆየት ይታገላል፡፡ ስለ ‹‹አሁን›› ግዝፈት ከሳይንቲስቶቹ ከነአይንሽታይን ሬለቲቪቲ ይልቅ ለኛ ለተርታዎቹ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ ሠዓሊዎች ሸራ ላይ መልክና ትርጉሙን መረዳት ይቀላል፡፡ ሥዕሎቹ ከትናንትና ከነገ ከቅድምና ከበኋላ ካለፈውና ከመጪው በላይ አግዝፈውና አስፍነው ‹‹አሁንን›› ትልቅ ቦታ ሰጥተውታል፡፡ የመኖር መረጋገጫው አሁንን አለማጣት ነው፡፡ አነሳሴ ስላልተካንኩበት ፍልስፍና ለማውራት አይደለም ይልቁንም በጣም ተራ የሆነች  ነገር ግን የተኖረች አጋጣሚን ለማካፈል ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ጂቡቲ የሚምዘገዘገው የአገራችን የባቡር ሐዲድ ብዙ ከተሞችን ነው አቋርጦ የሚያልፈው፡፡ ከነዚህ ከተሞች ብዙዎቹ ከባቡሩ መዘርጋት በኋላ ሐዲዱን ተጠግተው የተቆረቆሩ ናቸው፡፡ እንደ እኔ ከነዚህ ከተሞች በአንዱ ተወልዶ ላደገ ሰው ሐዲድና ባቡር ከመንገድና ከተሽከርካሪነት ያለፈ ትርጉም አለው፡፡ ላጋር፣ አቃቂ፣ ዱከም ደብረዘይት/ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ናዝሬት/አዳማ መተሐራና አዋሽ እያለ ይቀጥላል፡፡

የየባቡሩ ሰያሜዎች የሠራተኞቹ የሥራ ድርሻዎች የጣቢያዎቹ ቅጥሮች የመንገደኞቹ ዓይነት የጭነቱ ምስጢርና የጉዞው ተውኔቶች ብቻቸውን መጽሐፍ የሚወጣቸው ሰፋፊ ታሪኮች ናቸው፡፡ ዛሬ ግን ላወራው ያሰብኩትን ነጠላ ታሪክ ብቻ ላንሳ፡፡ እነዚያን ሁሉ ከተሞች እያቋረጠ የሚምዘገዘገው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ነባሩ የሐዲድ መስመር ከአምስት ቀናት በፊት ልክ በመቶ ሃያኛው ዓመቱ እየተነቀለ መሆኑን አብሮ አደጎቼ ከቢሾፍቱ ደውለው ነገሩኝ፡፡

በርግጥ አዲስ ዘመናዊ መስመር እንደተተካ አይቻለሁ፡፡ ለአሮጌው መነቀልም ቅዋሜ የለኝም፡፡ ነገር ግን ደብረ ዘይት ነጋ ጠባ ሳላሰልስ ከምመላለስባቸው ምክንያቶቼ አንዱ የባቡሩ ሐዲድ መኖር ነበር፡፡ የሐዲድ ላይ ዕርምጃና የሐይቅ ላይ ዋና ለደብረ ዘይት ልጆች ልናጣው የማንወደው ምናባዊ ‹‹አሁናችን›› ነው፡፡ የሐዲድ በላይና የሐዲድ በታች ልጆች መባባል እኮ ቀረ አለኝ አንድ አብሮ አደጌ ደውሎ፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ሐዲድ ከልባችን ከማይነቀልባቸው ታሪኮች መካከል ሁለቱ ሁሌም ካይነ ሕሊናዬ አይጠፉም፡፡ በሚያቅበጠብጠው የጉርምስናችን ወራት በአገራችን ወግ መሠረት (ዛሬም በአብዛኛው ያው ነው) የጀንበርን መጥለቅ ተከትለን ልጃ ገረዶች ለማሽኮርመም እንደ ሐዲድ መስመር ተመራጭ ቦታ አልነበረንም፡፡ ምክንያቱም ሐዲድ ምንም ቢጨልም ስፋቱም ከፍታውም ተመሳሳይ ወጥና እንቅፋት አልባ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ በጎን ስፋቱ ሊያራምድ የሚችለው ሁለት ሰው ብቻ በመሆኑ ለአብሮ ሂያጅ ሁሉ የመተቃቀፍ ሰበብ መሆኑ በራሱ ሌላው ተመራጭነቱ ነው፡፡ ከሕፃንነታችን አንስቶ ተሯሩጠንበት በሐዲድ ላይ የአንድ ዕርምጃ ልክ ምን ያህል እንደሆነ በደመነፍስ ስለተዋሀደን ዘና ብለን ለመጓዝም ፈጥነን ለመሮጥም ሐዲዱን በዓይን ማየት አይጠበቅብንም፡፡ ጀምበር ከጠለቀችም በኋላ ቢሆን በምቾት ተቃቅፎም ተዛዝሎም ለመዞር እንደ ሐዲድ ተመራጭ መንገድ አልነበረም፡፡ ሐዲድን ባየን ቁጥር እነዚያ ስኳር ስኳር የሚሉ ቅፅበቶች መዳፎቻችንን ከጣልንባቸው ትከሻና አንገቶች ጋር እንደ ህልም ውል ማለታቸው አይቀርም፡፡

ሌላው ሐዲድ በሐምሌ ወራት/የቡሔ መዳረሻ ቀናት ላይ በየመንደሩ ኩታራ ይወረራሉ፡፡ እያንዳንዱ የሐዲድ አግዳሚ ብረት ካንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ለቃጫ መፋቂያ የተሠራ ገበታ እስኪመስለን ድረስ በምቾት የጅራፋችንን ገመድ እናመርትበታለን፡፡ ሐምሌ የውሪው እጅና እግር ሁሉ በሚያሳክክ ሽፍታ ይወረራል፡፡ ቃጫ ሲፋቅ በሚፈናጠረው ፈሳሽ ቆዳ ተቆጥቶ ይደበድባል፡፡ በዚያን ሰሞን ያለማቋረጥ ማከክ አያሳፍርም፡፡ ነገር ግን በቀናት ውስጥ ስለሚድን መቆሳሰሉንም ቢሆን ማንም ከቁብ አይቆጥረውም፡፡ ጅራፍ ለመግመድ የቃጫ ክር ግድ ስለሆነ የቃጫ ተክል እየቆረጡ ተስተካክሎ ከተዘጋጀው ሐዲድ ላይ በቀኝ እግር የቃጫውን ጫፍ ጨምድዶ ረግጦ በማጭድ ወይም በደጋን ብረት ወደፊት እየዳመጡ ፈሳሹና ጄሉን በመግፈፍ ፋይበሩን ማስቀረት ተለምዷል፡፡ ከአዝናኝነቱ በላይ ትልቁ ጥቅሙ የሚፈልጉትን ነገር በራስ እጅ ሠርቶ ማሟላትን እንደ ጨዋታ መልመዱ ነበር፡፡ ስለ ባቡር ሐዲዱ ሌላም ብዙ ብዙ ታሪክ አለ፡፡ የሰው ልጅ መልኩን በፎቶ ኑሮውን በቁስና በድርጊት ጨምድዶ ለማቆየት የሚመኘው ያው ትናንትንም ነገንም አሁን ለማድረግ ሲል ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የአሁናችን ማረፊያና ማስታወሻ አንዱ የባቡሩ ሐዲድ ነበር፡፡ ዛሬ ድንገት መነቀሉ በአካል ከተተከለበት መሬት እንጂ ከቶም ከልባችን ክታብ ላይ አይደለም፡፡ የኖሩትን ሁሉ ሰብስቦ አሁን የሚያደርግ ትውስታ ለዘለዓለም ይኑር!

  • በቀለ መኰንን (ተባባሪ ፕሮፌሰር) በማኅበራዊ ገጻቸው እንደከተቡት
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች