Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ለማዳመጥ መድረክ እንዲያመቻች ተጠየቀ

መንግሥት የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ለማዳመጥ መድረክ እንዲያመቻች ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መንግሥት የራሱን ድምፅ ብቻ ደጋግሞ ከማዳመጥ ወጥቶ በሁሉም አካባቢዎች ማኅበረሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለማዳመጥ የሚያስችል መድረክ እንዲያመቻች ጥያቄ አቀረበ።

ኢዜማ ጥያቄውን ያቀረበው ‹‹የሰላም ዕጦቱና አለመረጋጋት ምንጩ በጠራ የፖለቲካ መስመር ላይ መቆም ያልቻለው፣ አቋምም ሆነ አቅም የሌለው የብልፅግና አመራር ነው!›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ከ2007 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ በኋላ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን፣ የሰላም መደፍረሶችንና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለመፍታት በሚል ዕሳቤ በተደጋጋሚ አገራዊና ክልላዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ተግባራዊ ቢደረጉም፣ አዋጆቹ በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚውሉት መንግሥት ኃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ካለመወጣት የመነጩ ተቃውሞዎች ሲነሱበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው ብሏል።

ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ድንገት የተከሰተ ሳይሆን መንግሥት ኃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ባለመወጣቱ የተከማቹ አገራዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች የግለታቸው ጫፍ ላይ ሲደርሱ የተፈጠረ ነው ያለው ኢዜማ፣ ይህ ለዓመታት የታመቀው ብሶት፣ የመጠቃት ስሜትና ተስፋ መቁረጥ ገደፉን አልፎ ክልሉን አሁን ላለበት ሁኔታ ዳርጎታል በማለት ገልጿል፡፡

ኢዜማ አክሎም ከዚህ ቀደም ለነበሩ በደሎች፣ ቅሬታዎችና ሥጋቶች ተገቢውን መልስ በትክክለኛው ሰዓት አለመሰጠቱና አሁንም ከሥጋት ነፃ የሆነ ድባብ አለመፈጠሩ ውጥረቱን አባብሶ አሁን ላለበት ውጥንቅጥ አብቅቶታል ብሏል፡፡

በብልፅግና ውስጥ ያለው የጋራ ርዕይ መጥፋት፣ ከመንደርተኝት ያልወጡ እበላ ባይ ካድሬዎች የእርስ በርስ መጓተትና መካረር፣ በተለይ በየክልሉ እርስ በርስ በመጓተት ላይ ያሉ ካድሬዎች የሚመሩት የመንግሥት የአስተዳደር ድክመትና በደል የቀውስ ምክንያት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ሲል ኢዜማ ኮንኗል።

በተጨማሪም በመንግሥት ውስጥና ከመንግሥት ውጪ ያሉ ፅንፈኛ ዘውጌ ፖለቲከኞች ተናበው ግጭት እየጠመቁ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የመንግሥት የአስተዳደር ድክመት አሁን በአማራ ክልል ለተከሰተው አለመረጋጋት መነሻ መሆኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩና በመንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ተብለዋል ብሎ ከዘረዘራቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ በመላው ኢትዮጵያ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አለመከበር፣ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎችና መሰል ተግባራት መበራከትና ለእነዚህም ተገቢው ፍትሕ ሲሰጥ አለመታየቱ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ አካባቢዎች መንግሥት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ሲል የሚጠራቸው ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ተደጋጋሚ ዕገታና ጥቃት ማስቆም አለመቻሉ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በቁርጠኝነት ከመሥራት ይልቅ በማናለብኝነት የገዥውን ፓርቲ የበላይነት የሚያረጋግጡ ተግባራት መበራከታቸው ሌሎች በኢዜማ መግለጫ የተብራራ ጉዳዮች ናቸው።

የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ወደ መደበኛ የፀጥታ መዋቅር እንዲገቡ ሲወሰን ውሳኔውን በአግባቡ ለሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ ማስጨበጥ አለመቻሉና ውሳኔውን በሁሉም ክልሎች በወጥነት አለመተግበሩ ሌላው ችላ የተባለ ጉዳይ ነው ያለው ኢዜማ፣ መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ ተነሳሽነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ችግሩ ገዝፎ ከመደበኛ የፀጥታ ማስከበር ሒደት ወጥቶ የመጨረሻ አማራጭ ወደ ሆነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደርሷል ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ኢዜማ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ የሰላም ግንባታ በረዥም ጊዜ ዕቅድ በፖሊሲ ተደግፎ መሠራት ያለበት እንጂ ግጭቶች ሲፈጠሩ የእሳት ማጥፋት ሥራ ማከናወን ብቻ አይደለም ሲል አፅንኦት ሰጥቶ አሳስቦ እንደነበር አስታውሶ፣ ‹‹በሰላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ባልተሰጣቸው ቁጥር መፍትሔዎች ከጉልበት ይመነጫሉ›› የሚል አስተሳሰብ መሬት እየያዘ መምጣቱ እንደሚያሠጋው ገልጿል፡፡ አክሎም መንግሥት በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ከማርገብ ጎን ለጎን መዋቅራዊ የሆነ አገር አቀፍ ዘላቂ የሰላም መላ እንዲበጅ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ አገር አቀፍ የዘላቂ ሰላም ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት መዋቅራዊና ሕጋዊ የሰላም ግንባታ በአስቸኳይ እንዲተገብር፣ የአማራ ክልል ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ ያደረገው ኃላፊነቱን ካለመወጣቱ የመነጨ መሆኑን ተገንዝቦ ለእያንዳንዶቹ ጉዳዮች በግልጽ ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ማኅበረሰቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

መንግሥት ቁርጠኛ የሰላምና ደኅንነት ማስከበር ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ በአስቸኳይ ማከናወን እንደሚጠበቅበት፣ የመንግሥት ኃላፊዎች ቁርሾዎችን ከሚያባብሱ ውሳኔዎች፣ ተግባራት፣ ንግግሮች ወይም ጽሑፎች እንዲታቀቡ ኢዜማ ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በሚል አገሪቱ ሕግ ተቀብላ ካፀደቀቻቸው ድንጋጌዎች ውጪ መብቶችን በመጣስ የተለያዩ የገፍ እስሮችንና መሰል ተግባራትን በመፈጸም ያለውን ሁኔታ ከማባባስ እንዲቆጠብ፣ እንዲሁም ገለልተኛ የሆኑ እንደ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ ተቋማት የሚሰጡትን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

ሕዝቡም በበደል ስሜትና በቁጭት ተነሳስቶ አውዳሚ ወደ ሆነ መንገድ እንዳይጓዝ ደግሞ ደጋግሞ እንዲያስተውል የጠየቀው ኢዜማ፣ ከአብራኩ የወጣውን የአገር መከላከያ ሠራዊት በሚገባው ክብር ልክ በመረዳት አላስፈላጊ መስዋዕትነቶች እንዳይከፈሉ የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መንግሥት በአማራ ክልል ለተከሰተው ቀውስ ውይይትና ሰላማዊ መፍትሔን በማስቀደም ችግሩን ለመፍታት በሙሉ ልብ እንዲሠራ፣ የታጠቁ ኃይሎችም ለሚቀርቡ የሰላም ጥሪዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በግጭት የሚጎዳውን ንፁህ ዜጋ በመታደግ የበኩላቸውን እንዲወጡ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...