Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለ 36 ወለል ሕንፃ ግንባታ በገንዘብ እጥረት መቆሙ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት በአዲስ አባባ ከተማ ሜክሲኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1.2 ቢሊዮን ብር ያስጀመረው ባለ 36 ፎቅ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መቆሙ ተነገረ፡፡

  በ3,543 ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባው ባለአራት ብሎኮች ሕንፃ ግንባታ  አምስት ዓመታት ይወስዳል ተብሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በበጀት እጥረት ምክንያት አንድ ዓመት በሙሉ ግንባታው ሳይጀመር ቀርቷል፡፡ ዲዛይን ተሠርቶለት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት እንደነበር የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ተናግረዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት የለውጥ ሥራ ሁሉን ዘርፍ የዳሰሰ በመሆኑ ሕንፃውን ለማስገንባት የገንዝብ እጥረት በማጋጠሙ፣ ቅድሚያ ትኩረት የሚስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

አቶ ሽፈራው በተቋማቸው የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና በ2016 ዓ.ም. የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2015 በጀት ዓመት 522,032 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ፣ 353,144 ደንበኞችን ከኃይል ጋር በማገናኘት የዕቅዱን 67.65 በመቶ ማስመዝገቡን አቶ ሽፈራው አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ማስቀጠያና ከንብረት ማስወገድ 37 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 35 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ከአጠቃላይ ገቢው ከኢነርጂ ሽያጭ ለመሰብሰብ ከታቀደው 27 ቢሊዮን ብር ውስጥ 25 ቢሊዮን ብር አሳክቻለሁ ብሏል፡፡ በአጠቃላይ የተሰበሰበው የኢነርጂ ሽያጭ ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 22 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ ከተሰበሰበው 35 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃየል 14 ቢሊዮን ብር የኃይል ግዥ ክፍያ መፈጸሙን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ማስቀጠያ ዘጠኝ ቢሊዮን ብርና ከአሮጌ ንብረት ሽያጭ 240 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አክለዋል፡፡

በተጠናቀቀው 2015 ዓ.ም. የዲሲፕሊን ችግር በታየባቸው 1,060 ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች መውሰዱን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ለ288 ሠራተኞች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ719 ሠራተኞች  ገንዘብ ቅጣት፣ 39 ሠራተኞች ስንብት፣ እንዲሁም ዘጠኝ ሠራተኞች ከቦታቸው ተነስተዋል ተብሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለ19,568 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን፣ በተጀመረው የ2016 በበጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32.8 ቢሊዮን ብር፣ ከልዩ ልዩ ገቢዎች ማለትም ከማያገለግሉ ዕቃዎች ሽያጭ 260  ሚሊዮን ብር፣ ከአዲስ ኃይል አገልግሎት ማስቀጠያ 11.9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 45 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብና 600 ሺሕ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች