Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ክሶች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ክሶች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ቅሬታዎችና አለመግባባቶች ሳቢያ፣ የሚቀርቡ ክሶች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የፍትሕ ሚኒስቴር ኢንቨስትመንትን መነሻ አድርገው በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርቡ ዓለም አቀፍ ክሶች በሚመሩበት፣ እንዲሁም አማራጭ በሆኑ መንገዶች እልባት እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ነው፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ጌዴዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ እየቀረቡ ያሉ የኢንቨስትመንት ክሶች ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል ብለዋል፡፡ አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለቀረቡት ክሶች ምላሽ በመስጠትና በመከራከር እንዲሁም ድርድር ላይ ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ሰፋፊ ጥረቶች በሚደረጉበት በዚህ ወቅት የኢንቨስትመንት ክሶች መበራከት አሉታዊ ጎኑ ያመዝናል።

የክሶቹ ክርክሮች በአገሪቱ ሊፈጥሩ ከሚችሉት የተዛባ ምሥል በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጡ የሚችሉ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስተሮች ቅሬታና አቤቱታ አፈታት ሥርዓት ማሻሻል፣ ማጎልበት፣ እንዲሁም አለመግባባቶችን በአማራጭ መንገድ መፍታትና ክርክሮችን ከምንጫቸው ማድረቅ እንደሚገባ ጌዴዮን (ዶ/ር) አሳስበዋል።

ከላይ ከተገለጹት አማራጮች አልፈው ወደ ክርክር የሚያመሩ ጉዳዮችንም የኢትዮጵያን መብትና ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ በቅንጅት የመያዝና የመምራት፣ እንዲሁም የተናበበ አሠራርን መተግበር እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

ሪፖርተር የተመለከተውና ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመቀነስ፣ የተቀናጀ ቅሬታ አፈታትና ምላሽ ሰጪነት ለማዳበር ባለፈው ወር መጀመሪያ ለተዘጋጀው አገራዊ ውይይት መድረክ አጭር ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡ ለኢንቨስትመንቶች ተገቢው ጥበቃና ድጋፍ ከማድረግና ዘርፉን ከማበረታታት አኳያ በሥራ ላይ በሚገኙት ብሔራዊ ሕጎች ውስጥ መብቶችና ግዴታዎች የተካተቱ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ውስጥም በተለይ ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮችን የሚጠብቁ የተለያዩ ተጨማሪ ስታንዳርዶች ተካተው እንደሚገኙ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ከላይ በተገለጸው መሠረት ኢንቨስተሮች ያሏቸውን መብቶች ከመጠቀምና ሥራዎቻቸውን ከማሳለጥ አኳያ የተለያዩ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች ሲያቀርቡ ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ኮሚሽንና ኢንቨስትመንቱ በሚካሄድባቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተዋቅሮ ከአገልግሎትና ተያያዥ ጥያቄዎች ጋር የተገናኙ የተለያዩ ምላሾች ሲሰጡ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ የፈረመቻቸው የሁለትዮሽ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ለኢንቨስተሮች ከሚሰጡት ሰፊ ጥበቃ በመነሳት፣ እንዲሁም ለቀረቡ ጥያቄዎች በቂና በተፈለገው ጊዜ ምላሽ ካለመስጠት ጋር የተያያዙ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የያዙ ክሶች በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶችና በውጭ አገር የዳኝነት አካላት እየቀረቡ እንደሚገኙ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

በኢንቨስተሮች እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎችና ክሶች ይዘት በጥቅሉ ሲታይ ከተቋማት የኢንቨስትመንት ጥበቃ ጋር ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ወቅታዊ መረጃና ምላሽ አለመስጠት፣ ከፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ ለጠፉ ኢንቨስትመንት ሀብቶች ካሳ መጠየቅ፣ የኢንቨስትመንት መሬት በወቅቱ ካለመመቻቸት ጋር በተገናኘ ለሥራው የመጡ ዕቃዎች ብልሽትና ለወደብ ኪራይ የወጡ ወጪዎችን የሚጠይቁ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ኢንቨስትመንት ከተጀመረ በኋላ በወጡ ሕጎችና በአስተዳደራዊ ውሳኔዎች ለደረሱ ጉዳቶች ኪሳራ የሚጠይቁ፣ ከአካባቢ ጥበቃና ግብር ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ጋር በተያያዘ ኢንቨስትመንታቸውን ለማስቀጠል በመቸገራቸው ለደረሰው ኪሳራ ክፍያ የሚጠይቁ፣ ዕቃዎችን ከግብር ነፃ ፈቃድ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ረገድ ለገጠማቸው መጉላላት፣ እንዲሁም ትርፋቸውን ወደ አገራቸው ከማስተላለፍ አኳያ የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ አለመለቀቅ ጋር ተያይዞ ለደረሰባቸው ኪሳራ ካሳ የሚጠይቁና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ የክርክር ደረጃቸውም ከፊሉ የግልግል ዳኝነት ክስ ለመጀመር የቀረበ ጥያቄ/ማሳወቂያ አቅርበው ሒደት ላይ ያሉ ሲሆኑ፣ ከፊሉ ካሳ እንዲከፈላቸው ዓለም አቀፉን ቋሚ የግልግል ዳኝነት ማዕከል (Permanent Court of Arbitration) ጨምሮ በሌሎች በውጭ አገር በሚገኙ የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከላት የኢንቨስትመንት ክስ አቅርበው በክርክር ላይ የሚገኙና አንዳንዶቹም በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተቋጩና ውሳኔ ያገኙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው ባደረጉት ንግግር፣ በአገሪቱ በኢንቨስትመንት በሚሰማሩ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች መካከል ያለውን መብትና ጥበቃ ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ፣ የኢንቨስተሮች ልየታ ሥራን ብቁ በሆነ ምርመራ መምራት፣ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያን ሕጎች እንዲያከብሩ መከታተል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ቅሬታና አለመግባባቶችን በአፋጣኝ መፍታትና በዘርፉ ሰፊ ግንዛቤን መፍጠር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም በተቋማት መካከል ተገቢውን ቅንጅታዊ አሠራር የማዳበር ሥራዎች በስፋት ሊተኮርባቸውና ሊሠራባቸው ይገባል ብለዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴርም በሁለትዮሽ ስምምነቶቹ ዙሪያ እየተደረገ በሚገኘው ጥናት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ በቅሬታና አለመግባባት አፈታት ዙሪያ ቅንጅታዊ ተሳትፎ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕጎችን በተመለከተ ለሚመጡ አዳዲስ ኢንቨስተሮች በሚመች ሁኔታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደሚያመቻች፣ የሚመለከታቸው ተቋማት የሕግ ክፍሎች ለዘርፉ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ እንደሚከናወን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር ባሰናዳው የውይይት መድረክ ላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳትፎ የሚያደርጉ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም በዘርፉ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች የተሳተፉ ሲሆን፣ በመድረኩም ኢትዮጵያ በተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች፣ በኢንቨስትመንት ቅሬታ አያያዝ ሥርዓት፣ በአማራጭ የአለመግባባት አፈታት፣ በክርክሮች አያያዝና አመራር ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየትም በዘርፉ ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን፣ ተቋማት በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት የማይናበቡ መሆኑን፣ የሕግ አተገባበር መላላት፣ የኢንቨስተሮች ልየታ ክፍተትና የመሳሰሉ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ከተሰጡት ዘርፈ ብዙ ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ የዳኝነት ሰጪ አካላት ዘንድ በሚከስባቸው ወይም በሚከሰስባቸው ጉዳዮች ላይ፣ መንግሥትን በመወከል ክስ/መልስ የማቅረብና ክርክር የማድረግ፣ ድርድር የማከናወንና ውሳኔዎችን ማስፈጸም ይገኝበታል፡፡

በውይይቱ መጨረሻም የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋማት ቅንጅትን በተመለከተ የክልልና የፌዴራል የሚመለከታቸው ተቋማት በጉዳዩ ላይ ለመምከር እንዲችሉ ቋሚ የሆነ የመገናኛ መድረክ እንዲኖራቸው፣ እንዲሁም ሥራቸውን በቅንጅት መሥራት የሚያስችላቸው የአሠራር ሥርዓት በጥናት ላይ ተመሥርቶ መነሻ እንደሚያዘጋጅና ከሁሉም ባለድርሻ ጋር በአጭር ጊዜ ተገናኝቶ በመምከር አሠራሩ ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት እንደሚወስድ ተገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...