Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልፈር ቀዳጅ የሰብል ብዝኃነት ጥበቃ ባለሙያና የገበሬዎች መብት ተሟጋች መላኩ ወረደ (ዶ/ር)...

ፈር ቀዳጅ የሰብል ብዝኃነት ጥበቃ ባለሙያና የገበሬዎች መብት ተሟጋች መላኩ ወረደ (ዶ/ር) ሲታወሱበሔኖክ ያሬድ

ቀን:

የኢትዮጵያ አገር በቀል ዕፀዋትና አዝርዕት ዘራቸው እንዳይጠፋ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ሲያስገነዝቡ፣ ብዝኃ ሰብልን የሚፃረረው ጂኤምኦ ዕውን እንዳይሆን ሲሞግቱ የኖሩ ናቸው፡፡ የዓለም ሎሬት መላኩ ወረደ (ዶ/ር)፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተለይም በብዝኃ ሕይወት ጥናትና ምርምር ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፉ የአማራጭ ኖቤል ሽልማትንም የተቀዳጁ ናቸው፡፡ በ1968 ዓ.ም. ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን የአፍሪካ የመጀመርያና ትልቁን የዘረመል (ጂን) ባንክ ያቋቋሙ ታዋቂ የጄኔቲክስና የግብርና ባለሙያ ነበሩ፡፡ በዋና ዳይሬክተርነትም መርተውታል፡፡ የዘረመል ባንክ በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ የሰብል ዝርያዎችን ያካተተ ከ80,000 በላይ የተለያዩ ዝርያዎችን የያዘ አስደናቂ ስብስብ መያዙም ይወሳል፡፡  በ1990 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዘረመል ባንክ በመላኩ ወረደ (ዶ/ር) መሪነት በሰብል ብዝኃነት ጥበቃ ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ በማሳደር ከዓለም ምርጥ ከሚባሉት ተርታ መሰለፉን <A pioneer crop diversity conservationist and farmers’ rights advocate > በሚል ርዕስ ስለ ፈር ቀዳጁ የሰብል ብዝኃነት ጥበቃ ባለሙያና የገበሬዎች መብት ተሟጋች መላኩ ወረደ (ዶ/ር) ሕይወትና ሥራ የጻፉት ተሾመ ሁንዱማ (ዶ/ር) እና ባዩሽ ፀጋዬ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

ፈር ቀዳጅ የሰብል ብዝኃነት ጥበቃ ባለሙያና የገበሬዎች መብት ተሟጋች መላኩ ወረደ (ዶ/ር) ሲታወሱበሔኖክ ያሬድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ለኩባውያን ባለሙያዎች ሥልጠና በሰጡበት ወቅት

 እንደ ባለሙያዎቹ ጸሐፍት ማብራሪያ፣ የጄኔቲክስ ባለሙያው መላኩ (ዶ/ር)፣ በአረንጓዴ አብዮት ዘመን በሳይንሳዊ ዕውቀት ብቻ መመራት አለብን ተብሎ የተመሠረተውን ዓለም አቀፋዊ አመለካከት ለመለወጥ ከታገሉ ፈር ቀዳጅ ሊቆች መካከል አንዱ ናቸው።

የሰብል ብዝኃነትን ከአያያዙ ጋር ለረዥም ጊዜ ለመጠበቅና የምግብ ምርትን ለዘለቄታ በማስቀጠል ረገድ ያላቸው ጥልቅ ግንዛቤ፣ ከባልደረቦቻቸው ጋር ተጨማሪ የሰብል ዘረመል ሀብት ጥበቃ ስትራቴጂ ነድፈዋል።

መላኩ (ዶ/ር) የገበሬዎችን ዕውቀት ግምት ውስጥ በማስገባት አርሶ አደሮችን ማስቀደም አስፈላጊ መሆኑን በጉልህና በፅኑ፣ በተለይም የግብርና ምርትንና የምግብ ዋስትናን የሚጎዱ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የአገር ውስጥ የምርምር አቅምን ማሳደግ የሰብል ብዝኃነትን ለመጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ያምናሉ።

ለ14 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጂን ባንክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በሠሩበት ጊዜ (በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት የሚገኝ) በገበሬዎችና በባንኩ መካከል ትብብር ለመፍጠር ተጨባጭ ዕርምጃዎችን ወስደዋል ይላል ዜና ሕይወታቸው፡፡

በኢትዮጵያ በ1977 ዓ.ም. በተከሰተው አስከፊ ድርቅና ረሃብ ወቅት ይህም ለበርካታ አርሶ አደሮች በተለይም በአንድ ወቅት የሰብል ብዝኃነት ማዕከል በነበሩ አካባቢዎች በተለይም የማሽላና የስንዴ ዘር ላይ ጉዳት አድርሷል። መላኩ (ዶ/ር) ለተከሰተው አስከፊ ድርቅ ምላሽ በመስጠት የጠፉትን ዘሮች ዳግም እንዲመለሱና ብዝኃ ሰብሉ እንዲጠበቅ ከጂን ባንኩ በመውሰድ የጠፋውን ብዝኃነት ወደነበረበት እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ ይህንን የሰብል ብዝኃነት ጥበቃና ለዘላቂ ግብርና የመጠቀም ሥራ ‹‹የኢትዮጵያ አካሄድ›› (The Ethiopian Approach) በማለት ተጠቅሷል።

‹‹የኢትዮጵያ ሥርዓት›› በተለይ ለየት ያለ ነው፣ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ሳይንቲስቶችን በመሳብ የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ።

በአካዴሚው ዓለም ውስጥ ካከናወኗቸው ተግባራት አንዱ የቀድሞ የአዋሳ  ግብርና ኮሌጅ መሥራች ዲን በመሆን ማገልገላቸው ሲሆን ኮሌጁ አሁን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥር ካሉት ከፍተኛ የግብርና ኮሌጆች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

በጅማ፣ አሥመራ፣ ሐሮማያ፣ ነብራስካና ዊስኮንሲን በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ዕውቀታቸውን ከማበርከታቸው ባለፈ ከ20 በላይ ሳይንሳዊ ሥራዎቻቸውንም  በዓለም አቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል።

በተለይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና በደርዘን የሚቆጠሩ ሌሎች አፍሪካውያን፣ እስያውያንና ላቲን አሜሪካውያን በሰብል ብዝኃነት አያያዝ ሥርዓት በማሠልጠን ጉልህ ሚና መጫወታቸውም ተጠቅሷል፡፡

መላኩ (ዶ/ር) እ.ኤ.አ. በ1989 የኢትዮጵያን የዘረመል ብዝኃነት ለመጠበቅ ላደረጉት አስደናቂ ተግባር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘረ መል (ጅን) በማቋቋምና አነስተኛ ገበሬዎችን በተግባር በመደገፍ ላሳዩት ብልጫ የራይት ላይቭሊሁድ አዋርድ (የአማራጭ ኖቤል ሽልማት በመባልም ይታወቃል) ተሸልመዋል።

እ.ኤ.አ. በ2016 በእንግሊዝ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የባዮግራፊካል ሴንተርም ‹‹ለጄኔቲክ ሀብቶች ማኅበረሰብ አገልግሎት›› የክብር ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡ በኢትዮጵያም ብሔራዊ የአረንጓዴ ሽልማትን ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ከፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ለመላኩ (ዶ/ር) አስተዋጽኦ ዕውቅና በመስጠት ከጽሕፈት ቤቱ ሕንፃዎች አንዱን በስማቸው ሰይሟል።

ወረደ በሙያቸው ልዕልና የተጎናፀፉ በመሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት የዕፀዋት ጄነቲካዊ ሀብቶች ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የዕፀዋት ጄነቲካዊ ሀብቶች ተቋምና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን ኢንተርናሽናል የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል።

በጡረታ ጊዜያቸው ሥራቸውን ከኢትዮጵያ አልፎ አስፋፍተዋል። በእስያና አፍሪካ ውስጥ በርካታ የጂን ባንክ ባለሙያዎችንና ወጣት ሳይንቲስቶችን በእርሻ ላይ የተመሠረተ የአገር በቀል ዘር አጠባበቅን በማስተማር ንቁ ነበሩ።

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር ከነበረው ዓለማያ እርሻ ኮሌጅ (አሁን ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ)፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪዎቻቸውን ከአሜሪካ ነብራስካ ዩኒቨርሲቲ በአግሮኖሚ አግኝተዋል፡፡

በሳይንስ ዘርፍ የ2008 ዓ.ም. የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊነትን ባገኙበት ወቅት በቀረበው ዜና ሕይወታቸው እንደተገለጸው፣ በተለያዩ የግብርና ኮሌጆች በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በወንጂ ስኳር ፋብሪካ በተመራማሪነት ተቀጥረው በሚሠሩበት ወቅት ‹አረማሞ› በመባል ለሚታወቀውና  ምርት ያስተጓጉል ለነበረ  በሽታ መፍትሔ ያገኙ ሳይንቲስት ናቸው፡፡

በዶክትሬት ጥናታቸው በዓለም ላይ በሚገኙ አራት ሺሕ የስንዴ ዝርያዎች የፕሮቲን ይዘት ላይ ምርምር አድርገው አራቱን በጣም ምርታማ የሆኑትን ለይተዋል፡፡ ከአራቱ ሦስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ፖርቱጋል ውስጥ የሚበቅለው አራተኛውም ከኢትዮጵያ የተወሰደ ነው በሚል ታሪክ ጠቅሰው ሞግተዋል፡፡

የዓለም ሎሬት (ዶ/ር) መላኩ ወረደ ከአብዛኛው ሳይንቲስቶች የሚለያቸውና ብዙ ጊዜም በአደባባይ ሲናገሩ የሚደመጡት፣ ‹‹ለገበሬው ዕውቀት ቦታ መሰጠት አለበት፡፡ እነርሱን ማዳመጥ አለብን፤›› በሚለው አመለካከታቸው ነው፡፡ ‹‹ሳይንቲስቱ የራሱን ግኝት እነርሱ ላይ መጫን ሳይሆን የእነርሱን ባህላዊ አሠራር መሠረት አድርጎና አቀናብሮ መጓዝ ያስፈልጋል፤›› በሚለው አቋማቸውና ተግባራቸው ይታወቃሉ፡፡

የጂኤምኦ (GMO) አንዱ ዋና ሥጋት

የጂኤምኦ (GMO) አንዱ ዋና ሥጋት ብለው፣ አግሮኖሚስቱ (Genetics and Breeding) ሎሬት መላኩ ወረደ (ዶ/ር) ቃል በቃል የተናገሩትን ልጃቸው ልጅ ተድላ መላኩ፣ በግንቦት 2012 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደሚከተለው አሥፍረውታል፡፡

‹‹ጂኤምኦ ዋናው ተጽእኖ ዳይቨርሲቲ (ብዝኃነት) የሚባለውን ነገር ድራሹን ያጠፋዋል። የሞኖክሮፒንግ (Monocropping) ችግር ብቻ አይደለም። ሆሞጂንየስ (Homogeneous) የሆኑ አንድ ዓይነት (materials) ነው በሰፊው፣ ትልቅ (continuous) በሆነ ቦታ ላይ የሚያመርቱት። እናም “one size fits all” የሚለውን መመሪያ ይይዙና ነው።

‹‹ለእንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አገር አደጋው ምን መሰለህ፤ ቶፖግራፊው ላይ ብትመለከት፣ እና የአፈሩን (soil) ባህርይ (charactersitic) ብትመለከት፣ በአንድ አንድ ኪሎሜትር እንኳን ልዩነቱ ብዙ ነው። ዩኒፎርሚቲ (ወጥነት)የለውም። አንድ ሞኖክሮፕ (monocrop) አምጥተህ እሱን ላልብስ ብትል አይሠራም፣ ዳይቨርሲቲውን ያጠፋዋል። ዳይቨርሲቲ ነው እስካሁን ያዳነን።

‹‹ዋናውና ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ባለ ሦስት መንገድ የዳይቨርሲቲ ሲስተም በዘመን ሒደት ፈጥረዋል። ይህን ነው ማሳደግ (በቴክኖሎጂ ማገዝ) የሚያስፈልገው። የዛሬ አርባ ዓመት ጀምሮ ስለ ባዮቴክኖሎጂ ከዓለም የዘረ መል ሳይንቲስቶች ጋር ስንመራመር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እስከ ጂኤምኦ መምጣት ድረስ ባለው ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ ውይይትና ሒደት ውስጥ አለሁ። ስለዚህ በደንብ መወያየት ይቻላል።

ከአባታቸው ቀኛዝማች ወረደ ገብረ ኪዳንና ከእናታቸው ከወ/ሮ አምሳለ ወዳጄነህ በአዲስ አበባ ከተማ ሚያዝያ 16 ቀን 1928 ዓ.ም. የተወለዱት የዓለም ሎሬት መላኩ ወረደ (ዶ/ር) ዓረፍተ ዘመናቸው የተገታው ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በ87 ዓመታቸው ነው፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም ሐምሌ 26 ቀን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ ሎሬት መላኩ ወረደ (ዶ/ር) ባለትዳርና የሦስት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ፡፡

መቋጫ

‹‹ግብርናን አስመልክቶ አባቴ (ዶክተር መላኩ ወረደ) ዕድሜ ዘመኑን በግብርና እና በብዝኃ ሕይወት ሳይንስ ላይ ጥናት ሲያካሂድ የኖረ ሰው ነው፤›› የሚሉት ልጃቸው  ተድላ መላኩ ናቸው።

‹‹የግብርና ክብሩ›› በሚል ርዕስ በማኅበራዊ ገጻቸው ስለአባታቸው አቋምና ዕይታ እንደሚከተለው ገለጹ፡፡

‹‹አባቴ የብዝኃ ሕይወት ሳይንቲስት (ተመራማሪ) እንደመሆኑ ለግብርና እና ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ክብር ከምንም በላይ የላቀ ነው። ሳይንስ ያልደረሰበትን ሕያው (organic) የምድር ሥነ ባሕርይና የዕፀዋት ጥቅም ደጉ አርሶ አደር በዘመን ጥበብ ያውቀዋል ይላል።

በሳይንሱ ዓለም አሉ ይባሉ ከነበሩ ምሁራን ጋር የአርሶ አደሩን ጥበብና እውቀት እየመሰከረ፣ ሳይንስ አርሶ አደሩን ማገዝና ሥራውን ማቅለል ነው እንጂ ያለበት፣ የአርሶ አደሩን ጥበብና እውቀት የሚያጠፋ መሆን የለበትም እያለ ሳይንስ አርሶ አደሩን በምን መንገድ ማገዝና ‘assist’ ማድረግ እንደሚችል ያጠና እና አርሶ አደሩን በሳይንሳዊ እውቀት ለማገልገል የደከመ ሰው ነው።

በአገራችን እና በሕዝባችን እንደ አርሶ አደሩ የአበርክቶው ታላቅ ዋጋ ባግባቡ ያልተገለጠና የተበደለ የሕዝብ ክፍል የለም። አርሶ አደሩ ግብርናውንም፣ አርበኝነቱንም፣ መጋቢነቱንም፣ ባህል ጠባቂነቱንም፣ ሃይማኖቱንና ሥርዓቱንም፣ ሁሉንም አቅሙን ሁሉ ሰውቶ ላቡ ጠብ እስኪል እየሠራ ይችን አገር በትከሻው ተሸክሞ ይዞአታል። የሚገባውን ክብር ብቻም ሳይሆን የሚገባውን ድጋፍ እና ዋጋ ግን ፈጽሞ ያላገኘና ትኩረት የተነፈገ የማንነታችን ዓምድ ነው!

የራይት ላይቭሊሁድ መልዕክት

የዓለም ሎሬት መላኩ ወረደ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ አክብሮታቸውን ከገለጹት መካከል የሎሬትነት ክብር የሰጣቸው ራይት ላይቭሊሁድ ይገኝበታል፡፡

‹‹የመላኩ ወረደ ቁርጠኝነትና በእርሻ ላይ የተመሠረተ የአገር በቀል ዘር ጥበቃ ሥራ ምርታማነትን ከማሳደጉም በላይ ለዘላቂነት ምስክር ሆኖ አገልግሏል፤›› ሲሉ የራይት ላይቭሊሁድ ሥራ አስፈጻሚ ኦሌ ቮን ኡክኩል ተናግረዋል። ‹‹የእርሳቸው ውርስ ከድንበርም ይሻገራል፡፡ ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምድራችን ብዝኃ ሕይወት እንዲንከባከብና እንዲጠብቅ ያነሳሳል፡፡››

መላኩ ወረደ ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያን የዘረመል ሀብት በማሰባሰብና ደኅንነቱ በተጠበቀበት መንገድ በማጠራቀም ስኬትን ተጎናፅፈዋል፡፡  የእሳቸው ጥረቶች የአፍሪካን ምርጥ ተቋምና ከዓለም ከፍተኛ የጄኔቲክ ጥበቃ ሥርዓቶች አንዱ የሆነውን እንዲመሠርቱ አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...