የትምህርት ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም. የክረምት ትምህርት መርሐ ግብር እንዳይሰጥ ያስተላለፈውን ውሳኔ መልሶ እንዲያጤነው፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጥያቄ አቀረበ፡፡
ማኅበሩ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የመምህራንና የትምህርት አመራሮች የሥራ ላይ የክረምት ሥልጠና መርሐ ግብር በ2012 ዓ.ም. እና በ2013 ዓ.ም. በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያትና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት፣ በትግራይና በአጎራባች ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ትምህርት መከታተል አለመቻላቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህም በተጠቀሰው ጊዜና ምክንያቶች የመምህራን ሥልጠና በመራዘሙ፣ በመምህራን የደረጃ ዕድገትና የትምህርት ማሻሻያ አያያዝ ላይ ችግር መፈጠሩን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ኮቪድ በሥልጠናው ላይ ያሳደረው ጫና ሳይካካስ፣ በ2015 ዓ.ም. ክረምት የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ሥልጠና እንደማይሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በደብዳቤ ማሳወቁ ማኅበሩን እንዳሳሰበው፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ለትምህርት ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ አስገንዝቧል፡፡
ማኅበሩ እንደሚለው የክረምት ትምህርት ሊጀምር የሚገባው ሐምሌ መጀመርያ ላይ ቢሆንም፣ በራሱ በሚኒስቴሩ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎቹን ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መፈተኛ በማድረጉ እንጂ፣ የክረምት ተማሪዎች ችግር አይደለም፡፡ የሚኒስቴሩ ክልከላ በቀጣይም ችግር የሚፈጥርና የመልካም አስተዳደር ግድፈት ምንጭ እንደሚሆን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም የአሠራር ሥርዓት ሳይዘረጋለት ሥልጠናውን ማቋረጡ ተገቢ ስለማይሆን፣ ለዩኒቨርሲቲዎች የተላለፈው ሰርኩላር እንደገና የሚታይበት አሠራር እንዲፈጠር ጠይቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት ዓመታት የተዛነፈውን የትምህርት ካላንደር ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለማስተካከል እየሠራ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በቀሪው አንድ ወር ውስጥ ብቻ የክረምት ትምህርትን መጨረስ የማይቻልና ጊዜውን ለማራዘም እንዲስተካከል እየተሠራ ያለውን የትምህርት ካላንደር መልሶ የሚያዛባ በመሆኑ፣ የ2015 ዓ.ም. የክረምት ትምህርት እንደማይኖር ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ‹‹ከፈለጋችሁ ተቀበሉ ካልፈለጋቹህ ተውት ዓይነት ነው፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ ያነሱት ደብዳቤው ከመጻፉ በፊት ለመምህራኑ መገለጽ ቢኖርበትም፣ ምንም ዓይነት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለማኅበሩም ሆነ ለመምህራኑ አለመስጠቱ ነው፡፡
ትምህርታቸው ከተስተጓጎለባቸው መምህራን መካከል በዚህ ዓመት መጨረስ የነበረባቸው፣ የመመረቂያ ጽሑፍ ብቻ የቀራቸውና በሚሠሩባቸው ተቋማት ትምህርቱን ጨርሰው የደረጃ ዕድገት ሊያገኙ የሚገባቸው የነበሩ ቢሆንም፣ በሚኒስቴሩ ደብዳቤ ምክንያት ይህን ማግኘት አልቻሉም ተብሏል፡፡
ሪፖርተር ካነጋገራቸው ወደ ትምህርት ለመሄድ ዝግጅት ላይ ከነበሩ መምህራን መካከል አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ መምህር እንዳሉት፣ መምህራን የክረምት ትምህርት ካልወሰዱና የትምህርት ማሻሻያ ካላደረጉ ወደ ቀጣይ ዕድገት መሄድ አይችሉም፡፡ ነገር ግን የትምህርት ማሻሻያ አለማድረጋቸው ሳይሆን፣ በትምህርት ላይ ያሉና ከአምስት ዓመት በላይ በትምህርት የቆዩ ተማሪዎች አሁን መጨረስ ሲገባቸው እንዳያጠናቅቁ ተደርገዋል ብለዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም. የክረምት ትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንደጀመሩና በ2014 ዓ.ም. መመረቅ እንደነበረባቸው የሚናገሩት መምህሩ፣ በዚህ ዓመትም በሚኒስቴሩ በራሱ ችግር የተነሳ ለመመረቅ እንዳይችሉ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሚያሳዝነው ነገር ግን የትምህርት ሚኒስቴር ዕቅዱን ቀድሞ ባለማሳወቁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ጉዞ ላይ በነበሩበት ወቅት መረጃው የደረሳቸውና የተመለሱ መምህራን መኖራቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ፈንታየ ሰይድ ሌላኛው ወደ ትምህርት ለመሄድ ዝግጅት ላይ የነበሩ መምህር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የትምህርት ሚኒስቴር ያስተላለፈው ውሳኔ በግዴለሽነትና ያለ አሳማኝ ምክንያት ነው፡፡ አክለውም በአንድ በኩል የትምህርት ጥራት የሚለው ተቋም በሌላ በኩል መምህራን እንዳይማሩ መከልከል ተቃርኖ ነው ብለው፣ ‹‹ውሳኔው በግለሰብ ግብታዊ እንጂ ታስቦበት የተከናወነ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ሪፖርተር የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ሳመኤል ክፍሌን (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ጠይቋል፡፡ ሚኒስትር ደኤታው፣ ‹‹በአንድ ወር ትምህርት ተሰጥቶ መምህር መፍጠር አይቻልም፣ በዚህ በኩል ትምህርት ጥራት እየተባለ በሌላ በኩል በአንድ ወር ዲግሪ እንደተማረ ተደርጎ ይነገራል፣ ይህ አብሮ አይሄድም ስለዚህ መታረም አለበት፤›› ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ዕቅድ የሚሄድ በመሆኑ ታስቦበት ኪሳራና ትርፍን መዝኖ የተሻለውን ማድረግ እንደሚሻል ታምኖበት የተወሰነ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር የራሱ የሆነ መጥፎና ጥሩ ጎን አለው፣ ነገር ግን ተመዝኖ ይወሰናል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ወደፊት ድሮ እንደነበረው የትምህርት ወቅት በመስከረም ተጀምሮ በሰኔ እንዲጠናቀቅና የክረምት ትምህርትም መጀመር ባለበት ከሐምሌ እስከ ጷጉሜን 4 ቀን ድረስ እንዲሰጥ እንደሚደረግ አክለዋል፡፡