Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

  ከወጪ ንግድ የታቀደው ገቢ በ31.8 በመቶ ቀነሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2015 የበጀት ዓመት ለማግኘት ከታቀደው 5.21 ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ 31.8 በመቶ ቅናሽ የተመዘገበበት፣ 3.64 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያገኘችው የወጪ ንግድ ገቢ ይሳካል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘው ገቢ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት ያለው ሲሆን፣ በ2014 የበጀት ዓመት ከተገኘው ገቢ ደግሞ የ480 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የተመዘገበበት መሆኑ ታውቋል፡፡

መንግሥት ካቀደው ገቢ የተገኘው ገቢ የዕቅዱን 69.8 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም ግብርና 79 በመቶ፣ አምራች ኢንዱስትሪ 11.7 በመቶ፣ ማዕድን 6.9 በመቶ፣ እንዲሁም ኤሌክትሪክና ሌሎች ምርቶች ሦስት በመቶ ድርሻ እንዳላቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የ11 ወራት አፈጻጸሙን በሰኔ ወር መጨረሻ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሪፖርት ሲያቀርብ፣ የወጪ ንግድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንዲሆን ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የዓለም የቡና ዋጋ መውረድ፣ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ መስፋፋት፣ የጫት ምርት የታክስና የቀረጥ መጨመር፣ የኬላዎች መበራከት፣ ከድርቅ ጋር በተያያዘ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቁም እንስሳት መጠን መቀነስ፣ የኬሚካል ግብዓት አቅርቦት እጥረትና የትልልቅ ላኪዎች የአውሮፓ ገዥዎች ትዕዛዝ መሰረዝ ተጠቃሾቹ እንደሆኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በተለይም የጫትና የቅባት እህሎች የበጀት ዓመቱ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ እንደሆነ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በተጨማሪም የወጪ ምርቶች በሚመረቱባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ችግር በማጋጠሙ ምክንያት መቀነሳቸውና የተመረቱትም በወቅቱ ለገበያ አለመቅረባቸው፣ በየደረጃው የሚታይ ሌብነትና ብልሹ አሠራር ለወጪ ንግድ አፈጻጸም ማነስ ምክንያት መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳለው ከሆነ፣ በ2015 የበጀት ዓመት አገራዊ የወጪ ንግድን ለማስፋፋት የወጪ ንግድ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠን፣ በጥራትና በገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተው ከተገኙ ውጤቶች መካከል የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ የውልና ኢንቨስትመንት አርሻ አፈጻጸም መመርያ ሪፎርም ተጠቃሾቹ ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህም ከቅባትና ከጥራጥሬ ወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሩ አክሏል፡፡

በ2015 የበጀት ዓመት የወጪ ንግድ ዘርፉ ለአገሪቱ ዕድገትና ልማት የሚያበረክተውን ወሳኝ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው፣ ዘርፉ የአገሪቱን በገቢና ወጪ መካከል ያለውን ከፍተኛ ልዩነት ለማጥበብ ዋነኛ መንገድ እንደሆነና በዚህም መነሻነት ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የውጪ ምንዛሪ ግኝት ለማሳካት ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን መጠን፣ ዓይነትና ስብጥር በመጨመር የኤክስፖርት ፕሮሞሽን ልማትና ስትራቴጂን የማስፋት ሥራ እንደሚከናወን በበጀት ዓመቱ መጀመርያ ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል፡፡

 በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተገኘው 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ካለፉት ዓመታት አፈጻጸም አንፃር በከፍተኛነቱ የተመዘገበ እንደሆነ፣ ከዚያም ውስጥ ጉልህ ድርሻ የተጫወተው ቡና ከግብርና ምርቶች  ከፍተኛ አፈጻጸም የተባለውን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ለመጀመርያ ጊዜ አስገኝቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ2015 የበጀት ዓመት ከቡና ከ1.8 እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም የተገኘው ገቢ1.33 በሊዮን ዶላር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በወጪ ንግድ ዘርፉ የተመዘገበው ውጤት አሁንም ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን የሚያሳይ መሆኑን የሚናገሩት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ አገሪቱ በወጪ ንግድ ልታሳካ ግብ የጣለችበትን ያህል ውጤት በዚህ ወቅት አስመዝግባለች ለማለት የሚያስደፍር አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከወጪ ንግድ የታሰበውን ያህል እንዳይሳካ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ አገሪቱን ብዙ ዋጋ ያስከፈላት ጦርነት መካሄዱና የወጪ ንግድ ምንጭ የሆኑት አንዳንድ ምርቶች ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸው፣ ከመስፋፋት አልፎ የተንሰራፋው ኮንትሮባንድ በዘርፉ ለማሳካት የታቀደው ግብ እንዳይሳካ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

ሰላምና መረጋጋት የወጪ ንግድን ጨምሮ ለሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስኬት ወሳኝ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ በቀጣይ ጊዜያት በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አገሪቱ ወደ ሙሉ ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች