Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ክልላዊና ብሔራዊ ፈተናዎችን አይወስዱም ተባለ

በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ክልላዊና ብሔራዊ ፈተናዎችን አይወስዱም ተባለ

ቀን:

የኢትዮጵያን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ በማያደርጉ አለም አቀፍ ትምህርት ትምህርት ቤቶች (ኢንተርናሽናል ስኩልስ) የሚማሩ ተማሪዎች፣ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ  የ6ኛ ክልላዊ፣ እንዲሁም የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናዎችን እንደማይወስዱ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ለ28 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውና የአዲሱ ሥርዓት ትምህርት መተግበርን ተከትሎ፣ ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ብቻ የተሰጠውን የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ትምህርቶች የኢትዮጵያን ሥርዓተ ትምህርት ያልተከተሉ ናቸው፡፡

ውጤቱን ይፋ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ቱሉ (ዶ/ር) ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርትና አጠቃላይ  ከትምህርት መዋቅሩ ሽግግር ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ በግል ትምህርት ቤቶች ያሉ ፍላጎቶች፣ ‹‹አንዳንዱ ከአገር አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታና ህልውና ጋር የሚገናኙ ሆነው አግኝተናል፤›› ብለዋል፡፡

በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች አስፈላጊ ነው ተብሎ በማይታመንበት ሁኔታ ሥርዓተ ትምህርቱን በመጥላትና በመሸሽ፣ ወደ ዓለም አቀፍ ትምህር ቤቶች (ኢንተርናሽናል ስኩልስ) የመግባት ፍላጎቶች እንደታዩም ጠቁመዋል፡፡

የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት ወስዶና ተማሪዎችን አብቅቶ ለዚህች አገር ማዘጋጀት ላይ ከፍተኛ ክፍተት በመታየቱም፣ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ተብለው በተቀመጡት ውስጥ የተመዘገቡ ተማሪዎች፣ ከ2016 የትምህርት ዘመን ጀምሮ የ6ኛ፣ የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አይሳተፉም ብለዋል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት አክብረውና ተግብረው ስለማይገኙ፣ የሚማሩትና የሚተገብሩት የሌላ አገር ሥርዓተ ትምህርት ሆኖ ስለሚገኝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት በመሸሽ የሌላ አገር ሥርዓተ ትምህርት ለመተግበርና ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ሊያገለግሉ የሚችሉ ተማሪዎች ከማዘጋጀት ይልቅ፣ በሌላ አገር ሥርዓተ ትምህርት፣ ባህልና እሴት ኮትኩቶ በማሳደግ የአዕምሮ ፍልሰት (ብሬንድሬን) እንዲኖርና ለሌላ አገር ምቹ የሆኑ ተማሪዎችን ማሳደግ ላይ መሆናቸውን ተናግረው፣ ይህ ማለት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት ማለት እንዳልሆነም አክለዋል፡፡

መረጃ የሌላቸው ወላጆች፣ አሳዳጊዎችና ሌሎች አካላት ከወዲሁ በመገንዘብ ውሳኔያቸውን እንዲያስተካክሉ የገለጹት ዘላለም (ዶ/ር)፣ ‹‹በራሳችን ሥርዓተ ትምህርት፣ በራሳችን አቅም ጠንከር ያለ ሥርዓት በመገንባትና ጥራትን በማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንችላለን ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

ውሳኔውን በመተግበሩ ሒደት የትምህርት መዋቅሩ፣ እስከ ታች ያለው እርከን ድረስ ያለው አመራር፣ የትምህርት ባለሙያና መምህራን ኃላፊነት እንዳለባቸው ከዚህ ውጪ የሚያፈነግጡ ትምህርት ቤቶችና በተግባር ውስጥ ያሉት የፈተናዎቹ ተጠቃሚ  እንደማይሆኑም ተናግረዋል፡፡

ቢሮው ይህንን በማስተግበር ተማሪዎች የሚፈለገውን የትምህርት ይዘት አግኝተው፣ ወደ ቀጣይ የትምህርት ዕርከን አልፈውና አገር ተረክበው አገር ማስተዳደር፣ ማብቃትና ማቆም የሚችል ትውልድ መገንባት ላይ ይሠራል ብለዋል፡፡

ውሳኔውም ሁለንተናዊ ሰብዕና፣ በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ተቆርቋሪነት ማደግ የሚችሉ ሕፃናትን መኮትኮት ያስፈልጋል ከሚለው እንደሚነሳ ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚማሩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን ሥርዓተ ትምህርት በመጥላትና አስፈላጊ አይደለም ብሎ በማመን ጠቅላላ ተማሪዎችን ይዞ የመሄድ ፍላጎቶች አሉ ብለዋል፡፡

እንደ ዘላለም (ዶ/ር)፣ ትምህርት ቤቶቹ ሥርዓተ ትምህርቱን ለምን እንደማይተገብሩ በሦስት መሥፈርቶች ተገምግመዋል፡፡ በዚህም አንደኛው የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት ያለ መቀበልና ያለ መፈለግ፣ ሁለተኛ ከቁጥጥር ለመውጣት ከመፈለግና ሦስተኛው በማናለብኝነት ሕግና ሥርዓትን ካለመፍራት የሚመነጩ መሆናቸው ታውቋል ብለዋል፡፡

ወላጆች ይህንን እንዲያውቁትና ተማሪዎቹ ምን ይሆናሉ የሚለውን እነሱ እንዲወስኑ፣ ወላጅ የትኛው ይሻላል ብሎ እንዲመርጥ ያሉት ኃላፊው ሕግና ሥርዓት አስከብሮ መሄድ፣ በሕግና ሥርዓት ብቻ መሥራት፣ ፖሊሲው በሚያዘውና በፖሊሲው መሠረት ብቻ መተግበር ግድ ስለሆነ የትምህርት መዋቅሩ ለተሰጠው ኃላፊነት ተገዥ ሆኖ ሥራዎችን እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...